1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሠሚ ያጣው የዛይሴዎች አቤቱታ

ረቡዕ፣ ሰኔ 19 2016

በዛይሴ ማህበረሰብ አባላት ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ የዘፈቀደ እሥርና ወከባ ይፈጸማል ሲሉ ነዋሪዎችና የምክር ቤት አባላት ገለፁ፡፡ የዞኑና የወረዳው የፀጥታ አባላት ሰሞኑን በሌሊት ቤት ለቤት በመዘዋወር ወጣቶች ፣ ሴቶች እና ቄሳውስቶችን ጨምሮ 112 የማህበረሰቡ አባላትን ይዘው ማሠራቸውን ነዋሪዎቹና እንደራሴዎቹ ለዶቼ ቬለተናግረዋል ፡፡

https://p.dw.com/p/4hWqt
የአርባምንጭ ከተማ ማዕከል
የአርባምንጭ ከተማ ማዕከል ምስል DW

ሠሚ ያጣው የዛይሴዎች አቤቱታ

ሠሚ ያጣው የዛይሴዎች አቤቱታ  


በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ በሚገኙ የዛይሴ ማህበረሰብ አባላት ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ የዘፈቀደ እሥርና ወከባ እየተፈጸመ ይገኛል ሲሉ ነዋሪዎችና የህዝብ እንደራሴ ምክር ቤት አባላት ገለፁ ፡፡  የዞኑና የወረዳው የፀጥታ አባላት ሰሞኑን በሌሊት ቤት ለቤት በመዘዋወር ወጣቶች ፣ ሴቶች እና ቄሳውስቶችን ጨምሮ 112 የማህበረሰቡ አባላትን ይዘው ማሠራቸውን ነው ነዋሪዎቹና የእንደራሴ ምክር ቤቱ አባላቱ ለዶቼ ቬለ የተናገሩት  ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት የዘፈቀደ እሥርና ወከባው እየተፈጸመ የሚገኘው በወረዳው ዛይሴ ደንብሌ ፣ ዛይሴ ኤልጎ እና ዛይሴ ወዘቃ በተባሉ የገጠር ቀበሌያት ውስጥ ነው ፡፡ 

የአቶ ጥሩነህ ስደት

በጋሞ ዞን አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ የዛይሴ ደንብሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶአደር ጥሩነህ አዲስ በሥጋት መንደራቸውን ከለቀቁ ከሁለት ሳምንታት በላይ ማስቆጠራቸውን ይናገራሉ ፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የጋሞ ዞን እና የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ የፀጥታ አባላት ቤት ለቤት በሚያደርጉት አሰሳ የተነሳ መሆኑን የጠቀሱት ጥሩነህ “ አሁን ወደ ሌላ ሥፍራ ተሰድጄ ነው ያለሁት ፡፡ ያም ሆኖ አጎቴ ፣ የአጎቴ ሚስት እና ልጄን ጨምሮ አብዛኞቹ የቤተሰብ አባሎቼ  ታስረው ተወስደውብኛል “ ብለዋል ፡፡በግጭት ሥጋት ውስጥ የሚገኙት የአርባ ምንጭ ዙሪያ ቀበሌያት
አቶ አብረሃም ኦላሼ በጋሞ ዞን የዛይሴ የምርጫ ክልልን በመወከል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴ መሆናቸውን ይናገራሉ ፡፡ አቶ አብረሃም በአካባቢው እሥርና ወከባው እየበረታ የመጣው ከሁለት ሳምንታት በፊት የማህበረሰቡን የአዲስ ዓመት በዓል ለማክበር የተሰባሰቡ ወጣቶች ከፀጥታ አባላት ጋር ተጋጭተው አምስት ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው ይላሉ ፡፡ የፀጥታ አባላቱ እስከ ትናንት ድረስ  ቤት ለቤት በመዘዋወር ፈጸሙት ባሉት እሥር ወጣቶች ፣ ሴቶች እና ቄሳውስቶችን ጨምሮ 112 ሰዎች ተይዘው መወሰዳቸውን ገልጸዋል ፡፡

የአርባምንጭ ከተማ
የአርባምንጭ ከተማ ምስል Arbaminch culture and Tourism office

የእሥሩ ዳራ

የዛይሴ ደንብሌ ነዋሪው ጥሩነህ እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴው አቶ አብረሃም ለእሥርና ወከባው የአዲስ ዓመት በዓል ለማክበር የተሰባሰቡ ወጣቶች መነሻ ቢደረጉም ዋናው ምክንያት ግን ሌላ ነው ይላሉ ፡፡ የዘይሴ ህዝብ ከቅርብ ጊዜ ዓመታት ወዲህ እያነሳ የሚገኘው የራስ አስተዳደር ጥያቄ መኖሩን የጠቀሱት ጥሩነህ እና አብረሃም “ ይህ በልዩ ወረዳ የመደራጀት ጥያቄ በጋሞ ዞን እና በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ፖለቲከኞች ዘንድ አልተወደደም ፡፡ የእሥርና ወከባው ዓላማም በማህበረሰቡ ዘንድ ፍርሃትን በመፍጠር የመደራጀት ጥያቄው እንዳይነሳ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ የሚገኝ ነው “ ብለዋል ፡፡አሳሳቢው የሰብአዊ መብት ጥሰት በጋሞ ዞን

የዋና አስተዳዳሪው ቅድመ ሁኔታ 

ነዋሪዎቹ ባነሱት ቅሬታ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ በዶቼ ቬለ የተጠየቁት የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቃፌ ቃፊሬ “ እከሌ እንደዚህ ታሠረ እከሌ እንደዚህ ሆነ ብዬ የምሰጠው ምላሽ  የለም “ ብለዋል ፡፡ ምላሽ መስጠት ያልፈለጉበትን ምክንያት አሁንም በዶቼ ቬለ የተጠየቁት ዋና አስተዳዳሪው “ ለእኛ ያልቀረበ ጥያቄ እናንተ [ ዶቼ ቬለ ] ጋር ሲመጣ መቀበል አልነበረባችሁም ፡፡ አሁን እኔ መረጃውን የምሰጠው ቅሬታ አቅራቢዎቹ መጀመሪያ እኔ ጋር ቀርበው ካመለከቱ በኋላ ነው “ በሚል ቅድመ ሁኔታ የሚመስል ምላሽ ሰጥተዋል ፡፡
ዶቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምላሽ ለማግኘት ለጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባይነህ አበራ ቢደውልም ስብሰባ ላይ በመሆናቸው ማናገር እንደማይችሉ ገልጸዋል ፡፡ ዋና አስተዳዳሪው በእጅ ሥልካቸው አጭር የጹሁፍ መልዕክት ቢላክላቸውም መልስ ሳይሰጡ ቀርተዋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ