ሺ ቺንፒን አዲሱ የቻያና ኮምኒስት ፓርቲ መሪ
ሐሙስ፣ ጥቅምት 29 2005ባለፉት 5 አመታት የቻያና ኮምኒስት ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ያገለገሉት ሺ ቺንፒን ተሰናባቹን ሁ ጂንታውን በመተካት የፕሬዝዳንትነቱን ሥልጣን ተረክበዋል ።
ምንም እንኳን አዲሱ የቻይና ኮምኒስት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ሺ ለ 5 አመታት በምክትልነት ቢሰሩም የፖለቲካ አቅጣጫቸው ግን አሁንም ግልፅ እንዳልሆነ ነው የሚነገረው ። ለመሆኑ ሺ ቺንፒን ማናቸው ቀጣዩ የማቲያስ ቦሊንገር ዘገባ በማንንነታቸው ላይ ያተኩራል ።
በቻይናው ፕሬዝዳንት በሁ ጂንታው ሥር አዲሱ ትውልድ የዛሬ 10 አመት ሥልጣን ሲይዝ የ ሁ ማንነት የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጥያቄ ነበር ። ፓርቲያቸው ይፋ ካደረገው ግለ ህይወታቸው ውጭ የሁ ማንነት ያኔም ሆነ ከ10 አመት በኋላ አሁን እምብዛም አይታወቅም ። ዛሬም እንደዛሬ 10 አመቱ ስለተተኪያቸው ስለ አዲሱ የቻይና ኮምኒስት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ሺ ቺንፒን ተመሳሳይ ጥያቄ እየቀረበ ነው ። አሁን ግን ጥያቄውን የሚያቀርቡ ቻይናውያን መልስ ያገኛሉ ። የታዋቂዋ አቀንቃኝ ፔንግ ሊዩዋና ባለቤት ናቸው ። የሃገር ፍቅር በሚገለጣባቸው ዘፈኖቻቸው የሚታወቁት ፔንግ የሺ ሁለተኛ ባለቤት ናቸው ። ከትዳር ታሪካቸው ውጭ ሺ እምብዛም ጎልቶ የሚታወቅ ስብዕና የላቸውም ። ዊኪሊክስ
የተባለው ድረ ገፅ ከዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ባገኘው መረጃ ሺ ን ምኞተ ብዙ ፣ የልሂቅ ቤተሰብና የተግባር ሰው መሆናቸውን ይገልፃል ። ሺ በምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን ይበልጥ የሚታወቁት ግን ሜክሲኮን በጎበኙበት ወቅት ፣ ቻይናን ከመውቀስ በቀር ሌላ ሥራ የሌላቸው ሲሉ ምዕራባውያንን በተቹበት በዚህ አባባላቸው ነው ።
«የተሳለቹና ምንም የማይሰሩ የውጭ ዜጎች ጣታቸውን ቻይና ላይ ከመጠቆም በስተቀር ሌላ ሥራ የላቸውም ። አንደኛ እኛ አብዮት ወደ ውጭ አንልክም ፣ ሁለተኛ ረሃምብ ሆነ ድህነትን ወደ ውጭ አንልክም ፣ በሶሶተኛ ደረጃ በሌሎች ጉዳዮች ጣልቃ አንገባም ። እና ምንድነው የምትፈልጉት ? »
በዚህ አነጋጋሪ ትችታቸው የሚታወቁት ሺ እጎአ በ 1953 አም ነው የተወለዱት ። አባታቸው አብዮታዊ ጀግና ነው የሚባሉት ። ያደጉት በኮምኒስት ልሂቃን ስብስብ ውስጥ ነው ። ዘር ማንዘራቸው ሁሉ የፓርቲው ባለሥልጣናት የሆኑት ሺ በታዛቢዎች ዘንድ የፓርቲው ልዑል ነው የሚባሉት ። አባታቸው እጎአ በ1960 ዎቹ በቻይና ኮምኒስት ፓርቲ ውስጥ በተፈጠረ ችግር ለአመታት ወሂኒ ወርደው ነበር ። በሚሊዮኖች እንደ ሚቆጠሩ ወጣት ቻይናውያን በቻይናው የባህል አብዮት ወደ ገጠሪቱ ቻይና ተልከው ነበር ። በሻንሺ ክፍለ ሃገር ውስጥ በሚገኝ የገጠር መንደር አመታት አሳልፈዋል ።
ቤይጂንግ እንደተመለሱም ወደ ፖለቲካው አለም ዘልቀው ገቡ ። የኮምኒስት ፓርቲ አባል ሆኑ ። ያኔ አባታቸው ታስረው ነበር ። በቻይና ጦር ኃይል ሥራ የጀመሩት ሺ የመከላከያ ሚኒስትሩ ጌንግ ብያዮ ረዳት እስከመሆኑ ደረሱ ። ከዚያም የፓርቲው ፀሃፊ ሆኑ ። ለባህርዳርቻዎቹ የዝሄቺያንግ ና የፉጅያን ክፍላተ ሃገር አገረ ገዥነትም ተመረጡ ። መንግሥት ግዙፍ ሥራዎች በሚያከናውንበት በቻይና በነዚህ ጊዜያትም የግሉን ዘርፍ ፍላጎት በማዳመጥ ዝና አትርፈዋል ። በ2007 የፖሊት ቢሮ አባል በመሆን ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኑ ። ሺ በምእራባውያን ግልፅ ተደርገው ነው የሚወሰዱት ። ሴት ልጃቸው ሃርቫርቫርድ አሜሪካን ስሟ ተቀይሮ ትምህርቷን እየተከታተለች ነው ። በወጣትነታቸው አሜሪካንን ተዘዋውረው አይተዋል ። ምዕራቡ አለም በቻይና ንግድና የሰብአዊ መበት አያያዝ ላይ ለሚሰነዝረው ትችት እንግዳ አይደሉም ። በቅርቡ አሜሪካንን በጎበኙበት ወቅት ቻይና በሰብአዊ መብት አያያዝ ረገድ ብዙ ፈተናዎች እንዳሉባት የተናገሩት ብዙዎችን አስገርሟል ።
« ቻይና ብዙ ህዝብ አላት ። የየክፍለ ሃገሩ እድገት በእጅጉ የተለያየ ነው ። በዚህ ሁኔታ የሰብአዊ መብት ይዞታን ለማሻሻል ብዙ ፈተናዎች አሉ ። »
ማቲያስ ቦሊንገር
ሂሩት መለሰ
ተክሌ የኋላ