1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለ ሰላም ድርድሩ የፖለቲካ ተንታኝ አስተያየት

ሰኞ፣ ጥቅምት 21 2015

በጥብቅ ምስጢር እየተከናወነ መሆኑ የተነገረለት የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት እና የሕወሓት የፊት ለፊት የሰላም ንግግር እሁድ ይጠናቀቃል የሚል መርሃ ግብር ነበር የተያዘለት። ሆኖም ንግግሩ እስከ ከነገ ወዲያ ረቡዕ መራዘሙን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የመረጃ ምንጮች እየገለጹ ነው። ለመራዘሙ ምክንያቱ ምን እንደሆነ በግልጽ ያለው ነገር ባይኖርም።

https://p.dw.com/p/4ItuT
Äthiopien | Soldaten der äthiopischen Armee in Mekelle
ምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance

የፖለቲካ ተንታኝ አስተያየት


በኢትዮጵያ መንግሥት እና በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከል ደቡብ አፍሪካ ውስጥ እየተደረገ ያለው የሰላም ንግግር እስከ ቀጣዩ ረቡዕ  ሊቀጥል እንደሚችል የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ያመለክታሉ። ባለፈው ሳምንት ማግሰኛ ዕለት የተጀመረውና ትናንት ይጠናቀቃል በሚል መርሃ ግብር ወጥቶለት የነበረው የሰላም ንግግሩ በጥብቅ ምስጢር እየተከናወነ ነው። በአሕጉራዊው ድርጅት አፍሪካ ሕብረት እየተመራ ያለው የሰላም ድርድር በምን በምን ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዳደረገ እና እስካሁን የተገኘው የሂደቱ ውጤት ምን እንደሆነ በግልጽ አይታወቅም ፣ አወያዩ አካልም እስካሁን ያንን ከመግለጽ ተቆጥቧል። 

በፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል የቀጠለውና በተለይ ሰሜን ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ውድመት ያስከተለው ጦርነት ከተጀመረ የፊታችን ሃሙስ ሁለት ዓመታትን ይደፍናል። ይህን አስመልክተን አንድ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አነጋግረናል

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የትግራይ ክልል ዋና ዋና የሚባሉና ወታደራዊም ይሁን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳቸው የላቀ ቁልፍ የሚባሉ ከተሞችና አካባቢዎች በመከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር መግባታቸው እየተነገረ ነው። 

በአንድ በኩል ጦርነቱ ሲቀጥል ፣ በሌላ በኩል በብዙዎች ዘንድ የሰላምና የስምምነት በር ይከፍታል በሚል ተስፋ የተጣለበት የሰላም ውይይት ከባለፈው ማግሰኞ ጀምሮ ከደቡብ አፍሪቃ ሦስቱ ዋና ከተሞች አንዷ በሆነችውና የአስተዳደር ጉዳዮች ዋና ከተማ ፕሪቶሪያ ሲካሄድ ሰንብቷል። 

በጥብቅ ምስጢር እየተከናወነ መሆኑ የተነገረለት የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት እና የሕወሓት የፊት ለፊት የሰላም ንግግር ትናንት ይጠናቀቃል የሚል መርሃ ግብር ነበር የተያዘለት። ሆኖም ንግግሩ እስከ ከነገ ወዲያ ረቡዕ መራዘሙን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የመረጃ ምንጮች እየገለጹ ነው። ለመራዘሙ ምክንያቱ ምን እንደሆነ በግልጽ ያለው ነገር ባይኖርም። 

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ዶክተር ታደሰ አክሎግ የፌዴራል መንግሥት ከኢትዮጵያ ሉዓላዊነት አንፃር ፣ ሕወሓት ደግሞ በሦስት አማራጮች ምክንያት ሊነጋገሩ ቢችሉም የሕወሓት የመጀመሪያው ፍላጎቱ ሀገር መመሥረት ቢሆንም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የሚሆን አይመስልም። ሁለተኛው አማራጩ በፌዴራል ሥርዓቱ ሥር ሆኖ ትግራይን እየመራ መቀጠል ነው። ይህን ግን ፌዴራል መንግሥቱ ቢቀበለው እንኳን ለአፋርና ለአማራ ክልሎች አስቸጋሪ ስለሚሆን አወንታዊ ምላሽ አያገኝም ብለዋል።
«ጦርነቱ በአስቸኳይ ይቁም፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ይኑር» የሚሉት እና ኢትዮጵያ ውስጥ በጦርነቱ ተሳትፎ አለው የሚሉት «የጎረቤት ሀገር የኤርትራ ሠራዊት ከኢትዮጵያ ይውጣ» የሚሉት ጉዳዮች የሕወሓት አቋሞች ሲሆኑ ሕወሓት ዳግም ለኢትዮጵያ አንድነት እና ሉዓላዊነት ሥጋት በማይሆንበት ደረጃ ላይ እስከሚደርስ መከላከያ ማንኛውንም አስፈላጊ ያለውን እርምጃ እየወሰደ እንደሚቀጥልም መንግሥት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። 

ዶክተር ታደሰ በሁለቱ መካከል ስምምነት ቢኖር ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ትሆናለች በማለት ማሳያዎችን ጠቅሰዋል። በፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል የቀጠለውና በተለይ ሰሜን ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የሚባል ውድመት ያስከተለው ጦርነት ከተጀመረ የፊታችን ሐሙስ ሁለት ዓመታትን ይደፍናል ። ዶክተር ታደሰ አክሎግ እንደሚለት ሱዳንና ግብፅ ከግድብ ጋር በተገናኘ ፣ ምዕራባዊያን ከጦር መሳሪያ ሽያጭና ቀጣናዊ ፍላጎቶቻቸው መነሻ እንዲሁም የሕወሓት ባህሪ አንፃር ንግግሩ በሰላም እንዳይቋጭ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ።


ሰሎሞን ሙጬ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ሽዋዬ ለገሠ