1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቦምባስ ከተማ የፀጥታ ኃይሎችና የታጠቁ ግለሰቦች 11 ሰዎች መግደላቸውን ኢሰመኮ አረጋገጠ

ሐሙስ፣ ግንቦት 4 2014

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በምህጻሩ ኢሰመኮ የደረሰውን ጥቆማ መነሻ በማድረግ በሶማሌ ክልል ጉርሱም ወረዳ ቦምባስ ከተማ አደረግሁት ባለው ምርመራ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች እና የታጠቁ ግለሰቦች በ11 ሰዎች ላይ ከፈጸሙት ግድያ ሌላ ቢያንስ በ33 ሰዎች ላይ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ማረጋገጡን ተናግሯል።

https://p.dw.com/p/4BDBD
Daniel Bekele | Leiter der äthiopischen Menschenrechtskommission
ምስል EDUARDO SOTERAS/AFP/Getty Images

በቦምባስ ከተማ የፀጥታ ኃይሎችና የታጠቁ ግለሰቦች 11 ሰዎች መግደላቸውን ኢሰመኮ አረጋገጠ


በሶማሌ ክልል ጉርሱም ወረዳ ቦምባስ ከተማ የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች እና የታጠቁ ግለሰቦች መጋቢት 11 እና 12 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የጎሳ መሪ ለመምረጥ በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ በፈፀሙት ጥቃት 11 ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በምህጻሩ ኢሰመኮ ይፋ አደረገ። ኮሚሽኑ የደረሰውን ጥቆማ መነሻ በማድረግ አደረግሁት ባለው ምርመራ በታጠቁ ሰዎች የተፈፀመው ግድያ እና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከመጠን ያለፈ የኃይል አጠቃቀም ቢያንስ በ33 ሰዎች ላይ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ማረጋገጡን ተናግሯል። ኢሰመኮ የዐይን ምስክሮችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን ፣ የሀገር ሽማግሌዎችን እና የአካል ጉዳት ሰለባ የሆኑትንና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን በማነጋገር ምርመራውን ማድረጉን ዐስታውቋል። ቦምባስ በተባለው ከተማ የሚገኙ የጥቃቱ ሰለባዎች የተቀበሩበትን ሥፍራ መጎብኘቱን የገለፀው ኮሚሽኑ በዚህም በመጀመርያው እለት ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች የተቀበሩበትን አንድ የጅምላ መቃብር እና በሁለተኛው ቀን የተገደለች ሴት የተቀበረችበት ለብቻው ያለ አንድ ሌላ የመቃብር ቦታ መምልከቱንም ገልጿል። ኮሚሽኑ በመግለጫው እንዳለው የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በዚህ ችግር ምክንያት ሕይወታቸውን ላጡ ሰዎች ቤተሰቦች እና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የገንዘብ ካሳ ከፍሏል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ የተሟላ ፍትሕ ለማረጋገጥ እና ለወደፊትም ተመሳሳይ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይከሰቱ ለመከላከል የወንጀል ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ይገባል፣ በአፋጣኝ የወንጀል ምርመራ መጀመር ያስፈልጋል ማለታቸውንም ተቋሙ ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።

ሰሎሞን ሙጬ

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ