በመቀሌ ለቀናት ሲካሄድ የቆየው የተፈናቃዮች ተቃውሞ ዛሬ ተጠቀቀ
ሐሙስ፣ ጥር 8 2017ለቀናት በመቐለ የተቃውሞ ሰልፍ ሲያካሂዱ የሰነበቱ ሰልፈኞች የክልሉ አስተዳደር አካላት ተፈናቃዩ ወደቦታው እንዲመልሱ፥ የማይችሉ ከሆነ ደግሞ ከስልጣናቸው እንዲወርዱ ጠየቁ። ሰልፈኞቹ ለፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ እና ለህወሓት መሪ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ጥያቄአቸው በደብዳቤ አቅርበዋል።
ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ተለከታታይ ቀናት ያለማቋረጥ በመቐለ ሲደረግ የሰነበተው ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው እንዲመለሱ የሚጠይቅ ሰልፍ ዛሬ ንጋት ላይ ተገባዷል። ተፈናቃዮቹ ከሶስት ቀናት እና ለሊት የአደባባይ ቆይታቸው በዋነኝነት መንግስት ወደ ቀዬአቸው እንዲመልሳቸው የጠየቁ ሲሆን፥ አራት ዓመት በዘለቀ የመጠልያ ኑሮአቸው እየደረሰባቸው ያለ የከፋ ችግርም ዓለም ይወቀው ብለዋል። ማእከሉ መቐለ ሮማናት አደባባይ አድርጎ ሲካሄድ በሰነበተው የተቃውሞ ሰልፍ ከተፈናቃዮቹ በተጨማሪ የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች በስፋት የተሳተፉበት ሲሆን በይፋዊ የሰልፉ መዝግያ ደግሞ የክልሉ አስተዳደር ባለስልጣናት ተፈናቃዮቹ እንዲመልሱ፥ የማይችሉ ከሆነ ደግሞ ከስልጣናቸው ሊወርዱ ይገባል ተብሎ ተገልጿል።
ከሰልፉ አስተባባሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ዳንኤል ነጋሽ "የተፈናቃዮች ጉዳይ ከጠባብ የፖለቲካ አጀንዳ በላይ መሆኑ አምናችሁ፥ ሌላ የፖለቲካ ቁሩቁሳችሁ አቆይታችሁ በጋራ ጉዳይ ትኩረት አድርጋችሁ ወደ ቀዬአችን እንድትመልሱን ጥሪ እያቀረብን፥ ይህ ማድረግ የማትችሉ ከሆነ ትግራይ ከዚህ የሚበልጥ አጀንዳ ስለሌላት ሐላፊነታችሁ በአስቸኳይ ለሚችል አሳልፋችሁ እንድትሰጡ ጥሪ እናቀርባለን" ብለዋል።
ተፈናቃዮቹ በትላንትናው ዕለት ለትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት፣ ለህወሓት ሊቀመንበር እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የሰልፈኛው ጥያቄ በፅሑፍ ቀርቧል። የሰልፉ አስተባባሪ የሆነው ፅላል ሲቪል ማሕበረሰብ ትግራይ ትላንት ባሰራጨው መግለጫው ደግሞ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት የገባው ግዴታ እንዳያከብር የጠየቀ ሲሆን ተፈናቃዮች የመመለስ መንግስታዊ ሐላፊነቱም ይመልስ ብሏል።
ሙሉ ዘገባውን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
አዜብ ታደሰ
ፀሐይ ጫኔ