1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቀይ መስቀል በኢትዮጵያ የሰብዓዊነት ትምህርት ቤት መሠረተ

ሥዩም ጌቱ
ሰኞ፣ ጥር 19 2017

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የመሰረተው ትምህርት ቤቱ ዋና ዓላማው ትውልድን በሰብዓዊነት ማነጽ ነው ተብሏል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የተስፋፉ ግጭቶችን ተከትለው የታዩ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ለሰብዓዊ ትምህርት ቤት መቋቋም አቢይ ምክንያት ነው ተብሏለም፡፡

https://p.dw.com/p/4phEy
Logo Ethiopian Red Cross Society
ምስል Ethiopian Red Cross Society

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ዛሬ በይፋ ያቋቋመውና ስራ ያስጀመረው የሰብዓዊነት ትምህርት ቤት የሰላም፣ የግጭት-አልባ እና ሰብዓዊነት መርህዎች ላይ አተኩሮ ትምርት የሚሰጥ ነው ተብሏል፡፡ በዚህም ትምህርት ቤቱ ትውልድን በሰብዓዊነት አንጾ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተለመዱና ግን ደግሞ ጎልተው የታዩት ጭካኔ የተሞላባቸው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን ለመግታት የሚሰራ ነው ተብሎለታል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ፕሬዝዳንት አበራ ቶላ የሰብዓዊ ትምህርት ቤቱን አስፈላጊነት በተመለከተ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት፤ “ባለፉት ዓመታት ሰው ለሰው ያለው ክብር ለነፍስ ያለው ዋጋ እያነሰ መምጣቱ እንደ ኢትዮጵያውያንም ባህል ተቀባይነት የሌለው ስለሆነ ወገን በወገኑ ላይ ልጨክን የቻለበት ምክንያት ምንድነው የምለውን አጠይቀን መፍትሄው ዜጋን ስለሰብዓዊነት ማስተማር ነው ያልነው” በማለት የትምህርት ቤቱን መከፈት አስፈላጊነት አስረድተዋል፡፡

የትምህርት ቤቱ ትኩረት

ስነምግባር እና ሰብዓዊነት ላይ ያተኮሩ ኮርሶች ተቀርጾለት የተዘጋጀው በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ለተመረጡ ሰልጣኞች ትምህርት ልሰጥ የተዘጋጀው የሰብዓዊነት ትምህርት ቤት ለጊዜው በልዩ ዲፕሎም ትምህርት ለመስጠት ዝግጅቱን ብያጠናቅቅም በሂደት ግን በመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪም ትምህርት ለመስጠት ውጥን ስለመያዙ ተነግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበርና የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ስምምነት

“ለስልጠናው ትኩረት ያደረግናቸው በመጀመሪያ ለራሳቸው ሰልጥነው ከዚህ ስወጡ ደግሞ ማህበረሰቡን ለማሰልጠን የተዘጋጁትን ወጣቶች ነው” ሲሉም የማህበሩ ፕሬዝዳንት በአስተያየታቸው አስገልዝበዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ አሁን ላይ “በስፔሻል ዲፕሎማ” ትምህርቱን በመስጠት በሂደት ወደ ዲግሪና ከዚያም በላይ የማሳደግ እቅድ ስለመያዙም ተነግሯል፡፡

አዲስ አበባ ሳሪስ አከባቢ በሚገኘው የማህበሩ ማሰልጠኛ ማዕከል ትምህርቱን ለመስጠት መምህራንን ከማዘጋጀት ጀምሮ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁም የተነገረለት ሲሆን አሁን ላይ በመጀመሪያ ዙር ስልጠናው ትምህርት ቤቱ 50 ተማሪዎችን እንደሚቀበል ታውቋል፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ መቀዛቀዝ እና ዘመን ተሻጋሪ ህልመኞች

አሁን ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ በተንሰራፋው ግጭትና አለመረጋጋት ሰበብ ማህበረሰቡ ውስጥ የተዛመተው ኢ-ሰብዓዊ ደርጊቶችን ውስን ተማሪዎች ብቻ በማሰልጠን ተፈላጊውን አንገብጋቢ እልባት

ማምጣት ይቻል ይሆን በሚል የተጠየቁት የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ አበራ፤ “ችግሮቹ በአንዴ ቀረፋሉ የሚል ተስፋ አለመኖሩን” አስረድተው ውጥኑ ትውልዱን የሚመሩትን ማሰልጠን ነው ብለዋል፡፡

ከ1970ዎቹ ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ስድስት ሚሊየን አባላት እና 100 ሺህ በጎ ፈቃደኞች አሉት፡፡ ማህበሩ ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ባገረሸው ግጭት አለመረጋጋት ውስጥ የተጎዱትን ተደራሽ ለማድረግ በሚሰማራበት ወቅት በርካታ ሰራተኞቹ እና በጎ ፈቃደኞቹ ብሎም ንብረቶች ከተተቁባቸው ተቋማት ተጠቃሽም ነው፡፡

ሥዩም ጌቱ 
እሸቴ በቀለ
ጸሀይ ጫኔ