1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሐድያ ዞን በሠራተኝነት ላልተቀጠሩ ግለሰቦች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ደሞዝ ይከፍላሉ ተባለ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 15 2016

በሐድያ ዞን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላልተቀጠሩ ሠራተኞች ደሞዝ ይከፍላሉ ሲሉ ነዋሪዎች ወነጀሉ። ነዋሪዎች እንደሚሉት በዞኑ መሥሪያ ቤቶች ሥራ የማይሰሩ፣ የት እንደሚኖሩ የማይታወቅ ግለሰቦች ደሞዝ ይከፈላቸዋል። በዞኑ አንድ ወረዳ ብቻ 19 ሰዎች በሕገ-ወጥ መንገድ ደሞዝ ይከፈል እንደነበር ማረጋገጡን ፖሊስ አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/4aZ9C
ሖሳዕና ከተማ
የሐድያ ዞን ነዋሪዎች እንደሚሉት በዞኑ መሥሪያ ቤቶች ሥራ የማይሰሩ፣ የት እንደሚኖሩ የማይታወቅ ግለሰቦች ደሞዝ ይከፈላቸዋል። ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በሐድያ ዞን በሠራተኝነት ላልተቀጠሩ ግለሰቦች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ደሞዝ ይከፍላሉ ተባለ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን በህዝብና በመንግሥት የገንዘብ ሀብት ላይ የሚደረገው ምዝበራ እየተባባሰ መምጣቱን ነዋሪዎች ገለጹ ፡፡ ነዋሪዎቹ እንዳሉት በዞኑ ከባለሥልጣናት ጋር ትሥሥር አላቸው የተባሉ የመንግሥት ሠራተኞች ያልሆኑ ግለሰቦች ሥማቸውን በደሞዝ መክፈያ ሠነድ ውስጥ በማካተት  የመንግሥትን በጀት እየመዘበሩ ይገኛሉ ፡፡

በዞኑ በመንግሥት የገንዘብ ሀብት ላይ የሚታየው የምዝበራ አይነት ለነዋሪው የማይታመን ፤ ለሰሚውም ግራ የሚያጋባ ነው ሲሉ የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎቹ “በዞኑ የሚገኙ አብዛኞቹ የወረዳ መስተዳድሮች በበጀት  ችግር ምክንያት ለቀጠሯቸው ሠራተኞች ደሞዝ ለመክፈሉ መቸገራቸውን ሲገልፁ እንሰማለን ፡፡ ግን ደግሞ በሠራተኝነት ለማይታወቁ ግለሰቦች የደሞዝ ክፍያ ሲፈጽሙ ይስተዋላሉ ፡፡ ክፍያ የሚፈጸምላቸው ሠራተኞች ከሰው ሃብትና ከፋይናንስ ሃላፊዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት የላቸው ናቸው ፡፡ አብዛኞቹ ተከፋዮች አይደለም በመንግሥት ሠራተኝነት በአካባቢው ነዋሪነትም የማይታወቁ ናቸው ፡፡ በዚህ መልኩ የወረዳዎቹን ሀብት እየመዘበሩ ይገኛሉ “ ብለዋል፡፡

ዶቼ ቬለ ጉዳዩን ለማጣራት በሞከረባቸው አንዳንድ የሃድያ ዞን ወረዳዎች የመንግሥትን ገንዘብ ሲዘርፉና ሲያዘርፉ ተደርሶባቸዋል የተባሉ አካላት በቁጥጥር ሥር እየዋሉ እንደሚገኙ ለማረጋገጥ ችሏል፡፡ ከእነኝሁ ወረዳዎች አንዱ በሆነው በሻሸጎ ወረዳ ብቻ የመንግሥት ሠራተኝነታቸው ያልተረጋገጡ 19 ሰዎች ደሞዝ ሲወስዱ እንደተደረሰባቸው የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ዮሃንስ ሀይሌ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

የሃድያ ዞን መምህራን እና ሐኪሞች የደሞዝ ጥያቄ ከምን ደረሰ?


የግለሰቦቹን ሥም በወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት የሠራተኞች ደሞዝ መክፍያ ሰነድ ውስጥ በማስገባት ክፍያው እንዲፈጸምላቸው ወደ ባንክ መላኩን የጠቀሱት የወረዳው ፖሊስ አዛዥ “ ግለሰቦቹ ላለፉት ዘጠኝ ወራት በወር ከሦስት ሺህ እስከ ስድስት ሺህ ብር በክፍያ መልክ ሲወስዱ ነበር ፡፡በዚህ ጊዜ ውስጥ ከ730 ሺህ በላይ የመንግሥት ሀብት መመዝበራቸው ፖሊስ መረጃ አሰባስቧል”   ብለዋል ፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ፋሲካ ጌታቸው
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ፋሲካ ጌታቸው በሃድያ ዞን እተፈጸመ ነው በተባለው የገንዘብ ምዝበራ ዙሪያ መረጃ እንደደረሳቸውና ጉዳዩንም በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ዶቼ ቬለ በሥልክ ተናግረዋል። ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በአሁኑወቅት ከአሥራ ዘጠኙ ተጠርጣሪዎች እስከአሁን ሦስቱ በህግ ተይዘው በዞኑ ፖሊስ መምሪያ የተጠርጣሪዎች ማረፊያ ቤት ውስጥ እንደሚገኙ የተናገሩት የወረዳው ፖሊስ አዛዥ  የግለሰቦቹን ሥም በመክፍያ ሰነድ ውስጥ ፍርሞ ያስገባ አንድ የፋይናንስ ባለሙያም አንዲሁ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ገልጸዋል ፡፡ ፖሊስ ከአካባቢው የተሠወሩ ቀሪ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል። 

ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን የጅምላ እስር ቀጥሏል

በሃድያ ዞን እተፈጸመ ነው በተባለው የገንዘብ ምዝበራ ዙሪያ መረጃ እንደደረሳቸውና ጉዳዩንም በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ዶቼ ቬለ በሥልክ ያነጋገራቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ፋሲካ ጌታቸው ተናግረዋል ፡፡ መረጃው ለኮሚሽኑ ከሦስት ቀናት በፊት መድረሱን የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ “ ተጠረጣሪዎች በፖሊስ እንዲያዙ እየተደረገ ያለውን ሂደት በቅርብ በመከታተል ላይ እንገኛለን ፡፡ አለአግባብ ደሞዝ ሲከፍሉ የነበሩ የወረዳ መስተዳድር ተቋማትም በአስቸኳይ ክፍያውን እንዲያቋርጡ እያደረግን ነው ፡፡ ኮሚሽኑ በቀጣይ በያዘው የመቶ ቀናት የሥራ  ዕቅድ ውስጥ በሌሎች ወረዳዎች ተመሳሳይ ምዝበራዎች ካሉ ለማጥራት ቅድመ ዝግጅት አድርጓል  “ ብለዋል፡፡

እንደሻው ጣሰው
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሳው በክልሉ ያለው የሰው ሀብት ይዞታን መፈተሸ ወይንም ኦዲት ማድረግ እንደሚያሥፈልግ ሰሞኑን በሆሳዕና ከተማ በተካሄደው የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የሥራ ግምገማ ላይ ገልጸዋል። ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን በበርካታ ወረዳዎች በሠራተኞች ቅጥር ሥም ተመሳሳይ የገንዘብ መዝበራዎች አንደሚካሄዱ ይነገራል ፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሳው በክልሉ ያለው የሰው ሀብት ይዞታን መፈተሸ ወይንም ኦዲት ማድረግ እንደሚያሥፈልግ ሰሞኑን በሆሳዕና ከተማ በተካሄደው የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የሥራ ግምገማ ላይ ገልጸዋል። 

የቀጠለው የሃድያ ዞን መምህራን አቤቱታ

ክልሉ በሽግግር ላይ የሚገኝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የባለሙያ ክፍተቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ “ ያም ሆኖ በውስጣችን የሚገኘው የሠው ሀይል ይፈተሸ / ኦዲት / ይደረግ ብለን አቅጣጫ አስቀምጠናል ፡፡ አሁን ላይ የአመራሩም ሆነ የሠራተኛው መዋቅር እየተፈተሸ ይገኛል ፡፡ በቀጣይ  በፍተሻውን ውጤት  መሠረት ችግሮችን እየፈታን የምንሄድ ይሆናል “ ብለዋል። 

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሰ