1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሰሜን ያገረሸው ውጊያ በሌሎች አከባቢዎች የሚኖረው አንድምታ

ሰኞ፣ ነሐሴ 23 2014

በሰሜን ኢትዮጵያ ያገረሸው ጦርነት በአገሪቱ የተለያዩ አከባቢዎች ሰፊ የሆነ አለመረጋጋት ሊያስከትል እንደሚችል ፖለቲከኞች አመለከቱ። በተለይም የሰሜን ኢትዮጵያውን ያህል ትኩረት እንዳላገኘ የሚነገረው የኦሮሚያ ክልሉ ግጭት ተባብሶ በመቀጠል ሰብዓዊ ቀውሱን ሊያደርገው እንደሚችልም ግምታቸውን ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/4GBkK
Tigray-Krise in Äthiopien
ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP

የኦሮሞ ፖለቲከኞች አስተያየት

በሰሜን ኢትዮጵያ ያገረሸው ጦርነት በአገሪቱ የተለያዩ አከባቢዎች ሰፊ የሆነ አለመረጋጋት ሊያስከትል እንደሚችል ፖለቲከኞች አመለከቱ። በተለይም የሰሜን ኢትዮጵያውን ያህል ትኩረት እንዳላገኘ የሚነገረው የኦሮሚያ ክልሉ ግጭት ተባብሶ በመቀጠል ሰብዓዊ ቀውሱን ሊያደርገው እንደሚችልም ግምታቸውን ገልጸዋል። ከአንድ ኣመት በፊት ከህወሓት ጋር አብሮ የመታገል ስምምነት ማኖራቸውን የገለጹት በኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱ ተፋላሚ ኃይላት በኦሮሚያ ለሚፈጸሙ ንጹሃን ላይ ላነጣጠሩ ግድያዎች በመንግሥት ክስ ይቀርብባቸዋል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት በሽብርተኝነት የፈረጃቸው ህዝባዊ ወያኔ ኃርነት ትግራይ (ህወሓት) እና እራሱን «የኦሮሞ ነጻነት ጦር» ብሎ የሚጠራውና መንግሥት «ሸነ» ያለው ሸማቂ ቡድን በጋራ ስልታዊ የጦር ትብብር አሁን አገሪቱን እየመራ ያለውን መንግሥት እንደሚወጉ በይፋ ካሳወቁ አንድ ዓመት ገደማ እየተቆጠረ ነው። መንግሥት በፊናው ከትግራይ ክልል ውጭ በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች፤ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ለሚስተዋሉ ግጭትና ግጭቱ ለሚያስከትላቸው ጥፋቶች የህወሓት እና «ሸነ» ያለውን «የኦሮሞ ነጻነት ጦር’ ስምን በተደጋጋሚ በተጠያቂነት ሲያነሳቸው ተስተውሏል፡፡

በቅርቡ እንኳ ከአንድ ወር በፊት ምዕራብ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች ውስጥ ለተከሰቱ የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ላነጣጠረው የጅምላ ግድያ መንግሥት በተጠያቂነት የከሰሰው ኦሮሚያ ውስጥ በሰፊው ታጥቆ የሚንቀሳቀሰውን «ሸነ» ያለውን ታጣቂ ቡድን ነው፡፡፡ በርግጥ ሸማቂ ቡድኑ በፊናው ብሔር ላይ አነጣጥሮ ለሚፈጸመው ግድያ ወደ የመንግሥት ታጣቂዎች በመጠቆም ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግም ሲጠይቅ ቆይቷል።

ለወራት የተናጥል ተኩስ አቁም ተደርጎበት ለዘብ ብሎ የታየውና ሰላማዊ እልባትም ሲፈለግለት የቆየው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከሰሞኑ ማገርሸቱም ስጋቱን በሰሜን የአገሪቱ አከባቢዎች ብቻ ያጠላ አልሆነም፡፡ በኦሮሚያ በርካታ ዞኖችን ያዳረሰው ግጭትና አለመረጋጋት ከወትሮም በከፋ አሁንም እንዳይቀጥል የሰጉ በርካቶች ናቸው።ወትሮም ከሰሜኑ እኩል ትኩረት አልተሰጠውም የተባለው «የኦሮሚያው ግጭት» አሁንም በአሳሳቢነቱ ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችል ከተናገሩት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከፍተኛ ባለሥልጣን ፖለቲከኛ ሙላቱ ገመቹ ይገኛሉ።

Tigray-Krise in Äthiopien
ምስል Eduardo Soteras/AFP

እሳቸው እንደሚሉት ጦርነቱ በኦሮሚያ ያደረሰው ጥፋትና ሰቆቃ ከዓለም ዕይታና ትኩረት የተደበቀ ይመስላል። ከትግራዩ ጦርነትም አስቀድሞ አራት ዓመታት ገደማ እያስቆጠረው ነው ያሉት በኦሮሚያ በሸማቂ ቡድኖች እና በመንግሥት መካከል የሚደረገው ፍልሚያ በርካቶችን ለረሃብና ለሰቆቃ መዳረጉንም አክለው አብራርተዋል። ሌላው አስተያየታቸውን ያጋሩን ፖለቲከኛ የገዳ ስርዓት ለኦሮሞ ነጻነት (ገዳ ቢሊሱማ) ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሮበሌ ታደሰ ናቸው፡፡ እንደ አቶ ሮቤለ ማብራሪያ ሁሉም ተፋላሚዎች የህዝብ ጥያቄን ማዕከል ወደ አደረገ ውይይት ካልሄዱ ግጭቱ ተባብሶ ከቁጥጥር ውጪ ወደመሆን ሊያመራ ይችላል።

የህወኃት ኃይሎችና መንግሥት «ሸነ» ያላቸው በኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱ ሸማቂ ኃይላት ከአንድ ዓመት በፊት ደርሰውበታል የተባለው አብረው የመዋጋት ትብብር አሁን በሰሜን ኢትዮጵያ ካገረሸው ጦርነት አንጻር በኦሮሚያ ምን ሊያስከትል ይሆን የተባሉት ፖለቲከኛ ሙላቱ ገመቹ፤ የሁለቱን ታጣቂ ቡድኖች ስምምነት ዝርዝር ጉዳይ አንደማያውቁ ገልጸው፤ አሁንም ግን ለሰላማዊ መፍትሄ አለመርፈዱን ገልጸዋል።

ሥዩም ጌቱ 

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ