1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ንጹሃን ላይ የተፈጸመ ግድያ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 11 2016

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ቢፍቱ ጃለላ ቀበሌ ልዩ ስሙ ቆንዳላ በሚባል አከባቢ ባለፈው ዓርብ ሌሊት ለቅዳሜ አጥቢያ በንጹሃን ዜጎች ላይ ባነጣጠረ የታጣቂዎች ጥቃት ወደ 30 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸው ተነገረ፡፡

https://p.dw.com/p/4hCuH
Äthiopien | Oromiya Region
ምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

በጥቃቱ የደረሰው ጉዳት

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ቢፍቱ ጃለላ ቀበሌ ልዩ ስሙ ቆንዳላ በሚባል አከባቢ ባለፈው ዓርብ ሌሊት ለቅዳሜ አጥቢያ በንጹሃን ዜጎች ላይ ባነጣጠረ የታጣቂዎች ጥቃት ወደ 30 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸው ተነገረ፡፡ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የአይን እማኞች እና የአከባቢው ነዋሪዎች ጥቃቱ በሰርግ ቤት ላይ በተወረወረ ቦንብ እና የቤቶች ቃጠሎ የተፈጸመ በመሆኑ ሙሽኖችን ጨምሮ በሰርጉ ቤት የነበሩ ሁሉ አልቀዋል ነው ያሉት፡፡ በጥቃት አድራሾቹ የሰርግ ቤቱ ተዘግቶ እንዲቃጠል በመደረጉ በክስተቱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር እንኳ መለየትን አዳጋች ማድረጉንም ነዋሪዎቹ አመልክተዋል፡፡ 

በጥቃቱ የደረሰው ጉዳት

ዓርብ ሌሊት ለቅዳሜ አጥቢያ ምሽቱን በግምት ከ4-5 ሰዓት ተፈጸመ በተባለው በዚህ የታጣቂዎች ጥቃት በአንድ ጊቢ ውስጥ ካሉ ቤቶች ውስጥ የተረፈ አንድም ሰው አለመኖሩን የዐይን እማኖች ተናግረዋል፡፡ በዚህ ቀበሌ ከዚህ በፊት በድርቅ ምክንያት ከሀረርጌ እና አርሲ ተፈናቀለው የነበሩ በብዛት ይኖሩበታል ያሉን ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀው አስተያየት የሰጡን ነዋሪ ሁሉም ሰው በእሳት ጋይቶ ባለቀበት ከሰርጉ ቤት ጥቃት በሙሉ አካል አግኝተን የምንቀብረውን እስከማሳጣት የደረሰው ጥቃት እጅጉን አሰቃቂ ነው ይሉታል፡፡ "ክስተቱ መፈጠሩን ሰምተን እንደ አከባቢው ነዋሪ ለመድረስ ስንሄድ ነው የሰዎቹን ማለቅ ያየነው እንጂ በምን ምክንያት ነው የተከሰተው የምለውን አናውቅም፡፡ ማታ ላይ የመሳሪያ ድምጽ እና በእሳት የሚጋየውን ቤቶቹን እየተመለከትን ነበር ያደርነው፡፡ ከአከባቢውም ብዙ ሰው በቻለ መጠን ስሸሽ ነበር፡፡ በዚያ ሁኔታ ማታውኑ ሄደን ለመርዳት ባለው የጸጥታ ሁኔታ   በመስጋታችን ቅዳሜ ጠዋት በንጋታው ነው ሄደን የሆነውን የተመለከትነው፡፡ በማግስቱ ደርሰን የሰርጉ ቤት ውስጥ የሆነውን ስናይ ተቃጥሎ ነዶ ያለቀ የሰው በድን፣ አንስሳት፣ እህል እና የወደሙ የተለያዩ ንብረቶችን አየን፡፡ ከቤቱ ውስጥ ሙሽሮቹን ጨምሮ 28 ሰው ተቃጥለዋል፡፡ ውጪ ላይ በጥይት የተመቱትን ስጨምር ከ30 ሰው በላይ አልቀዋል” ነው ያሉት፡፡

የክስተቱን መነሻ ምክንያት ለመረዳት አለመቻላቸውን የገለጹት ሌላው አስተያየት ሰጪ የአከባቢው ነዋሪ ምናልባትም ጥቃቱ ፖለቲካዊ ፍላጎት ያነገበ ካልሆነ በስተቀር የሞቱት ሁሉ ንጹሃን ሰላማዊ የአከባቢው ነዋሪ ናቸው ይላሉ፡፡ "ለጥቃቱ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለማወቅ ተቸግረናል፡፡ የታጠቁ ሰዎች ኦሮሞ በመሆናቸው በማንነታቸው ጥቃቱ ከተነጣጠረባቸውም አናውቅም፡፡ በማግስቱ ስንደር ለቅመን የቀበርነው አስከረን ያው ይሄ የነደደ የሰው በድን በሳፋ በመሰብሰብ ነው፡፡ በዚያ ውስጥ እንደ አንጨት ነደው ያለቀው 24 ሰው መሆኑን ተረድተናል፡፡ ውጪ ላይ በጥይት ተመተው ከቆሰሉ 19 ሰዎችም በብዛት ወደ ህክምና ስወሰዱ አራት ሰው ግን ሞተዋል፡፡ ከዚያ ውጪ በዚያ ምሽት ታጣቂዎቹ የሰርግ ቤቱን ከውጪ ቆልፈው ቦንብ ወርውረው በእሳት ሲያጋዩ ለማዳን የደረሱ ጎረቤቶች ደርሰው እንዳያድኗቸው ዝርያለውን ሰው ሁሉ በጥይት ስመቱዋቸው ነበርና አንድም ሰው ማዳን አልተቻለም” ነው ያሉት፡፡

ዓርብ ሌሊት ለቅዳሜ አጥቢያ ምሽቱን በግምት ከ4-5 ሰዓት ተፈጸመ በተባለው በዚህ የታጣቂዎች ጥቃት በአንድ ጊቢ ውስጥ ካሉ ቤቶች ውስጥ የተረፈ አንድም ሰው አለመኖሩን የዐይን እማኖች ተናግረዋል፡፡
ዓርብ ሌሊት ለቅዳሜ አጥቢያ ምሽቱን በግምት ከ4-5 ሰዓት ተፈጸመ በተባለው በዚህ የታጣቂዎች ጥቃት በአንድ ጊቢ ውስጥ ካሉ ቤቶች ውስጥ የተረፈ አንድም ሰው አለመኖሩን የዐይን እማኖች ተናግረዋል፡፡ ምስል Seyoum Getu/DW

የጥቃት አድራሾች ማንነት

ሌላም አስተያየት ሰጪ የአከባቢው ነዋሪ ተመለከትኩ ያሉትን እዲህ አስረዱን፡፡ "በዚያ ሌሊት በአከባቢው ታጣቂዎች የምንቀሳቀሱ የጽንፈኛው ታጣቂዎች የሰርግ ስነስርዓት የነበረበትን ቤቱን ከበው በር በሙሉ ዘግተው ነው ቦንብ የወረወሩባቸው፡፡ ከዚያን ከውጪ እሳት አያያዙባቸው፡፡ ለድረስ የመጣን ሰው ሁሉ እንዳያድኗቸው በጥይት እየመቱ ይከለክሉም ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ የማህበረሰቡ ጥላቻ ካልሆነ በስተቀር ይህ ነው የሚባል ጥል የለም፡፡ ግን ጽንፈኞች ታጣቂዎችን በጊቤ በረሃ ስያሰለጥኑ እንደነበር ይሰማ ነበር፡፡ ምናልባት ጥቃቱን ለፈጸሙት ፖለቲካም ሊሆን ይችላል እኛ አናውቅም፡፡ መንግስትም ያን ያህል አስተማሪ እርምጃ እየወሰደ አለመሆኑ ይመስላል የመሰል ክስተት በአከባቢው መደጋገም” ሲሉ በጉዳዩ ተማረው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የአከባቢው የፀጥታ እጦት ዳራ

ከዚህ በፊትም በ2014 ዓ.ም. በዚሁ ኖኖ ወረዳ መቱ-ስላሴ ቀበሌ የታጠቁ ኢ-መደበኛ አካላት  አደረሱ በተባለ ጥቃት ከ30 በላይ ንጹኀን የአከባቢው ማህበረሰብ ማለቃቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ባሁኑ የኖኖ ጥቃት በእለቱ ከተቀጠፈው የሰው ህይወት በተጨማሪ ቢያንስ ከ20 በላይ ቤቶች በቃጠሎ መውደማቸውን ነዋሪዎቹ በአስተያየታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ስለጥቃቱ እና አሁናዊ የአከባቢውን ሁኔታ በተመለከተ ተጨማሪ መረጃዎችን ለመጠየቅ ዶይቼ ቬለ ለአከባቢው ኮማድ ፖስት ኃላፊ አቶ ተሾመ ሰቦቃ እንዲሁም ለወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አለማየሁ ወርቁ ደጋግሞ ብደውልም ለዛሬ ምላሻቸውን ማግኘት አልተቻለም፡፡ የአከባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ግን ከክስተቱ ማግስት ከቅዳሜ ጠዋት ጀምሮ የአገር መከላከያ ሰራዊት ቦታው ላይ ሰፍሮ ተጨማሪ ጉዳቶች እንዳይደርሱ የመከላከል ስራ እየሰራ ነው፡፡ 

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ    

አዜብ ታደሰ