1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማጉፉሊ፣ ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 11 2013

የሥራ ሚንስትር በነበሩበት ዘመን የዕቅድ-ምግባራቸዉ መነሻና መድረሻ ሙስናን መዋጋት፣ ሙሰኞችን መመንጠር፣ መንገድ መገንባት ነበር።የበታቾቻቸዉ እንደማድነቅ-የበላዮቻቸዉ እንደማላገጥ ብለዉ «ዳምጠዉ» አሏቸዉ-ቡልዶዘር።

https://p.dw.com/p/3qtKB
Tansania Präsident John Magufuli verstorben
ምስል AFP

ማጉፉሊ መወደድና መጠላትን ያጣመሩ መሪ

የታንዛኒያዉ ፕሬዝደንት ጆን ማጉፉሊ ባለፈዉ ሮብ አርፈዋል።እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ከ2015 ጀምሮ ታንዛኒያን የመሩት ማጉፉሊ የሞቱት በልብ ሕመም መሆኑን የሐገሪቱ መንግሥት አስታዉቋል።ይሁንና ብዙ የፖለቲካ ተንታኞችና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እንደሚሉት ማጉፉሊ ያረፉት በኮቪድ 19 በሽታ ተይዘዉ ለረጅም ጊዜ በሕክምና ሲረዱ ቆይተዉ ነዉ።የማግፉሊ ምክንትል የነበሩት ወይዘሮ ሳሚያ ሱሑሉ ሐሰን የፕሬዝደንትነቱን ሥልጣን ተረክበዋል።የዛሬዉ ትኩረት በአፍሪቃ የማጉፉሊን የሕይወት ታሪክ ይቃኛል።ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

የሥራ ሚንስትር በነበሩበት ዘመን የዕቅድ-ምግባራቸዉ መነሻና መድረሻ ሙስናን መዋጋት፣ ሙሰኞችን መመንጠር፣ መንገድ መገንባት ነበር።የበታቾቻቸዉ እንደማድነቅ-የበላዮቻቸዉ እንደማላገጥ ብለዉ «ዳምጠዉ» አሏቸዉ-ቡልዶዘር።ስም ይቀድሞ ለምግባር እንዲሉ ሆኖ- ነዉ መሰል ፕሬዝደንት ከሆኑ በኋላም የታንዛኒያን ነባር ፖለቲካዊ አተሳሰብ፣ በሙስና የተተበተበ አሰራርና ልምድን እንደ ሜዳ፣ ጉባ፣ ሸለቆዉ እየፈነቃቀሉ፣ የራሳቸዉን አስተሳሰብ ሥራና አሥራር ይገነቡ ገቡ።ዶክተር ጆን ፖምቤ ጆሴፍ  ማጉፉሊ።
«ሥልጣን የያዙት ሙስናን መዋጋትና ተራዉን ሰዉ ለስልጣን ማብቃት  የመርሐቸዉ መሠረት በማድረጋቸዉ ነዉ።ሙስናን በመዋጋታቸዉም ከተራዉ ሕዝብ ከፍተኛ ድጋፍ አትርፈዋል።»
ይላሉ ኬንያዊዉ የፖለቲካ ተንታኝ ማርቲን አንዳቲ።በ2015 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሥልጣን እንደያዙ፣የታዛኒያን የነፃነት በዓልን በድግስ፣ ፌስታ፣ፈንጠዚያ መከበሩን አገዱ።ምክንያት-ወጪዉ ብዙ ነዉ የሚል ነበር።ይልቅዬ ሕዝቡ በየአደባባይ-አዳራሹ መጨፈር-መፈንጠዙን አቁሙ መንገድ እንዲጠርግ፣ ከተማ እንዲያፀዳ አዘዙ።እራሳቸዉም  እጄጌያቸዉን ሰቅስቀዉ አካፋ ይዘዉ ቁሻሻ ሲጠርጉ ዋሉ።
አምና ይሔኔ የኮሮና ተሕዋሲ ወረርሺኝ ዓለምን ሲያተራምስ፣ ቡልዶዞሩ የምርጫ ዘመቻ ላይ ነበሩ። ያቺን ባይን የማትታይ ረቂቅ ሕዋስ እርግጥ እንደ ሙስና መንገዱ መደፍለቅ አልቻሉም።ግን ካዷት።አደገኛ አይደለችም ብለዉ።የታንዛኒያ ጎረቤቶች በተለይ ዩጋንዳና ኬንያ የተሕዋሲዉን ስርጭት ለመከላከል የሰዓት እላፊና የመንቀሳቀስ ገደብ ሲጥሉም ታዛኒያ አታደርገዉም አሉ።ታንዛኒዉያን በተሕዋሲዉ አይለከፉምም።
«እኛ ታንዛኒያዉያን እራሳችንን ከእንቅስቃሴ አንገታም።አንድም ቀን ቢሆን የመንቀሳቀስ እገዳ አልጥልም።ምክንያቱም ፈጣሪያችን አሁንም አለና።እኛ ታንዛኒያዉያንን ይጠብቀናል።»
እንዲያዉም ባንድ ወቅት የፍየል ደምና የፓፓያ ጭማቂ በሚስጢር ለላቦራቶሪ ልኬ የሁለቱም ዉጤት ፖዘቲቭ (ተሕዋሲዉ አለበት) የሚል መልስ ሰጥተዉኛል» በማለት ተሳልቀዋል አሉ።የታንዛኒያ የጤና ሚንስቴር በኮቪድ 19 የተያዙና የሞቱ ሰዎችን ብዛት በይፋ ማስታወቁን ያቆመዉ አምና ግንቦት ላይ ነዉ።ያኔ በተሕዋሲዉ የተያዘዉ 509፣ የሞተዉ ደግሞ 19ኝ ታንዛኒያዊ ነበር።
ትንሽ ቆየት ብለዉ ግመሌንም እጠብቃለሁ፣ በአላሕም እወከላለሁ እንዳለዉ ሙስሊም ዓይነት ነገር አሉ።እንደ ሐኪምም ቃጥቷቸዋል።
«በእንፋሎት መታጠን (ስቲም)ን ጨምሮ መጠንቀቅ አለብን።እንፀልያለንም።ሰዉነታችን የኮሮና ተሕዋሲን መቋቋም እንዲችል ጥሩ ትመገቡ ዘንድ የየዕለት ሥራችሁን ማከናወን አለባችሁ።»
ከታንጋኒካ ጋር በፌደሬሽን ተጣምራ ታንዛኒያን የመሰረተችዉ የዛኒዚባሩ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንት ሰይፍ ሸሪፍ ሐማድ ባለፈዉ የካቲት በኮቪድ19 በሽታ መሞታቸዉ ሲሰማ ግን ደፋሩ፣ጠንካራዉ፣ አይበገሬዉ ማጉፉሊ፣ ደንገጥ፣አፈር ማለታቸዉ አልቀረም።ግን ዘግይተዋል።እሳቸዉም ብዙዎች እንዳሉት በዚያች በናቁ፣ በካድዋት ሕዋስ በጠና ታመዉ ወደቁ።ሞቱም።ምክትል ፕሬዝደንት ሳሚያ ሱሉሐ ሐሰን።ሮብ።
«ወገኖቼ ሆይ፣ ዛሬ መጋቢት 17፣ 2021፣ ከአመሻሹ 12 ሰዓት ላይ  ጀግናዉን መሪያችንን፣ የታንዛኒያ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት፣ ክቡር ጆን ፖምቤ ጆሴፍ ማጉፉሊን ማጣታችንን ስነግራችሁ በታላቅ ሐዘን ነዉ።(ፕሬዝደንቱ) ያረፉት ይታከሙበት በነበረዉ በዳሬሰላም፣ ምዜራ ሆስፒታል ዉስጥ በልብ ሕመም ነዉ።»
የተከበሩት መሪ አደገኛነቱን በካዱ፣በናቁ፣ በተሳለቁበት ሕዋስ ሞቱ አይባልም።ብቻ ሞቱ።61 ዓመታቸዉ ነበር።
የጁሊየስ ኔሬሬ ፅናት፣ የዓሊ ሐሰን ምዊኚይ ብስለት፣ የቤንጃሚን ምካፓ ትዕግስት፣ የጃኪያ ኪኪዌቴ ብልጠት ብዙ አይታይባቸዉም።ግን የሁሉም ጅምር አስቀጣይ፣ የስልጣን-ፓርቲያቸዉ ወራሽም ነበሩ።ጆን ፖምቤ ጆሴፍ ማጉፉሊ።ከሁሉም በፊት ግን እንደ ኔሬሬ «ሙዓሊም» በሚል ቅፅል ለመንቆለጳጳስ አይታደሉ እንጂ በርግጥ መምሕር ነበሩ።
የገበሬ ልጅ ናቸዉ።ጎበዝ ተማሪ።በ1994 ሁለተኛ፣ በ2009 ሶስተኛ ዲግሪያቸዉን ከዳሬ ኤ ሰላም ዩኒቨርስቲ እንዳገኙ ሴንግራማ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት አስተማሪ ሆነዉ ነበር።ጥቂት ቆይተዉ የኢንዱስትሪያል ኬሚስትሪ ባለሙያ ሆኑ።የኔሬሬን የቻማ ቻ ማፒንዱዚ (CCM) ፓርቲን የተቀላቀሉትም ያኔ ነበር።
በ1995 የምክር ቤት እንደራሴ ሆነዉ ተመረጡ።የሥራ ሚንስቴር ምክትል ሚንስትር ሆነዉ የተሾሙትም በዚያዉ ዓመት ነዉ።በ2000 ሚንስትር ሆነዉ ሌላ መስሪያ ቤት ተዛወሩ።ከ10 ዓመት በኋላ በ2010 ዳግም የሥራና የመገንድ ትራስፖርት ሚንስትር ሆነዉ ሲሾሙ በሙስና የሚጠረጠሩ ሰራተኞችንና የየክፍል ኃላፊዎችን ከየነበሩበት ሥፍራ እየነቀሉ ጣሉ።የመንግድ፣ የከተማና የምድር ባቡር ሐዲድ ግንባታዉን ያጣድፉት ያዙ።«ቡልዶዘር» የተባሉትም ያኔ ነበር።
በ2015 በተደረገዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ  የተቃዋሚዉን የቻዴማ ፓርቲን ዕጩ ኤድዋርድ ሎዋሳን አሸንፈዉ በግጭት ዉዝግብ በሚታበጡ ጎረቤቶችዋ መሐል ሰላሟን ጠብቃ የኖረችዉን ሐገር የመሪነት ሥልጣን ተቆጣጠሩ።በ2020ም ደገሙት።የአምናዉ ምርጫ ሒደት፣ ግጭት፣ የገዢዉ ፓርቲ ጫናና የፀጥታ አስከባሪዎች ተፅዕኖ አልተለየዉም ነበር።
የተቃዋሚዉ ፓርቲ ዕጩም የተጭበረበረ ብለዉታል።የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲን ጨምሮ የአንዳድ ሐገራት ታዛቢዎችም የምርጫዉ ሒደት አጠራጣሪነቱን አስታዉቀዋል።ሰዉዬዉ ግን በድል ማግስት ተቃራኒዉን አሉ።
                                 
«እንደምታዉቁት፣ በብዙ ሐገራት ምርጫ የግጭት ምንጭ ነዉ።እኛ ታንዛኒያዉያን ግን ይሕንን ፈተና በሠላም አልፍነዉ። ታንዛኒያዉያን ሠላም ወዳድ መሆናችንን ለመላዉ ዓለም ያስመከርንበት ነዉ።ዲሞክራሲያችን እየበሰለ መሆኑንም ያረጋገጥንበት ነዉ።»
6 ዓመት ባልሞላ ዘመነ ሥልጣናቸዉ፣ የመሠረተ ልማት አዉታሮችን አስፋፍተዋል።መንገዶች አስገንብተዋል።የባጋሞዮ ወደብን፣ የዳሬ ኤ ሰላም ዓለም አቀፍ አዉሮፕላን ማረፊያን ባዲስ መንገድ አስገንብተዋል።የሐዲድ መስመር ዘርግተዋል ወይም አሻሻለዋል።
በተለይም በዝቅተኛዉ መደብ ታንዛኒያዊ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት አትርፈዋል።ለተቃዋሚ፣ ለተቺ፣ ለገለልተኛ መገናኛ ዘዴዎች ግን ምሕረት የለሽ ነበሩ።ገለልተኛ መገናኛ ዘዴዎች ከመንግስት ሳይፈቀድላቸዉ ዓለም አቀፍ ይዘት ያላቸዉን ጉዳዮች እንዳይዘግቡ በሕግ አግደዉም ነበር።አምና በተደረገዉ ምርጫ ማጉፉሊን ተፎካክረዉ የነበሩት ቱንዱ ሊሱ ማጉፉሊን ብዙ የሠሩ ግን አምባገነን ይሏቸዋል።
«አዎ አነዚሕን ሁሉ ገንብተዋል።ይሕ ግን ለተዛባ አገዛዛቸዉ የትክክለኛነት ማረጋገጪያ ሊሆን አይችልም።ይሕ በሐገሪቱ ላይ ያሰፈኑትን የፈላጭ ቆራጭ አምባገነናዊ መርሕን ሊሸፍን አይችልም።»
ሮብ ማታ በሞታቸዉን ያወጁት ምክትል ፕሬዝደንት ሳሚያ ሱሉሑ ሐሰን ትናንት አርብ የፕሬዝደንትነቱን ሥልጣን ይዘዋል።ለሟቹ አለቃቸዉ ክብርም የ14 ቀን ብሔራዊ ሐዘን አዉጀዋል።

Tansania Daressalam| Amtseinführung neue Präsidentin Samia Suluhu Hassan
ምስል AFP/Getty Images
Tansania Präsident John Magufuli verstorben
ምስል AFP
Tansania Dar es Salaam | Trauer um John William:  Präsident John Magufuli leitet Trauerveranstaltung
ምስል Said Khamis/DW
Tansania Daressalam | Amtseinführung neue Präsidentin Samia Suluhu Hassan
ምስል Stringer/REUTERS

ነጋሽ መሐመድ 

እሸቴ በቀለ