1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ውሎ

ዓርብ፣ ሐምሌ 5 2016

የሲዳማ ክልል 3ኛ ዓመት 7ኛ መደበኛ ጉባኤውን በሀዋሳ ከተማ እያካሄደ ይገኛል ፡፡ ም/ቤቱ የክልሉን ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል፡፡ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በአቶ ደስታ ሌዳሞ የቀረበው የ2016 ዓ.ም የሥራ ሪፖርት በማህበራዊ ፣ በምጣኔ ሀብታዊና በመልካም አስተዳደር ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትን የዳሰሰ ነው ፡፡

https://p.dw.com/p/4iDxY
የሲዳማ ክልል 3ኛ ዓመት 7ኛ መደበኛ ጉባኤ
የሲዳማ ክልል 3ኛ ዓመት 7ኛ መደበኛ ጉባኤምስል Shiwangizaw Wogayehu/DW

የሲዳማ ክልል 3ኛ ዓመት 7ኛ መደበኛ ጉባኤ

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ውሎ  

የሲዳማ ክልል 3ኛ ዓመት 7ኛ መደበኛ ጉባኤውን ከትናንት ሐሙስ ጀምሮ በሀዋሳ ከተማ እያካሄደ ይገኛል ፡፡ ምክር ቤቱ በትናንት እና በዛሬው ውሎው የክልሉን ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል፡፡ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በአቶ ደስታ ሌዳሞ የቀረበው የ2016 ዓ.ም የሥራ ሪፖርት በማህበራዊ ፣ በምጣኔ ሀብታዊና በመልካም አስተዳደር ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትን የዳሰሰ ነው ፡፡

ክልሉ በዓመቱ ምን ከወነ ? 

በምክር ቤቱ ጉባኤ ላይ የመንግሥታቸውን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ በዓመቱ በግብርና ፣ በትምህርት ፣ በጤና ፣ በመስኖ ልማት እና በመሠረተ ልማት ግንባታ ተከናውነዋል ያሏቸውን ተግባራት በኅሃዝ በማስደገፍ ጠቅሰዋል ፡፡ ከጉባዔው ጎን ለጎን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ በክልሉ በግብርና፣ በመስኖ ፣ በሥራ እድል ፈጠራ እና በሌሎች ዘርፎች የተሻሉ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል ፡፡

በተለይም በውሃ ዘርፍ በ8 ወረዳዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ሥራዎች መከናወናቸውን የጠቀሱት ዋና አፈ ጉባዔዋ በግብርናው ዘርፍ በቤተሰብ ደረጃ የጓሮ ልማት በማከናወን ሠፊ ምርት ተገኝቷል ፡፡ በጤና ዘርፍም የመድሃኒት አቅርቦትን ለሟሟላት በ30 ሚሊየን ብር ግዢ ተፈጽሞ ለጤና ተቋማት እንዲሠራጭ ተደርጓል ፡፡ እንዲሁም የትምህርት እና የመንገድ መሠረተ ልማቶችም ተከናውነዋል ፡፡ በሪፖርቱ የተጠቀሱት ሥራዎች በትክክል መሬት ላይ የተከናወኑ ሥለመሆናቸው በቋሚ ኮሚቴዎቻችን አማካኝነት የመስክ ግምገማ በማድረግ አረጋግጠናል  “ ብለዋል ፡፡

የእርምት እርምጃዎች

በሲዳማ ክልል በዓመቱ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የህዝብ ቅሬታ የሚነሳባቸው የአስፈጻሚ አካላት እና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በተመለከተ የክትትል እና የእርምት እርምጃዎች መወሰዳቸውን ዋና አፈ ጉባዔዋ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ ገልጸዋል ፡፡ በተለይም በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ለህዝቡ ቅርበት ያላቸው በታችኛው መዋቅሮች ክፍተቶች እንደነበሩ የጠቀሱት አፈ ጉባዔዋ “  ምክር ቤቱ ከመደበኛ የክትትልና የቁጥጥር ሥራው በተጨማሪ ድንገተኛ ምልከታ በማድረግ ችግሮችን ለመለየት ጥረት አድርጓል ፡፡ ከተገኘው የግምገማ ውጤት በመነሳት በአስፈጻሚ አካላትና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አመራሮች ላይ ከሃላፊነት ማንሳት እስከ ህግ ተጠያቂነት የሚደርሱ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ በተጨማሪም በምክር ቤቱ በተቋቋመው የኦዲት ግብረ ሃይል አማካኝነት ከፍተኛ መጠን ያለው የመንግስት ገንዘብ ለማስመለስና አጥፊዎችንም ተጠያቂ ለማድረግ ተችሏል “ ብለዋል ፡፡

የምክር ቤት አባላቱ ምን አሉ ? 

ዶቼ ቬሌ በምክር ቤቱ የቀረበውን ሪፖርት ላይ እንዴት አያችሁት ሲል ጠይቋል፡፡ ከዱባ ምርጫ ክልል የህዝብ ተወካይ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ኢሽኔ ሀንቃሎ በክልሉ በዓመቱ የተሻሉ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል ፡፡ ይሁንእንጂ በቀጣይ የበለጠ ትኩረት የሚሰጣቸው ተግባር መኖራቸውን የጠቀሱት የምክር ቤት አባሉ “ በተለይም በክልሉ የከፍተኛ ትምህርታቸውን አጠናቀው ያለሥራ የተቀመጡ ብዙ ወጣቶች ይገኛሉ ፡፡ እነኝህን ለማደራጀትና ወደ ሥራ ለማስገባት የተጀመሩ ሥራዎች ቢኖሩም ካለው የፍላጎት ሥፋት አንጻር ከዚህ የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል “ ብለዋል ፡፡

ከበሌላ የምርጫ ጣቢያ መምጣቸውን የተናገሩት  ወይዘሮ አማረች  ሰቀሎ በክልሉ በበጀት ዓመቱ ሊታዩ የሚችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል ፡፡ ይሁንእንጂ እሳቸው በተወከሉበት የበሌላ ወረዳ የገጠር መንገድ ችግር መኖሩን የተናገሩት የምክር ቤት አባሏ “ ወረዳው  ቆላማ የአየር ንብረት ያለውና ቀደምሲልም ግጭት የነበረበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአስፈጻሚውን ትኩረት አላገኘም ፡፡ ህዝቡ ከረጅም ጊዜ አንስቶ እየጠየቀ የሚገኘውን የመንገድ ልማት ነው ፡፡ የህዝቡን ጥያቄ እዚህ ምክር ቤት ላይ በተደጋጋሚ ያነሳን ቢሆንም እስከአሁን ተፈጻሚ ሊሆን አልቻለም ፡፡ አሁንም ጥያቄውን ለጉባዔው እያቀረብን እንገኛል “ ብለዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ 

ፀሐይ ጫኔ