1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በረራ ወደ ነቀምት

ሰኞ፣ ሰኔ 10 2016

ከዚህ ቀደም ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ ለመጓዝ በተለይም ከሶስት ወራት በፊት ዳግም ስራውን የጀመረው የደምቢዶሎ አየር ማረፊያ ስራውን ከመጀመሩ በፊት በየብስ ከመጓዝ ውጪ ምንም አይነት አማራጭ አልነበረም፡፡

https://p.dw.com/p/4h96P
Ethiopian Airlines EAL CEO Inauguration, Addis Abeba, Ethiopia
ምስል Seyoum Getu/DW

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ነቀምቴ የጀመረው በረራ

የነቀምቴ ጉዲና ቱምሳ አውሮፕላን ማረፊያ የበረራ ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት በትናትናው እለት የመንግስት በለስልጣናት እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ስራውን በይፋ መጀመሩ ተበስሯል፡፡
የአውሮፕላን ማረፊያው ተገንብቶ አገልግሎት መጀመር በአካባቢው የሚገኘውን የተፈጥሮ ጸጋ በተሻለ ለማልማት፣ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማስፋት ብሎም ቱሪዝምን ለማነቃቃት አወንታዊ ሚና ይጫወታል ተብሏል፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ የሕዝቦችን ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ለማቀላጠፍ ብሎም በአጠቃላይ የሕዝቡን ሕይወት ለመቀየር ይህ ጉልህ ሚና እንዳለውም ነው የተገለጸው፡፡ ለታ ዘሪሁን የምእራብ ኦሮሚያ አከባቢዎች ማዕከል በሆነችው ነቀምቴ ከተማ ተወልዶ ማደጉንና አሁን ደግሞ ንሮውን በአዲስ አበባ በመመስረት እንደሚኖር ይገልጻል፡፡ ለታ ትናንት የተጀመረውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ነቀምቴ የሚያደርገውን በረራ በጉጉት ሲጠብቁ ከነበሩ የአከባቢው ተወላጆች ውስጥ ይጠቀሳልም፡፡ ለዚህም ይመስላል ታሪካዊ ባለው በትናንቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የነቀምቴ የመጀመሪያ በረራ ለመጠቀም መረጃው ከደረሰው ቀን ጀምሮ አስቀድሞ ትኬት በመቁጥ ሲጠባበቅ የነበረው፡፡
“የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደዚያ ይበራል የሚባለውን መረጃ ከሰማሁበት ቀን ጀምሮ ወደዚያው ለመሄድ እቅድ ነበረኝ፡፡ ከግል እቅድም ባሻገር የታሪካዊ ሁነቱ ተካፋይ መሆኑንም አስደሳች ነው፡፡ የአየር ማረፊያ በአከባቢው መከፈቱ በየትኛውም አቅጣጫ ስንመለከተው ፋይዳው ጉልህ ነው፡፡ የአከባቢውን ማህበረሰብ ከመጥቀም ታዳጊዎች ይህን አይተው ትልቅ እንዲያልሙ ከማድረግ ጀምሮ ኢኮኖሚውን ከማነቃቃትና ቱሪዝም ከመሳብም አንጻር ፋይዳው ትልቅ እንደሚሆን መገመት ቀላል ነው፡፡ ከአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ተጓዦች ወደዚህ እንድሳቡ በጣም የሚጠቅም ነው” ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላንምስል AP


የአየር ትራንስፖርት ለጊዜያዊው የጸጥታ ስጋቶች እንደ መፍትሄ
ከዚህ ቀደም ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ ለመጓዝ በተለይም ከሶስት ወራት በፊት ዳግም ስራውን የጀመረው የደምቢዶሎ አየር ማረፊያ ስራውን ከመጀመሩ በፊት በየብስ ከመጓዝ ውጪ ምንም አይነት አማራጭ አልነበረም፡፡ የዚህን የየብስ ትራንስፖርት ጉዞን ደግሞ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአከባቢው አለመረጋጋትን ተከትሎ የጸጥታው ይዞታ ይፈትነዋል፡፡ የአከባቢው ተወላጅ ለታም ይህን እውነታ አረጋግጧል፡፡
“እውነት ለመናገር ያሳስበኝ ነበር፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ በረራ ሳደርግ እነ የዚህ የምዕራብ ኦሮሚያ አከባቢ ተወላጅ እንደመሆነ እመኝም ነበር፡፡ እቀናለሁም፡፡ ለምሳለ ሳነሳልህ በአገር ውስጥ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ መቀሌ በየብስ ለመጓዝ የጸጥታ ሁኔታ ብያሰጋህ በቀላሉ በአየር ደርሰህ ትመጣለህ፡፡ ያንን ሳደርግ እኔም መቼ ይሆን በቀላሉ አንድም ለደህንነት ስጋት ሳይዘኝ ሌላም ጊዜን በሚቆጥብ አኳሃን ቤተሰቦቼን እየጠየቅኩ የምመለሰው እያልኩ አስብ ነበር፡፡ በሚወራው ደረጃ ባይሆንም እንኳ የጸጥታ ሁኔታም አልፎ አልፎ በመኪና መጓዝ ስለሚያሰጋ ደግሞም በአጭር ሰዓት ውስጥ ነቀምቴ ደርሰህ መመለስ ስለምትችል፤ ደግሞም በአቅራቢያው ወዳሉ ሌሎች የምዕራብ ኦሮሚያ አከባቢዎችንም መድረስ ስለሚያቀል አሁን በጣም ተደስቻለሁ” ነው ያለው፡፡
ሌላም ለዶይቼ ቬለ አስተያየታቸውን የሰጡ የነቀምቴ ዙሪያ ተወላጅ እና አሁን ላይ ኑሮያቸውን በመዲናዋ አዲስ አበባ መስርተው የምገኙት አስተያየት ሰጪ አልፎ አልፎ የየብስ ትራንስፖርት ላይ ያጋጥም ነበር ያሉት የደህንነት ስጋቶች እንዲህ ያለን ቀን እንድጠባበቁት አድርጓቸው ቆይቷል፡፡ “አሁን እንደ ኢትዮጵያ እንኳ ስትመለከት የአገር ውስጥ በረራ ተጠቃሚዎች በጣም ጨምረዋል፡፡ ይህ ደግሞ የሆነው የፀጥታ ችግር በተለያዩ አከባቢዎች ስላለ ነው፡፡ ይህም የተለየ አይደለም፡፡ ትልቁ ጉዳይ የበረራውን መጀመር አስደሳች የሚደርገው ለዚህ ችግር ሁነኛ መፍትሄ ስለሚሆን ነው፡፡ በየብስ መጓዝ ችግር በሚሆንበት ጊዜ በተለይም ብዙ ሰው የአየር አማራጩን እንዲጠቀም ይረዳል፡፡ በርግጥ በየብስ እንቅስቃሴ ነበር ወደ ነቀምቴ ሁል ጊዜም፡፡ ይሁንና ለደህንነታቸው የሚፈሩ በተለያዩ ሃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች ጉዳይ እንኳ ብኖራቸው ስጋት ነበራቸው፡፡ እኔም እራሴ በተለያዩ አጋጣሚዎች ለመሄድ እያሰብኩ የሆነ ነገር ያጋጥመኛል በሚል ስጋት ሳልሄድ ቀርቻለሁ” በማለት አስተያየታቸውን አጋርተውናል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰውምስል Seyoum Getu/DW


የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገር ውስጥ መዳረሻዎችን የማስፋት ውጥን
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ትናንት ስራውን በይፋ የጀመረውን የነቀምቴ አየር ማረፊያን ስራ ከማስጀመር ባለፈ በአገር ውስጥ የአየር መንገዱን መዳረሻዎች የማስፋት ትልቅ ውጥን መኖሩን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ “የነቀምት አየር ማረፊያን ስንገነባ ቆይተናል፡፡ አሁንም ሌሎች በግንባታ ላይ ያሉ የአገር ውስጥ መዳረሻ ማስፋፊያዎች አሉ፡፡ አየር መንገዱ መዳረሻዎቹን በአገር ውስጥ በማስፋት ህዝቦችን ተጠቃሚ ማድረግ ብሎም ቱሪስቶች በቀላሉ በአገሪቱ ከቦታ ቦታ እንዲንቀሳቀሱ ጥረት እያደረገም ነው” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ነቀምቴ ጉዲና ቱምሳ አውሮፕላን ማረፊያ በሣምንት ሦስት ጊዜ እንደሚበር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ ጠቁሟል፡፡
ስዮም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
አዜብ ታደሰ