1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምክር ቤቱ የድጋፍ እና ብድር ስምምነቱን ማጽደቁ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 24 2016

ሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ከዓለም አቀፉ የልማት ማሕበር የተገኘን የ1.5 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍና ብድር ስምምነት አዋጅ አፀደቀ። የገንዘብ ድጋፉ ለሥራ ፈጠራ፣ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ፣ የመዋቅር ማስተካከያ ለማድረግ እንዲሁም የፌደራል መንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትን በቀጥታ ለመደገፍ የሚውል ነው ተብሏል።

https://p.dw.com/p/4iyEs
ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲስ አበባ
ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲስ አበባ ፎቶ ከማኅደርምስል Solomon Muche/DW

ምክር ቤቱ የድጋፍ እና ብድር ስምምነቱን ማጽደቁ

ሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ከዓለም አቀፉ የልማት ማሕበር የተገኘን የ1.5 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍና ብድር ስምምነት አዋጅ አፀደቀ። የገንዘብ ድጋፉ ለሥራ ፈጠራ፣ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ፣ የመዋቅር ማስተካከያ ለማድረግ እንዲሁም የፌደራል መንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትን በቀጥታ ለመደገፍ የሚውል ነው ተብሏል። የቀረበው አዋጅ በአንድ ተቃውሞ እና በአንድ ድምፅ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።

የኢኮኖሚ ማሻሻያው ላይ የተነሱ ጥያቄዎች

የዚህን አዋጅ አስፈላጊነት በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ካብራሩ በኋላ ከውስን የምክር ቤት አባላት ልዩ ልዩ ጥያቄዎች ቀርበዋል።

መንግሥትበቅርቡ ተግባራዊ ካደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ ሕገ ወጥ ንግድን ለመከላከል ምን የተለየ አቅጣጫ ይከተላል? ዝቅተኛ እና ቋሚ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ከሚፈጠረው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ለመታደግ መንግሥት ምን እቅድ ይዟል? የውጭ ምንዛሪ ሥርዓቱ የጥቁር ወይም የትይዩ ገበያ መናር እየታየበት መሆኑ ተጠቅሶ እንዴት ለመግታት ታስቧል? የውጭ ሃገራት ገንዘቦች የበለጠ ከሀገር እንዳይሸሹ ሥጋት መኖሩ፣ በእርዳታ እና ብድር ብቻ ሀገሪቱ የገጠማትን የውጭ ምንዛሪ ጉድለት እንዴት መሸፈን ይቻላል? የሚሉ ጥያቄዎች ቀርበዋል። በተጨማሪም የፀጥታ ችግር ባልባት ሀገር ውስጥ ሕዝብ በነፃነት ከቦታ ቦታ እንቅስቃሴ ማድረግ በተቸገረበት በዚህ ወቅት የውጭ ኢንቨስትመንትን ታሳቢ አድርጓል የተባለው ማሻሻያን እንዴት ማሳካት ይቻላል? ግብር የመክፈል አቅምም ቢሆን በተዳከመበት በዚህ ጊዜ ይህንን መሰል የማሻሻያ እርምጃ መውሰዱ ለምን አስፈለገ? በሚል ተጨማሪ ጥያቄዎችም ተሰንዝረዋል። ከምክር ቤት አባላት መንግሥት የወሰደውን እርምጃ በበጎ የተመለከቱትም የድጋፍ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ምላሽ

የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ለቀረቡ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ዛሬ ለምክር ቤቱ እንዲፀድቅ የቀረበው ገንዘብ የዓለም ባንክ ትናንት ያፀደቀው ነው ብለዋል። ይህ ሀብት የሀገሪቱን የዕዳ ጫና ከሚገኝበት ከፍተኛ ደረጃ ወደ መካከለኛ የሚያወርድ መሆኑን፣ ምክር ቤቱ ካፀደቀው በኋላ በሰዓታት ውስጥ የገንዘብ ሚኒስቴር የሀብት ቋት ውስጥ የሚገባ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይሁንና ይህ ገንዘብ መንግሥት ያያዘው የ 2017 በጀት አካል ሆኖ በታሳቢነት የተያዘ በመሆኑ እንደገና ምክር ቤቱ የበጀቱ አካል አድርጎ እንዲያውጀው ለመጽደቅ እንደሚቀርብም ገልፀዋል።

የተደረገውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ ለወራት፣ ምናልባትም ለዓመት ያህል ጊዜ የኑሮ ውድነት መኖሩ እንደማይቀር ያስታወቁት ሚኒስትሩ፣ ያም ሆኖ ግን ወደፊት ችግሩ አብሮ እንደማይዘልቅ እና ገንዘቡንም መንግሥት በከፍተኛ ጥንቃቄ ጥቅም ላይ እንደሚያውለው ተናግረዋል።

የዓለም የገንዘብ ድርጅት IMF መለያ
የዓለም የገንዘብ ድርጅት IMF መለያፎቶ ከማኅደር ምስል Yuri Gripas/REUTERS

በሀገሪቱ ዕድገት «ከፍተኛ ተጠቃሚነት የሚያመጣ ነው" ያሉት ይህ የማሻሻያ እርምጃ በከፍተኛ ጥንቃቄ የተዘጋጀ፣ ከፍተኛ ድርድር የተደረገበት፣ በኅብረተሰቡ ላይ የሚደርስን የአጭር ጊዜ ጫና ለመቀነስ ታስቦበት የተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል። ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ካገኘችው የገንዘብ ብድር ስምምነት በተጨማሪ ከቻይና እና ከሌሎች ተቋማት ጭምር የዕዳ እፎይታ እና ሽግሽግም ያገኘች መሆኑን ጠቅሰዋል።

የዛሬ የውጭገራት የምንዛሪ ተመን 

መንግሥት ሰኞ ዕለት ይፋ ያደረገውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድባንክ አንድ የአሜሪካ ዶላርን በዛሬው ዕለት በ80 ብር፣ አንድ ዩሮን በ86 ብር እንዲሁም አንድ ፓውንድ ስተርሊንግን በ97 ብር እየመነዘረ መሆኑን አስታውቋል። ሀገሪቱ ያፈራቻቸው ዋና ዋና ጉምቱ የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ባለሙያዎች፣ ይህ የማሻሻያ እርምጃ ያመጣው የውጭ ሃገራት ገንዘቦች ገበያ መር የምንዛሪ ሥርዓት ከፍተኛ ቀውስ ሊያስከትል የሚችል መሆኑን ደጋግመው እየገለፁ ይገኛሉ።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ