1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

አላሳድን ከሥልጣን ያባረረችው ሶርያ ዕጣ ፈንታ እና አሜሪካ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 1 2017

በሶርያ ጉዳይ አሜሪካንን የሚያስጨንቃት ለውጡን ተከትሎ የሚመሰረተው መንግሥት ምን ዓይነት ይሆን የሚለው እንደሆነ በዊድሮው ዊልሰን ማዕከል የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ባለሞያዋ ፕሮፌሰር ማሪና ኦታዌይ አመለከቱ።

https://p.dw.com/p/4nyOv
በሽር አልአሳድ
በኃይል ከሥልጣን የተባረሩት የቀድሞው የሶርያ ፕሬዝደንት በሽር አልአሳድ ፎቶ ከማኅደር ምስል picture alliance / AP Photo

የሶርያ ዕጣ ፈንታ እና አሜሪካ

በሃያት ታህሪር አልሻም እስላማዊ ቡድን መሪነት፣ የሶሪያውያን አማጽያን ሕብረት በጥቂት ቀናት ውስጥ ሶርያን በቁጥጥር ስር ማዋሉ እና አይነኩ፣ አይገረሰሱ የመሰላቸውን በሽር አላሳድን ለስደት መዳረጉ ለሁሉም ዱብ እዳ ሆኗል። በተለይ ውጥረት በሰፈነበት በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ጂዖ ፖለቲካዊ ሁነት ላይ ያለው አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ጫና ገና የሚሰላ፣ የሚታይ ይመስላል።

«እስካሁን አማጽያኑ ምን ዓይነት መንግሥት እንደሚመሰርቱ ስለማናውቅ፣ ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ ለማወቅ ይከብዳል» ያሉት ያነጋገርናቸው ፕሮፌሰር ማሪና ኦታዌይ፣ የዊድሮው ዊልሰን ማዕከል የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ባለሞያ ናቸው። ይሄው ለውጥ ለዓመታት የቆየውን፣ ለበርካቶች ሞት፣ እንግልትና፣ ሰብዓዊ ቀውስ ምክንያት የሆነውን የእርስ በርስ ጦርነት ምዕራፍ ማብቅያ ሆኗል። «በተለይ አሜሪካንን የሚያስጨንቃት ደግሞ አዲስ የሚጀምረው ምዕራፍ ወዴት አቅጣጫ ያመራ ይሆን?» የሚለው ነው ይላሉ ፕሮፌሰር ማሪና።

ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚገኘው ደግሞ በሶርያ ምድር የሚመሰረተው መንግሥት አወቃቀር ላይ እንደሆነ የተናገሩት ፕሮፌሰሯ፣ የበሽር አላሳድ መንግሥት መውደቅ ለሩሲያ ትልቅ ኪሳራ እንደሆነም ጠቁመዋል። ከዚህ ባለፈ አሁን ላይ የሶርያ ሕዝብ ከዳር እስከዳር የፈነጠዘለት ለውጥ፣ ነገን ተስፋን ይሰንቅ ፣ ጨለማን ያምጣ የምናውቀው በሂደት ነው ብለዋል።

ፕሮፌሰር ማሪና ኦታዌይ
በዊድሮው ዊልሰን ማዕከል የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ባለሞያዋ ፕሮፌሰር ማሪና ኦታዌይምስል Professor Marina Ottaway

አንዱና መሰረታዊው የአሜሪካና የምዕራቡ ዓለም ጥያቄ የአማጽያኑ ቡድን ጽንፈኛ ወይስ ለዘብተኛ የፖለቲካ ማዕቀፍንን ይዘረጋል የሚለው ነው። የታህሪር አል ሻም ቡድን መሪ አኑ ማህሙድ አል ጁላኒ ይሄንኑ ድል ተከትሎ ለዘብተኛ እና ሁሉን አቀፍ መልክቶችን ሲያሰማ ቆይቷል። ይሄም ቡድኑ የሚመራቸው የሕብረቱ አባላት ከተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ጎራዎች የተውጣጡ በመሆናቸው በሁሉም ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘትና ሁሉንም ለመወከል ያቀደ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት የሰጡት ፕሮፌሰሯ ነገ ሁኔታዎች መስመር ሲይዙ የሚሆነው አይታወቅም ባይ ናቸው።

ሊሰናበት ጥቂት ሳምንታት የቀሩት የጆ ባይደን አስተዳደር ይሄንኑ ግርግር ተጠቅሞ በምሥራቅ ሶርያ አካባቢ እራሱን እስላማዊ መንግሥት በሚለው በአይሲስ ላይ ያነጣጠረ መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት ፈጽሟል። ይሄው፤ እርምጃ በመውሰድና ጣልቃ በመግባት የሚታወቀው የጆ ባይደን አስተዳደር ሲያበቃ ግን ቀጣዩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዘወትር እንደሚሉት ጣልቃ ያለመግባት ፖሊሲን ተከትለው አሜሪካንን ከተጫዋችነት ወደ ተመልካችነት እንደሚቀይሯት ፕሮፌሰር ማሪና ገልጸዋል።

«ነገሮችን በጽሞና ማየትና ሁኔታወችን አጥንቶ መንቀሳቀስ የበሰለ ፖለቲካዊ እምጃ እንደሆነ» የሚስማሙት ፕሮፌሰር ማሪና ከአካባቢው ሃገራት ሁነቶችን ቁጭ ብላ የማታልፈው እስራኤል ናት ይላሉ።

ሶርያን ነጻ አውጥተው፣ የእርስ በርስ ግጭቱን የቋጩት ኃይሎች ሁለት ምርጫ አላቸው። አንደኛው የሁሉም ሃሳብና እምነት የሚንጸባረቅበት፣ የሁሉም ድምጽ የሚደመጥበት የጥምረት መንግሥት መመስረት ነው። ሁለተኛው ደግሞ እጅግ አክራሪና ጽንፈኛ እስላማዊ መንግሥት መመስረት። እናም በፕሮፌሰሯ እምነት አሁን ሶርያ ውስጥ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ሁለተኛውን አማራጭ የማምጣት እድሉ ጠባብ ነው።

አበበ ፈለቀ

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር