1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሶማሌ ክልል ጎርፍ ሰዎች ገደለ፣ ሺዎችን አፈናቃለም

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 27 2016

በክልሉ ከሚገኙ አስራ አንድ ዞኖች በስምንት የተከሰተው ችግር በተለያየ መጠን ጉዳት ማድረሱን የጠቀሱት አቶ በሽር አስቀድሞ ሲደረግ በቆየው ዝግጅት የነፍስ አድን ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

https://p.dw.com/p/4YWVO
በሶማሌ ክልል በደረሰዉ የጎርፍ አደጋ 24 ሰዎች ሞተዋል
ሶማሌ ክልል በጎርፍ ከተጥለቀለቁት ከተሞች አንዱምስል Somali region government communication bureo

የሶማሌ ክልልን ያጥለቀለቀዉ ጎርፍ

                         

በሶማሌ ክልል ባለፉት ተከታታይ ቀናት የጣለዉ ዝናብ ያስከተለዉ ጎርፍ በትንሽ ግምት 24 ሰዎች ገደለ፣ ሌሎች ከ40 ሺሕ በላይ ጎዳ፣ ሺዎችን አፈናቀለ።የክልሉ አደጋ ስጋት ቅነሳ ፅ/ቤት እንዳስታወቀዉ በተከታታይ የጣለዉ ዝንብ በክልሉ 8 ዞኖች የሚገኙ አካባቢዎችን አጥለቅልቋል።የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ በአደጋዉ የተጎዱትን አካባቢዎች ዛሬ ጎብኝተዋል።

ነዋሪዎች ወደ ቤታቸዉ መግባትና ከቤታቸዉ መዉጣት ተስኗቸዋል
በሶማሌ ክልል ጎርፍ ካጥለቀለቃቸዉ አካባቢዎች አንዱምስል Somali region government communication bureo

በቀጣዮቹ ቀናት በክልሉ መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖር የሚያመልክተው የሚቲዎሮሎጂ መረጃ ችግሩን እንዳያባብስ ተሰግቷል።በሶማሌ ክልል አደጋ መከላከል ቢሮ የቅድመ መከላከል ቡድን መሪ አቶ በሽር አረብ ለዶይቼ ቬለ በስልክ በሰጡት መረጃ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ሲጥል በቆየው ዝናብ ሳቢያ የተከሰተ ጎርፍ እና የወንዝ ሙላት ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሃያ አራት መድረሱን እንዲሁም ሃያ ሶስት ሺህ አባወራዎች መፈናቀልቸውን ገልፀዋል።

በክልሉ ከሚገኙ አስራ አንድ ዞኖች በስምንት የተከሰተው ችግር በተለያየ መጠን ጉዳት ማድረሱን የጠቀሱት አቶ በሽር አስቀድሞ ሲደረግ በቆየው ዝግጅት የነፍስ አድን ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል ።በብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ መረጃ መሰረት ቀጣዮቹ ቀናት በክልሉ ዝናብ የሚጠበቅበት መሆኑን አመላካች መሆኑ ስጋት የሚፈጥር መሆኑንም ቡድን መሪው ተናግረዋል።በአካባቢያቸው የተከሰተው ጎርፍ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ መግባቱን የገለፁት የጎዴ አካባቢ ነዋሪው አቶ ሻፊ በርካታ ቤቶች በውሀ መጥለቅለቃቸውን  ለዶይቼ ቬለ በስልክ ተናግረዋል።

የሶማሌ ክልልን ያጥለቀለቀዉ ጎርፉ ከ60 ሺሕ በላይ ሕዝብ ጎድቷል
ጎርፉ በተለይ አነስተኛ ቤቶችን ጠራርጎ ወስዷቸዋልምስል South Omo Zone Government

አቶ ሻፊ ጎርፉ በንብረት እና በመሰረተ ልማት ላይ ጉዳት ማስከተሉንም ጠቅሰዋል።ጉዳቱን ተከትሎ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ የተመራ የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ቡድን ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች እየጎበኘ መሆኑ ተገልፆል።

መሳይ ተክሉ 

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ