1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ጉልህ ጭማሪ ተደረገ

ሰለሞን ሙጬ
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 30 2017

ማክሰኞ ታኅሣሥ 29 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ይፋ የሆነው የአዲስ አበባ የነዳጅ ምርቶች ግብይት አዲስ ጉልኅ የመሸጫ ዋጋ በተገልጋዮች ዘንድ ከወዲሁ ሥጋት አጭሯል ። የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው አዲሱ የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ አንድ ሊትር ቤንዚን ላይ የ10 ብር ጭማሪ ተደርጎ በ101.47 ብር እንዲሸጥ ተወስኗል ።

https://p.dw.com/p/4owlX
Äthiopien Addis Abeba | Gas
ምስል Solomon Muchie/DW

ሥጋት ያጫረው ጉልኅ የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ አዲስ ዋጋ

ማክሰኞ ታኅሣሥ 29 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ይፋ የሆነው የአዲስ አበባ የነዳጅ ምርቶች ግብይት አዲስ ጉልኅ የመሸጫ ዋጋ በተገልጋዮች ዘንድ ከወዲሁ ሥጋት አጭሯል ። የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው አዲሱ የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ አንድ ሊትር ቤንዚን ላይ የ10 ብር ጭማሪ ተደርጎ በ101.47 ብር እንዲሸጥ ተወስኗል ። እንዲያም ሆኖ ዛሬ የአዲስ አበባ ወኪላችን በተመለከታቸው ጥቂት የነዳጅ ማደያዎች ከዚህ በፊት እንደነበረው ሁሉ ረጃጅም ወረፋዎች ተስተውለዋል ። ሌላው ጉልኅ የዋጋ ጭማሪ የተደረገበት የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ ነው ።  በሊትር የ32 ብር ጭማሪ ተደርጎበታል ። ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ የክልል ከተሞች ከዚህ ቀደምም ቢሆን ሸማቹ  ነዳጅን ከዋጋው እጥፍ በሕገ ወጥ የግብይት ሰንሰለት ለመግዛት እንደሚገደድ ለማወቅ ተችሏል ። በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የምጣኔ ሐብት ባለሞያ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው በአጠቃላዩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል ሲሉ ገልፀዋል ። 

የዋጋ ጭማሪው በንጽጽር ሲታይ

ትናንት ምሽት ይፋ የተደረገው የአዲስ አበባ የነዳጅ ምርቶች ግብይት አዲስ የመሸጫ ዋጋ በሰፊው መነጋገሪያ ሆኗል፤ ሥጋትንም የፈጠረ ይመስላል። ከሦስት ወራት በፊት መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም ተደርጎ በነበረው የነዳጅ የመሸጫ ዋጋ ተመን አንድ ሊትር ቤንዚን በ 91.14 ይሸጥ የነበረ ሲሆን ከትናንት ጀምሮ የ 10 ብር ጭማሪ ተደርጎበት 101.47 ብር እንዲሸጥ ተወስኗል።

በነጭ ናፍጣ፣ በከባድ እና ቀላል ጥቁር ናፍጣ ላይም እስከ 9 ብር ድረስ ጭማሪ የተደረገ ሲሆን 77.76 ብር የነበረው የአውሮፕላን ነዳጅ ጉልኅ የሚባል የ31.8 ብር ጭማሪ ተደርጎበት በ 109.56 ብር በሊትር እንዲሸጥ ሆኗል።  የከተማ ውስጥ የሜትር ታክሲ አገልግሎት የሚሰጥ አንድ አሽከርካሪ ኹኔታው የሥራ መስክ የመቀየር ውሳኔ ላይ ሳያደርሰው አልቀረም።

የከተማ ውስጥ የሜትር ታክሲ አገልግሎት
የከተማ ውስጥ የሜትር ታክሲ አገልግሎትምስል Solomon Muchie/DW

የሜትር ታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች አስተያየት

"የነዳጅ ዋጋው በፍጹም የሚገናኝ አይደለም። እና የታሪፉ ጉዳይ የሚገናኝ ነገር አይደለም። እኔ ዝም ብየ ሳስበው አሁን ላይ ልወጣ እያሰብኩ ነው፤ ወደሌላ ሥራ።" ብሏል። ሌላኛው ተመሳሳይ ሥራ ላይ የተሰማራ ሰው ደግም እርምጃው አላቂ ምርቶች ላይ ዋጋ እንዳይጨምር አሥግቶታል። "በዚህ ጭማሪ ላይ ደግሞ አላቂ ፍጆታዎች ለምሳሌ ምግብ ላይ ከፍተኛ ችግር ያመጣል ብየ አስባለሁ" ።

የሕብረተሰቡ የመክፈል አቅም መቀነሱን የሚገልፀው ይህ የሜትር ታክሲ አሽከርካሪ አሁን የበለጠ መቸገሩ እንደማይቀር ከልምዱ በመነሳት ገልጿል።

«ኅብረተሰቡ የሚቸገር ይመስለኛል እኛ ብቻ ሳንሆን»

አዲስ አበባ ውስጥ የሜትር ታክሲ ከሚሰጡ ኩባንያዎች ወደ አንደኛው ደውለን ነበር። የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው በነበረው ዋጋ ለመሥራት እንደከበዳቸው የሚገልፁ አሽከርካሪዎች መኖራቸውን በመግለጽ ጭማሪ አድርገው እንደሆን ጠይቀናል። በአሁኑ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ምክንያት ዛሬ ዋጋ እንዳልጨመሩ ገልፀውልኛል። ለረጅም ጊዜ አሽከርካሪ ሆነው እየሠሩ ያሉት አንድ ግለሰብ የዋጋው ጭማሪ የተጋነነ በመሆኑ መንግሥት ቢያስተካክለው ይበጃል ይላሉ። "የተደረገው የነዳጅ ጭማሪ ታስቦበት ቢሆን እላለሁ። እና ቢስተከከል አሁንም ጊዜው አልረፈደም።" ብለዋል።

ነዳጅ ለመቅዳት የተሰለፉ ተሽከርካሪዎች
ነዳጅ ለመቅዳት የተሰለፉ ተሽከርካሪዎች። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Solomon Muchie/DW

የምጣኔ ሐብት ባለሞያ አስተያየት

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነዳጅ በየወሩ እየተከለሰ በሥራ ላይ እንዲውል ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት የዋጋ ጭማሪ ማድረጉን ገልጿል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሐብት መምህር የሆኑት ዶክተር አጥላው ዓለሙ የዋጋ ጭማሪው ጉልህ ልዩነት ያለው በመሆኑ በአጠቃላዩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል ብለዋል።

«የትራንስፖርት ኦፕሬተሮች ይጨምራሉ [ዋጋ]። ሌሎችም ይጨምራሉ። ቲማቲም የሚያመጣው የትራንስፖርት ጨምሮብኛል ብሎ ይጨምራል። እህል የሚያመጣውም ይጨምራል። ኑሮ ስለተወደደ ብሎ የቤት አከራይም ሊጨምር ይችላል።»

ሰሞኑን የተደበቁ የተባሉ ነዳጅ ጫኝ ቦቴዎች አፋር ውስጥ ተገኙ ተብሎ ነበር።  በዚሁ ሰሞን አዲስ አበባ ውስጥ የነበረው ረጃጅም የነዳጅ ወረፋ ዛሬም ተስተውሏል።

በየ ክፍለ ሀገሩ የነዳጅ ሽያጭ በጥቁር ገበያ ከመደበኛ መሸጫው ዋጋ እጥፍ ጨምሮ እንደሚሸጥ በአራቱም አቅጣጫ ያነጋገርናቸው ሰዎች አረጋግጠውልናል።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ