1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሐረር የንጹህ የመጠጥ ዉሃ አቅርቦት ፈተና ሆኗል፤ ነዋሪዎች

ቅዳሜ፣ ሰኔ 15 2016

በሀረሪ ክልል በአንዳንድ አንባቢዎች የከተማው የንፁህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት ለወራት በመቋረጡ መቸገራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ። አንድ ባለ ሃያ ሊትር ጀሪካን ውሀ በአስር ብር ገዝተው እየተጠቀሙ መሆናቸውን የጠቀሱት ነዋሪዎች ችግሩ እንዲቀረፍ ጠይቀዋል።

https://p.dw.com/p/4hO0g
Äthiopien - Harar
ምስል Mesay Tejkelu/DW

የሀረር ከተማ የንጽህ መጠጥ ዉሃ አቅርቦቱ እየከፋ መሄዱን ነዋሪዎች ተናገሩ

በሀረሪ ክልል በአንዳንድ አንባቢዎች የከተማው የንፁህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት  ለወራት በመቋረጡ መቸገራቸውን ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ገልፀዋል። አንድ ባለ ሃያ ሊትር ጀሪካን ውሀ በአስር ብር ገዝተው እየተጠቀሙ መሆናቸውን የጠቀሱት ነዋሪዎች ችግሩ እንዲቀረፍ ጠይቀዋል። ከድሬደዋ አካባቢ ለሀረር በሚቀርበው የውሀ አቅርቦት ላይ በኤሌክትሪክ መቆራረጥ እና ተያያዥ ችግሮች ሳቢያ

ችግሩ መከሰቱን የጠቀሰው የክልሉ ውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን በተቻለ አቅም ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚሰራ አስታውቋል ።

በሀረር ከተማ የቀልአድአምባ ነዋሪዋ ወ/ሮ ማህሌት  በአካባቢያቸው የንፁህ መጠጥ ውሀ አቅርቦቱ ከተቋረጠ ከሶስት ወራት በላይ መሆኑን እና አንድ ባለ ሃያ ሊትር ጀሪካን ውሀ በአስር ብር እየቀዱ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ወ/ሮ አይናለም ካሳ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ስለ ችግሩ ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል።

የንፁህ የመጠጥ ዉኃ አቅርቦት ችግር በኢትዮጵያ

የክልሉ ውሀ እና ፍሳሽ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ ዲኒ ረመዳን ከድሬደዋ አካባቢ ለከተማዋ በሚቀርበው አገልግሎት ላይባጋጠመ የመብራት መቆራረጥ እና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ሳቢያ ችግሩ መከሰቱን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ለከተማዋ አማራጭ የውሀ አቅርቦት በሚቀርብበት ኤረር በክልሉ የተካሄደው የማስፋፊያ ስራ መጠናቀቁን የጠቀሱት አቶ ዲኒ የፕሮጀክቱ ስራ መጀመር ችግሩን በተወሰነ መልኩ ይቀርፋል ብለዋል።

የሀረር ጀጎል ግምብ
የክልሉ ውሀ እና ፍሳሽ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ ዲኒ ረመዳን ከድሬደዋ አካባቢ ለከተማዋ በሚቀርበው አገልግሎት ላይባጋጠመ የመብራት መቆራረጥ እና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ሳቢያ ችግሩ መከሰቱን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።ምስል Mesay Teklu/DW

የሀረር ውሀ አቅርቦት 

በሀረር ከተማ አንዳንድ አካባቢዎች ውሀ ከተቋረጠ ሶስት ወራት ማስቆጠሩን የሚገልፁት የከተማይቱ ነዋሪዎች ለውሀ ፍለጋ እንግልት እና ወጪ መዳረጋቸውን በመግለፅ መፍትሄ የሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የዉሃ አቅርቦት በአዲስ አበባ

ከድሬደዋ አካባቢ ተመርቶ ሰባ ሁለት ኪ.ሜ ያህል በተዘረጋ የውሀ ማስተላለፊያ መስመር  ለሀረር ከተማ በሚቀርበው የንፁህ መጠጥ ውሀ ላይ ያጋጠመው እክል አሁን ለተፈጠረው የውሀ መቋረጥ ምክንያት መሆኑን የክልሉ ውሀ እና ፍሳሽ አገልግሎት ባለስልጣን ገልጿል።

የባለስልጣኑ ስራ አስኪያጅ አቶ ዲኒ ረመዳን ለዶይቼ ቬለ በስልክ በሰጡት መረጃ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እንዲሁም ይሄንኑ ተከትሎ በውሀ መሳቢያ ፓምፖች ላይ ያጋጠመው ችግር ለወራት ሳይፈታ ለቆየው የውሀ አቅርቦት መቋረጥ መንስኤ መሆኑን አስረድተዋል። ችግሩን ለመፍታት ጥረት ቢደረግም በወቅቱ ግን መፍትሄ አለመሰጠቱ ተናግረዋል።

የንፁህ መጠጥ ዉኃ ችግር በከተሞች

ለከተማው አማራጭ ውሀ በሚቀርብበት ኤረር የውሀ ፕሮጀክት ላይ የተከናወነው የማስፋፊያ ስራ መጠናቀቀቁን የጠቀሱት አቶ ዲኒ ወደ ስራ ሲገባ ችግሩን በተወሰነ መልኩ ሊቀርፍ እንደሚችል ገልፀዋል።

በከተማይቱ የውሀ ፍላጎት እና አቅርቦት ዙርያ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ያስችላል የተባለ ጥናት መገባደዱን እና በቀጣይ ዓመት በክልሉ ይተገበራል ተብሎ እንደሚታሰብ ስራ አስኪያጁ በማብራሪያቸው ጠቅሰዋል።

መሳይ ተክሉ

ታምራት ዲንሳ