1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሥነ-ጽሑፎቻችን በዉጭ ቋንቋዎች ምን ያሕል ተተርጉመዋል?

ሐሙስ፣ ጥር 23 2011

በአፍሪቃዉያን የተጻፉ መጻሕፍት መሸጫ መደብር ጀርመን መዲና በበርሊን በርካታ አንባብያንን የጋዜጠኞችን እና የሚዲያዉን ዓለም ቀልብ ስቦ ነዉ የሰነበተዉ። ከኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፎች ምን ያህሉ በዉጭ ቋንቋ ተተርጉሟል?

https://p.dw.com/p/3CXDs
Buchhandlung für afrikanische Literatur in Berlin | Karla Kutzner & Stefanie Hirsbrunner
ምስል DW/D. Pelz

ሀገርን ባህልን ለሌሎች ማስተዋወቅ ሥነ ጽሁፍን በሌሎች ቋንቋዎች መተርጎም ጠቃሚ ነው።

«ያሉት ፀሐፍያን ሥራቸዉ ወደሌላ ቋንቋዎች ተርጉመዉ ለአንባብያን እንዲደርስ ሳይሆን ትኩረታቸዉ ሃሳባቸዉን በቋንቋቸዉ ማድረስና ያንኑ ለአንባቢ ማቅረብ ነዉ፤ ትልቁ የመጀመርያ ጥረታቸዉ»    

አፍሪቃዉያን ደራስያን የሥነ-ጽሑፍ ባለሞያዎች፤ ሥራዎቻቸዉን ለዓለም ለማስተዋወቅ ምን ያህል ጥረት ያደርጋሉ፤ በሚል ኢትዮጵያዊዉ ደራሲ አስራት ከበደ የሰጡን አስተያየት ነበር። በአፍሪቃዉያን የተጻፉ መጻሕፍት መሸጫ መደብር ጀርመን መዲና በበርሊን በርካታ አንባብያንን የጋዜጠኞችን እና የሚዲያዉን ዓለም ቀልብ ስቦ ነዉ የሰነበተዉ። የአፍሪቃዉያኑ ሥነ-ፅሑፍ መሸጫ መደብሩ ሲገባ በጉልህ ቦታ ከተቀመጡት መጽሐፍቶች መካከል የአፍሪቃዊዉ የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ በአፓርታይድ ዘመን ከእስር ቤት የጻፉዋቸዉ ደብዳቤዎችን የያዘዉ ጥራዝ ፤ በዴሞክራቲክ ኮንጎ ታዋቂ የሆኑት የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ እና የሕክምና ዶክተር እንዲሁም በሰላም ኖቢል ተሸላሚ ዴኒስ ማኩቬጌ የሕይወት ታሪክ ተጠቃሽ ናቸዉ።  የኢትዮጵያን ደራስያን ጽሑፋቸዉን ለሌላዉ ዓለም ለማስተዋወቅ ምን ያህል ጥረት ይደረጋል ስልንል እንጠይቃለን።

Olumide Popoola
ምስል Karla Kutzner

ከአንድ ወር ገደማ በፊት በጎርጎረሳዉያኑ 2018 መጠናቀቅያ ላይ በጀርመን መዲና በርሊን ላይ ፍሪድርሽ ሻይን በተባለ አካባቢ የአፍሪቃዉያንን ሥነ-ጽሑፍ የሚያስተዋዉቀዉን በመጽሐፍ መደብር የከፈተችዉ ሽቴፋኒ ሂርቡሸር እንደሌላዉ የዓለም ክፍል ሁሉ የአፍሪቃዉያን ሥነ-ጽሑፍም በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ ስትል ትናገራለች።    

« የአፍሪቃዊያን ሥነ-ጽሑፍ በዓለም የሥነ-ጽሑፍ መድረክ ተቀባይነት እንዲያገኝ እና እንዲተዋወቅ እንፈልጋለን፤ እንመኛለን። የአፍሪቃ ደራስያን በዓለም ዙርያ ባሉ ሃገራት ሁሉ ተቀባይነት እንዲኖራቸዉ እና ታዋቂ እንዲሆኑ እንፈልጋለን። የሚጽፉአቸዉ እና አብረን የምንጋራዉን ታሪክ ብሎም የማናዉቀዉን ታሪክ ሁሉ እንድናዉቅ ያስፈልጋል፤ ልዉዉጥ ማድረግ ያስፈልጋል ምኞታችንም ነዉ። »

በርሊን መዲና እምብርት ላይ የተከፈተዉ የአፍሪቃን ሥነ-ጽሑፍ የሚያስተዋዉቀዉ የመጽሐፍ መደብር በአፍሪቃዉያን  ብቻ ሳይሆን አፍሪቃዊ ዝርያ ባላቸዉ የተጻፉ መጽሐፍትን ያካተተ ወደ 1000 ሺህ የሚሆኑ ደራስያን የጻፉዋቸዉ ሥነ-ጽሑፎች ለገበያ የቀረበበት ነዉ።  ለምሳሌ የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ባለቤት ሚሼል ኦባማ ትዉስታቸዉን ያሳፈሩበት መጽሐፋቸዉ ተጠቃሽ ነዉ። በሌላ በኩል በመጽሐፍ መደብሩ  ዘረኝነትን ተዋሕዶ መኖርን እንዲሁም በሴትነት የሚደርስ ጭቆና ላይ የሚያዉጠነጥኑ መጻሕፍት ጽሑፎች ይገኛሉ። የምሽት እንግዳ እንዲሁም የጨረቃ ጥላ በሚል ልቦድ መጽሐፋቸዉ የሚታወቁትና በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚጽፉት ደራሲ አስራት ከበደ እንደሚሉት ሃገርን ባህልን ለሌሎች ለማስተዋወቅ ሥነ-ጽሑፍን  በሌሎች ቋንቋዎች መተርጎሙ ጠቃሚ ነዉ እንድያም ሆኖ የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ጥንታዊ ነቱ የታወቀ ነዉ።  

Buchcover Book Cover von  Author Haddis Alemayehu
ምስል Privat

በኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ የዳበሩባቸዉ ዘመናት እናዳሉ የሚናገሩት ደራሲ አስራት ከበደ ከአክሱም ዘመነ መንግሥት በኋላ በዮዲት ዘመን በርካታ የኢትዮጵያ የሥነጽሑፍ ኃብቶች የወደሙበትም እንደሆን ሳይናገሩ አላለፉም። በኢትዮጵያ ወርቃማ የሥነ ጽሑፍ ዘመንም አላት ብለዋል ደራሲ አስራት ።

ኢትዮጵያ የዳበረ የቅኔ ባህል እና ልምድ ያላት ሃገርም እንደመሆንዋ በቅኔ ዉስጥ ሥነ-ጥበባዊ መንገድ እየተገለጸ እየተሰራበት በትምህርት መልክ ከትዉልድ ትዉልድ እያለፈ እዚህ መድረሱን እና በዓለም ደረጃ የዳበረ የሥነ ጽሑፍ ሃብት አላቸዉ ከሚባሉት ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የምትቀመጥ ናት ሲሉ ደራሲ አስራት ከበደ ተናግረዋል። እንድያም የኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ሃብት ጥንታዊ እንደመሆኑ የሚጠበቀዉን ያህል ዳብሮአል ወይ ለሚለዉ መልስ ማግኘት አጠያያቄነሩን ደራሲዉ ተናግረዋል።

Äthipien - Bücher für Afrika - Dr. Abebe Kebede
ምስል privat/Abebe Kebede

ስለ ሥነ ጽሑፍ ማደግ መዳበር አልያም መቀጨጭ ሌላዉ ምክንያት የሚሆነዉ የሕትመት ጉዳይ ነዉ። መጽሐፍን ወይም አንድ ጽሑፍን ለማሳተም የሚገጥመዉ ችግር እና ሂደትን ደራሲ አስራት ከበደ ገልፀዋል። ስለዚህም ይላሉ ደራሲዉ በኢትዮጵያ ጻሕፍት መጻሕፍቶቻቸዉን ሥራዎቻቸዉን ለራሳቸዉ አንባቢ ለማቅረብ ፈተናዎችን ለማለፍ ያልፋሉ እንጂ አልፈዉ ተርፈዉ በሌላ ቋንቋ ለማሳተም ብዙም የሚያመቻች ሁኔታን አያገኙም።

ሙሉ ቅንብርሩን የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ