1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተፈናቃዮች መመለስና ስጋት

ማክሰኞ፣ የካቲት 19 2016

ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ አካባቢያቸው መመለስ ቢጀመርም አሁንም ግን የፀጥታ ስጋት እንዳለ ተመላሾቹ ለDW ተናግረዋል። በአካባቢው የፀጥታ ስጋት በመኖሩም ወደ ቀድሞው ቀያቸው እስከአሁን ሳይሄዱ በወረዳ ከተማ በተዘጋጀው መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4cw49
በመንዲ ከተማ ከሚገኙ ተፈናቃዮች በከፊል
በመንዲ ከተማ ከሚገኙ ተፈናቃዮች በከፊልምስል Negassa Dessalegen/DW

ከምስራቅ ወለጋ ዞን ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች እየተመለሱ ነው

ከምስራቅ ወለጋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች እየተመለሱ ነው
ከምስራቅ ወለጋ ዞን ከተለያዩ ወረዳዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል በደብረብርሃን ከተማ የነበሩ ዜጎች ወደ የወረዳቸው እየተመለሱ እንደሚገኙ የዞኑ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽ/ቤት ወይም ቡሳ ጎኖፋ አስታውቋል፡፡ ለሁለት ዓመት በደብረ ብርሀን ከተማ የነበሩ 680 ሰዎች እስከ ትናንትናው እለት በዞኑ ስር በሚገኙ ስቡ ስሬ፣ጎቡ ሰዩ የተባሉና ሌሎችም ወረዳዎች ሰዎች መመለሳቸውን ጽ/ቤቱ ገልጸዋል፡፡ ወደ ወልዲያ እና ሌሎች አካባቢዎች የተፈናቀሉትንም ወደ ቀድሞ ቀያአቸው ለመመለስ ዝግጅት መደረጉን የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ዳኜ ላቺሳ ተናግረዋል፡፡ ወደ አካባቢው የተመለሱ ዜጎች በበኩላቸው በከተማ ውስጥ በተዘጋጀው መጠለያ መስፈራቸውን ገልጸውበጸጥታ ስጋት ምክንያትግን ወደ ገጠር መሄድ አለመቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡ 


በጎቡ ሰዩ ወረዳ አሁንም የፀጥታ ስጋት አለ
ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ አካባቢያቸው መመለስ ቢጀመርም አሁንም ግን የፀጥታ ስጋት እንዳለ ተመላሾቹ ለDW ተናግረዋል። በአካባቢው የፀጥታ ስጋት በመኖሩም ወደ ቀድሞው ቀያቸው እስከአሁን ሳይሄዱ በወረዳ ከተማ በተዘጋጀው መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች እና ሸማቂዎች መካከል ግጭት ተከስቶ እንደነበረ በአብነት አስረድተዋል፡፡
በምስራቅ ወለጋ ዞን ስቡ ስሬ በተባለ ወረዳ በ2014 ዓ.ም ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ የተከሰተውን ግጭት ሸሽተው ደብረ ብርሀን ከተማ እንደቆዩ የነገሩን ሌላው ነዋሪም ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ወደ ወረዳው መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡ የአብዛኛወ የተፈናቀሉ ዜጎች ንብረት መውደሙን የነገሩን ነዋሪው በስቡ ስሬ ወረዳም በተከተማ አካባቢ በተዘጋጀው መጠለያ ማረፋቸውን ጠቁመዋል፡፡ ወደ ወረዳው ለተመለሱ ዜጎች የቁሳቁስና በነፈስ ወከፍ ሰባት ኪሎ የእህል ድጋፍ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡


በደቡብ እና ሰሜን ወሎ የሚገኙ በቀጣይ ዙር ይመለሳሉ ስለመባሉ


በምስራቅ ወለጋ ዞን አምስት ወረዳዎች ውስጥ ከዚህ ቀደም በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ዜጎች ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተፈናቅለው ቆይተዋል፡፡ በዞኑ ዋዩ ጡቃ፣ለቃ ዱላቻ፣ ጎቡ ሰዩ እና ስቡ ስሬ ከተባሉ አካባቢዎች ሰዎች ተፈናቅለው እንደነበር የዞኑ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽ/ቤት/ቡሳ ጎኖፋ ኃላፊ አቶ ዳኜ ላቺሳ ተናግረዋል፡፡ የኦሮሚያ እና አማራ ክልል አመራሮች ከተፈናቀሉ ዜጎች ጋር ባደረጉት ውይይት ወደ ወረዳዎች በመጀመሪያ ዙር መመለስ መጀመራቸውን አመልክተዋል፡፡
‹‹በመጀመሪያ ዙር የተመለሱት 680 ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የተመለሱት ተፈናቅለው ደብረ ብርሀን ከተማ የነበሩ ናቸው፡፡ የተፈናቀሉ ዜጎች በሰሜን እና ደቡብ ወሎ፣ወልዲያም አሉ፡፡ በቀጣይ ዙር በተቀናጀ መልኩ ወደ ቀያአቸው የመመለስ ስራው ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ »
በምስራቅ ወለጋ ዞን ውስጥ ወደ ሌላ አካባቢ ከሸሹት በተጨማሪ ከ100ሺ በላይ ዜጎች ተፈናቅለው በተለያዩ የዞኑ ወረዳዎች ውስጥ እንደነበሩ ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በዞኑ ከ38ሺ በላይ የተፈናቀሉ ዜጎች የሚገኙባት ኪረሙ የተባለ ወረዳ ውስጥም ሰላም በሰፈነባቸው አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያአቸው እየተመለሱ እንደሚገኙ ተገልጸዋል፡፡
የፀጥታ ሁኔታውን ሳይሻሻልሌሎችም እንዲመለሱ ይደረጋል መባሉን አስመልክቶ የምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳር ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡን በስልክ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡


ነጋሳ ደሳለኝ 
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ማንተጋፍቶት ስለሺ