1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስአፍሪቃ

በ2024 በብዛት የተጫኑ መተግበሪያዎች የትኞቹ ናቸው? በ2025 የሚጠበቁትስ?

ፀሀይ ጫኔ
ረቡዕ፣ ጥር 7 2017

የመተግበሪያ አጠቃቀምን በተመለከተ በተለያዩ ድረ ገፆች የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በ2024 ዓ/ም ተጠቃሚዎች አውርደው የተጠቀሙባቸው መተግበሪያዎች የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ናቸው። በቻይናው ኩባንያ ባትዳንስ የተሰራው እና በአሜሪካ የመዘጋት አደጋ የተጋረጠበት ቲክቶክ /TikTok/ በ2024 በብዛት የተጫነ መተግበሪያ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/4p8r3
Symbolbild Social Media | TikTok
ምስል Dado Ruvic/REUTERS

በ2024 በብዛት የተጫኑ መተግበሪያዎች የትኞቹ ናቸው? በ2025 የሚጠበቁትስ?

ከሁለት ሳምንት በፊት በተሸኘው የጎርጎሪያኑ 2024 ዓ/ም ተጠቃሚዎች በብዛት አውርደው የተጠቀሟቸው መተግበሪያዎች እና በተያዘው 2025 ዓ/ም በብዛት ጥቅም ላይ ይውላሉ ተብለው  በሚጠበቁ  መተግበሪያዎች የትኞቹ ናቸው?
መተግበሪያዎች በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ከ4 ቢሊዮን በላይ የስማርት ስልክ ተጠቃሚዎች  የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን በማቃለል አስፈላጊ የህይወት አካል ሆነዋል።  በዓለም ላይ የአዳዲስ መተግበሪያዎች ፈጠራ እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል። ያም ሆኖ በተሸኘው የጎርጎሪያኑ 2024 ዓ/ም የታወቁት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ መተግበሪያዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በተጠቃሚ ቁጥር የበላይነት እንደያዙ  ቀጥለዋል።ያለፈውን የጎርጎሪያኑን 2024 ዓ/ም የመተግበሪያ አጠቃቀምን በተመለከተ  በተለያዩ ድረ ገፆች የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ፤ባለፈው ዓመት ተጠቃሚዎች አውርደው የተጠቀሙባቸው መተግበሪያዎች በአብዛኛው የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ናቸው

በ2024 በብዛት የተጫኑ መተግበሪያዎች

ከነዚህም መካከል በቻይናው ኩባንያ ባትዳንስ የተሰራው  እና በአሜሪካ የመዘጋት አደጋ የተጋረጠበት ቲክቶክ /TikTok/  በ2024 በብዛት የተጫነ መተግበሪያ ሆኗል።ኢንስታግራም/Instagram/እና ሌሎች በሜታ ኩባንያ ባለቤትነት የተያዙ እንደ ፌስቡክ/Facebook / እና ዋትስ አፕ/WhatsApp/ ያሉ ታዋቂ መተግበሪያዎችም ከቲክ ቶክ ቀጥለው  ከፍተኛ ዓለም አቀፋዊ ተደራሽነትን የያዙ መተግበሪያዎች ሆነዋል።

ባለፈው የጎርጎሪያኑ 2024 ዓ።ም የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተመራጭ መተግበሪያዎች ነበሩ።
ባለፈው የጎርጎሪያኑ 2024 ዓ።ም ተጠቃሚዎች አውርደው የተጠቀሙባቸው መተግበሪያዎች በአብዛኛው የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ናቸው።ምስል Jens Büttner/dpa/picture alliance

ሌላው በባይትዳንስ ኩባንያ ባለቤትነት የተያዘው ካፕ ከት /CapCut/ የሰኘው  የቪዲዮ አርትዖት መተግበሪያም ቀላል በሆነ መንገድ የተጠቃሚዎችን ይዘት በተንቀሳቃሽ ስልክ አርትኦት በመስራት በ2024 በአምስተኛ ደረጃ ተመራጭ መተግበሪያ ሆኖ ተመዝግቧል።የሶፍትዌር ባለሙያው እና አፍሮ ሪድ የተባለውን መተግበሪያ ካበለፀጉት ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ዳዊት ዓለሙ ለማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎቹ መተግበሪያ ተፈላጊነት መጨመር  ርካሽ የመልዕክት መለዋወጫ መሆናቸውን በምክንያትነት ይጠቅሳሉ።

«የእነኚህ የ«ሶሻል ሚዲያ» መተግበሪያዎች «ፖፕላሪቲ» የሚያሳየው የማኅበረሰቡን አኗኗር አንፀባራቂ ነው።እነኝህን ነገሮች የምንጠቀምባቸው ከቤተዘመድ ከጓደኛ ጋር በድንበር ሳንገታ ለመገናኘት ነው።ከአሁን በፊት ቴሌፎን ስንጠቀም በፅሁፍ መልዕክት ወይም በመደወል ነበረ።እነንህ ነገሮች ግን ያለውን ቴክኖሎጅ አይከተሉም ባይባሉ እንኳ፤ያላቸው የገቢ ምንጭየሰዎች ቴክስት መለዋወጥ እና መደዋወል ስለሆነ እናም ውድም ስለሆኑ ሰው ገንዘብ በማያስወጡ በነፃ ወይም በትንሽ ዳታ በሚያገለግሉ መተግበሪያዎች ግንኙነቱን ቀጥሏል።እና የፌስ ቡክ፣ የቴሌግራም፣ የዋትስ አፕ የመልዕክት መለዋወጫዎች በሙሉ ከመደበኛ ስልክ እና ከኢ ሲ ኤም ኤስ/ከፁሁፍ መልዕክት/ የተነጠቁ ናቸው።» በማለት ገልፀዋል። 

አቶ ዳዊት ዓለሙ ፤ስዊዘርላንድ የሚኖሩ የሶፍትዌር መሀንዲስ
አቶ ዳዊት ዓለሙ ፤ስዊዘርላንድ የሚኖሩ የሶፍትዌር መሀንዲስ እና የአፍሮሪድ መተግበሪያ ባለቤትምስል Privat

እነዚህ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችመተግበሪያዎችየፅሁፍ እና የድምፅ መልዕክት መላላኪያ ሆነው ከማገልገላቸው ባሻገር ለእርዳታ፣ ለግብይት እና ለገንዘብ ዝውውር ማገዛቸውም ሌላው ምክንያት ነው ይላሉ ባለሙያው። በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የጤና መረጃ የምትሰጠው እና የጤና ሰብ መተግበሪያ ባለቤትዶክተር ዝማሬ ታደሰ በበኩሏ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከመዝናኛ ባሻገር ጤናን የተመለከቱ መረጃዎች የሚገኝባቸው መሆናቸውም ለተፈላጊነታቸው ሌላው ምክንያት መሆኑን ትገልፃለች።

 መተግበሪያዎችን የመጠቀም ፍላጎት  እያደገ ነው  

መተግበሪያዎች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች  ከሚገኝ መረጃ እና የመዝናኛ ይዘት ጀምሮ እስከ ገንዘብ ዝውውር  እና ግብይት ድረስ  ጥቅም ላይ ይውላሉ። ከዚህ አንፃር በተሸኘው የጎርጎሪያኑ 2024 ዓ/ም የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ ገበያው  በፍጥነት ማደጉን ቀጥሏል።በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ በመጣው የዲጂታል መሳሪያዎች ፍጆታ እና በቢሮ ሳይወሰኑ በርቀት የመስራት  አዝማሚያ መጨመር ደግሞ፤ መተግበሪያዎችን የመጠቀም ፍላጎት  በፍጥነት እንዲያድግ አድርጓል።

በ2025 በሰፊው ጥቅም ላይ የሚውሉ መተግበሪያዎች   

በሌላ በኩል በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ምርት እና አገልግሎትን ከማስተዋወቅ ይልቅ እያንዳንዱ ኩባንያ የራሱን መተግበሪያ በማበልፀግ አገልጎሎትን በማስፋፋት የተሻለ ገቢ ማግኘት እና ደንበኞችን መያዝም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ  መጥቷል። ከዚህ የተነሳ፤  የገንዘብ ነክ ፣የጤና በተለይም የአእምሮ ጤና ፣የኢ-ኮሜርስ ፣ የርቀት ሥራ ፣ የትምህርት ፣ የግብይት  እና የቤት እንስሳት አጠባበቅ መተግበሪያዎች በተያዘው 2025 ዓ/ም በብዛት ጥቅም ላይ ይውላሉተብለው  በሚጠበቁ  መተግበሪያዎች ናቸው።ሲሉ ባለሙያዎች ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
አቶ ዳዊት እንደሚሉት በሁለት ምክንያቶች እነዚህ መተግበሪያዎች ተመራጭ ሊሆኑ ይችላሉ።አንደኛው የኩባንያዎችን ወጭ በመቀነስ ፤ ሌላኛው ደግሞ  ለተጠቃሚዎች አስተማማኝ አገልግሎት በማቅረብ።

ዶክተር ዝማሬ በበኩሏ  ጤና ሰብ የተሰኘውን መተግበሪያዋን እንደ ምሳሌ በማቅረብ በአቶ ዳዊት ሀሳብ ትስማማለች።

ዶክተር ዝማሬ ታደሰ፤ ጠቅላላ ሀኪም እና የጤና ሰብ መተግበሪያ ባለቤት
ዶክተር ዝማሬ ታደሰ፤ ጠቅላላ ሀኪም እና የጤና ሰብ መተግበሪያ ባለቤት ምስል privat

«እኔም እስማማለሁ።አሁን ለምሳሌ አሁን አብዛኞቻችን ኦን ላይን ባንክ ነው የምንጠቀመው ,የራሱ የሆነ መተግበሪያ አለው።በእርሱ ተጠቅመን ነው የምንሰራው።ትምህርርት፣ ፋይናንስ እያንዳንዱ የራሱን አገልግሎት የሚሰጥበት የተለዬ መንገድ ክፍያም ቢሆን ክፍያውን የሚያስከፍልበት የራሱን መስመር ይፈልጋል።እኔ አሁን ጤና ሰብ እንደ መተግበሪያ ለሴቶች ጤና አገልግሎት ብዬ ሳስብ ለሰው እንዲደርስ የምፈልግበት መንገድ አለ። ያንን ተግባራዊ ለማድረግ እና ሰዎችን ይበልጥ «ታርጌት»ያደርጋል።ብዬ በማስብበት መንገድ የተሰራ ነው።በተለይ የኢንተርኔት አቅርቦት እና የስማርት ስልክ ተጠቃሚነት እየጨመረ በመምጣቱ  ስለዚህ «ዲማንድ» ስላለ ፍላጎትን የማርካት ጉዳይ ይሆናል።»በማለት አብራርታለች።

ከዚህ ባሻገር በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ እየታዬ ካለው የዋጋ ግሽበት  ጋር ተያይዞ እንደ ቴሙ ያሉ ሸቀጦችን በርካሽ የሚያቀርቡ የግዥ መተግበሪያዎች ተፈላጊነቻው እየጨመረ መምጣቱን መታዘባቸውን የሶፍትዌር ባለሙያው አቶ ዳዊት ገልፀዋል።

የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያዎች የወደፊት ዕጣ

በአጠቃላይ በ2024 ተጠቃሚዎች በብዛት አውርደው የተጠቀሟቸው መተግበሪያዎች ዓለም አቀፍ ሸማቾች ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ነገሮች እና ባህሪያት የሚያንፀባርቁ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ያለው የመተግበሪያ ተደራሽነት ሲታይም፤ አፕል አፕ ስቶር 1.96 ሚሊዮን መተግበሪያዎችን፤ጎግል ፕሌይ ስቶር ደግሞ 2.87 ሚሊዮን መተግበሪያዎችን ለአንድሮይድ ተጠቃሚዎች አቅርቧል።ከዚህ  የተትረፈረፈ የመተግበሪያዎች አማራጭ ባሻገር የመተግበሪያ አበልፃጊዎች የተጠቃሚን ትኩረት ለመሳብ ግላዊነትን በማላበስ እና አጠቃቀምን እንከን የለሽ በማድረግ በየጊዜው አዳዲስ ፈጠራዎችን ያክሉበታል። 
ከዚህ አንፃር ዓለማችን ከጊዜ ወደ ጊዜ ዲጂታል እየሆነች በመምጣቷ፤ መተግበሪያዎች  የምንግባባበትን ፣የምንገበያይበትን፣ የምንሰራበትን  እና ህይወታችንን የምንመራበትን መንገድ መቀረጻቸውን የሚቀጥሉ ይሆናል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

 

ፀሐይ ጫኔ 
አዜብ ታደሰ