1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሱዳን

ማሕደረ ዜና፣ የሱዳን ጦርነት፣ የተቃራኒ መሪዎቿ- ተቃራኒ መልዕክት

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ መስከረም 14 2016

ሱዳን በ1956 ነፃነቷን ካወጀችበት ጊዜ ጀምሮ ጦርነት ተለይቷት አያዉቅም።ዋናዉ ጦርነት ደቡብ ሱዳን ዉስጥ ሁለቴ በተደረገዉ ረጅም ጦርነት ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ አልቋል። ለኢትዮጵያ ኤርትራ እንደነበረች ሁሉ ለሱዳንም የደቡብ ሱዳን መገንጠል ሰላም ያመጣል ተብሎ ነበር። ተገነጠለች። ለሁለቱም ሱዳኖች ያመጣዉ ሠላም የለም።

https://p.dw.com/p/4Wn8o
ቻድ ከገቡት ስደተኞች አብዛኞቹ የዳርፉር ግዛት ነዋሪዎች ናቸዉ
የሱዳንን ጦርነት ሸሽተዉ ቻድ ከገቡ የሱዳን ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ አንዱምስል ZOHRA BENSEMRA/REUTERS

የሱዳን ጦርነትና የተዋጊዎቹ ኃይላት የመሪዎች መልዕክት

በመፈንቅለ መንግስት የዓለምን «ክብረ-ወሰን» የያዘችዉ፣ በርስ በርስ ጦርነት ረጅም ዘመን ያስቆጠረችዉ ሱዳን ዛሬም በጦርነት ትወድማለች።በመፈንቅለ መንግስት ሥልጣን ይዘዉ የነበሩት የተፋላሚ ኃይላት መሪዎች መወጋገዝ፣ መዛዛት፣የዉጪ ኃይላትን ከየጎናቸዉ ለማሰለፍ መጣጣር፣ ማስጠንቀቃቸዉን ቀጥለዋል።ደግሞ በተቃራኒዉ ለመደራደር ፈቃደኛ መሆናቸዉን እያስታወቁ ነዉ።ጦርነቱ፣ የህዝቡ ስቃይ-ስደትም እንደቀጠለ ነዉ።ሁለቱ ተፋላሚ ኃይላት «ወዳጅ» በነበሩበት ዘመን «የጋራ ጠላት» የነበሩት አማፂያን እንደየዝንባሌ-ጥቅማቸዉ ተቃራኒ ጎራዎችን እየተቀየጡ ነዉ።ኃያል፣ ሐብታሙ ዓለም ወዳጅ-ጠላት ለመምረጥ መመዘኛዉ፣ ድጋፍ ጠያቂዉ ወገን ከኪቭ-ሞስኮዎች መቃረን-መጣጣሙ ነዉ።የሴዳን ተቃራኒ መሪዎች ተቃራኒ መልዕክት መነሻ፣ የኃይል አሰላለፉ ማጣቃሻ፣ የጦርነቱ ጉዳት መድረሻችን ነዉ። የሱዳን ጎረቤቶች ጉባኤ
                                  
ዋዲ-ሐልፋ-ሰሜን ሱዳን።ያዉ እንደ ሁሌዉ ተናዳፊዋ የቀትር ፀሃይ ወደ ምዕራብ ዘንበል፣ በረድ ስትል  ከቅድሞዉ ትምሕርት ቤት ግቢ የሰፈሩ ስደተኞች ወደ ዉጪ፣ወደ በንረዳ፣ ወደ ሜዳም ብቅ ይላሉ።ሕጻናቱ  ይጫወታሉ።ከአዋቂዎቹ ገሚሱ ልጆቹን ያያል። ሌላዉ የሚላስ የሚቀመስ ያበስላል።የተቀረዉ ፈጣሪዉን ይማፀናል።ሲሐም ሳሌሕ ትቆዝማለች።ጋዜጠኛ ነበረች።»ከሱዳን መዉጣት በጣም ከባዱ ምርጫ ነዉ» ትላለች። የ45 ዓመቷ ሲሐም። ግብፅ ገብታ ስደተኛ ለመሆን ድንበር ላይ ትጠባበቃለች።
      
«ከሱዳን መዉጣት የማይታመን ከባድ ምርጫ ነበር።ግን ምን ይደረግ።እኛ ጋዜጠኞች ሙያዊ ምግባራችንን መከወን በጣም አደገኛ ሆነ።ጋዜጠኞች ከዚሕ ቀደም በነበረዉ ደረጃ እንኳ ሥራቸዉን በነፃነት መስራት አይችሉም።ሕይወታቸዉ ላደጋ የተጋለጠ ነዉ።ወይም ይታሰራሉ።የሁሉም ኢላማ ናቸዉ።ለዚሕ ነዉ ለመሰደድ የወሰንኩት።ፈጣሪ ሰላሙን እስኪያመጣ ምናልባት መሸሸጊያ ባገኝ።»ትኩረት በአፍሪቃ፤ የሱዳን ዉጊያ፣የአፍሪቃ ቀንድ ቀዉስ

ሁለቱ ጄኔራሎች ካለፈዉ ሚያዚያ ወዲሕ ለመጠፋፋት ይፈላለጋሉ
ከግራ ወደ ቀኝ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎና ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አልቡርሐን ወዳጅ በነበሩበት ዘመንምስል Mahmoud Hjaj/AA/picture alliance

አላበለችም።ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐንና ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ ጠባቸዉ ከርሮ የሱዳን መከላከያ ጦርና የሐገሪቱ ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት ኻርቱም ዉስጥ ዉጊያ በገጠሙ ዕለት ሚዚያ 7 ከተደበደቡት የከተማዋ ነዋሪዎች አንዱ የቢቢሲ ዘገባ ነበር።በዚያዉ ሚያዚያ ዘጋቢና ፎት ግራፍ አንሺ ፈይዝ አቡበከር ጀርባዉን በጥይት ተመታ።ግን አልሞተም።
ከዚያ በኋላ የተገደለ፣ የቆሰለ፣ የተደበደበ፣ የታሰረዉ ጋዜጠኛ ብዛት ገና እየተቆጠረ ነዉ።ከጋዜጠኞች ሌላ እዉቋ ተዋኝ አሲያ አብዱል መጆድ፣ ድምፃዊት ሻዳን ጋርዱድ፣ የቀድሞዉ የብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋች ፎዉዚ አል መሕዲ ከነልጆቹ እና ሌሎች ብዙዎች አንድም የተባባሪ፣ ሁለትም ያነጣጥሮ ተኳሾች ጥይት ማብረጃ ሆነዋል። 
ጋዜጠኛ ሲሐም የተጠለለችበት ዋዲ ሐልፋ 22 ሺሕ ስደተኞች በ53  ጣቢያዎች ሠፍረዋል።የዋዲ ሐልፋ ወጣቶች የመሰረቱት የሐልፋ አስቸኳይ ክፍል የተባለዉ ስብስብ  ኃላፊ ኦዴይ መሐመድ እንደሚለዉ ተፈናቃዮቹ ምግብ፣መድሐኒት፣ በቂ መጠለያ አያገኙም።
       
«የያዙትም ገንዘብ እያለቀባቸዉ ነዉ።ምግብ፣መድሐኒት፣ መጠለያ፣ የጤና ጥበቃ ይፈልጋሉ።ወደ ግብፅ ለመሻገር ደግሞ ቪዛና ፓስፖርት ያስፈልጋቸዋል።»
 ሐሙስ፣ መስከረም 21፣2023 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የአዣንስ ፍራንስ ፕረስ ጋዜጠኞች ግብፅ ድንበር አጠገብ የሠፈሩትን ሱዳናዉያን የመሰደድ ተስፋና ቀቢፀ-ተስፋ የተጠናቀረበትን የቪዲዮ ዘገባ ለዓለም አሰራጩ።ማሕደረ ዜና፣ ሱዳን «የጅል ዉጊያ» ሐገር
ከዋዲ ሐልፋ ኻርቱም 9 መቶ ኪሎ ሜትር ይርቃል።ሰዉዬዉ ግን ኻርቱም መሆን አለመሆናቸዉ ከጥርጣሬ በስተቀር በዉል እይታወቅም።እሳቸዉም ስለ ዋዲ ሐልፋ ይሁን ሌላ ሥፍራ ስላሉ ወይም ስለሞቱ  ሱዳናዉያን ብዙ የሚያዉቁት፣ ቢያዉቁም ብዙ የተጨነቁበት አይመስሉም።
ያስጨነቃቸዉ ከኻርቱም 10 ሺሕ ኪሎ ሜትር ርቀዉ የሔዱት ቀንደኛ ጠላታቸዉ ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን ኒዮርክ ላይ የሚሉ-የሚያደርጉት ነዉ።ኒዮርክ ነጋ። አል ቡርሐን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የሚያደርጉትን ንግግር አስረቅቀዉ፣ አርመዉ፣እየተለማመዱ ተራቸዉን እየጠበቁ ነዉ።
ኻርቱም መሽቷል።ቴሌቪዥን የማየት እድል፣ ምቾትና ፍላጎት ያለዉ ሱዳናዊ የአል ቡርሐንን ንግግር ለመስማት ሲጠባበቅ የጄኔራል መሐመድ ዳግሎ መልዕክት ካልታወቀ ሥፍራ በኢንተርኔት ተሰራጨ።
 «የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (RSF)በመላዉ ሱዳን ተኩስ አቁም ለማወጅ ዝግጁ ነዉ።ይሕ ሰበአዊ ርዳታ እንዲገባ፣ ሰላማዊ ሰዎችና ርዳታ አቅራቢዎች ሰላማዊ መተላለፊያ እንዲያገኙ ይረዳል።ከዚሕም በተጨማሪ ትርጉም ያለዉና ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ ምክክር እንዲደረግ መነሻ ይሆናል።ምክክሩ አጠቃላይ ፖለቲካዊ መፍትሔ የሚያመጣ፣ የሲቢላዊ መንግስት ለመመሰረት የሚያስችል፣ ሐገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ሰላም የሚመራ መሆን አለበት።»
ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን የመሐመድ ሐምዳን ዳግሎን መልዕክት አልሰሙም ማለት ሲበዛ ከባድ ነዉ።ይሁንና ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር ጠላታቸዉ በአሸባሪነት እንዲፈረጅ ዓለምን ከማሳሰብ ባለፍ የድርድር ፍንጭ አልሰጡም።
«የፈጥኖ ደራሽ ጦርንና ተባባሪዎቹን ሚሊሻዎች (የዓለም መንግስታት) በአሸባሪነት እንዲፈርጁ በድጋሚ እጠይቃለሁ።የፈፀሙት ወንጀል በአሸባሪነት እንዲፈረጁ በቂ ማስረጃ ነዉ።እነሱን የሚደግፉት ወገኖችም ጠንካራ ርምጃ ሊወሰድባቸዉ ይገባል።ሰዉ የገደሉ፣ ቤት ያቃጠሉ፣ ሴቶችን የደፈሩ፣ ሕዝብ ያፈናቀሉ፣ሐብት ንብረት የዘረፉ፣ የሰረቁ፣ የገረፉ፣ የጦር መሳሪያና አደንዛዥ ዕፅ ያሸጋገሩ፤ ቅጥረኛ ወታደሮችን ያስገቡ፣ልጆችን ለወታደርነት ያሰለፉና ተባባሪዎቻቸዉ ሊጠየቁ ይገባል።»
አል ቡርሐን በንግግራቸዉ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ሁነኛ ርምጃ ካልወሰደ የሱዳኑ ጦርነት ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሊዛመት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
እዚያዉ ሱዳን ዉስጥ የሚገኙት የደቡባዊ ሱዳንና የዳርፉር አማፂያን አንድም የአል ቡርሐን መከላከያ ሠራዊትን አለያም የሐምዲቲን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል እየወገኑ መዋጋት ይዘዋል።ዘገቦች እንደሚጠቁሙት የግብፅና የዩክሬን መንግስታት የአል ቡርሐንን መከከያ ሠራዊት፣ የሩሲያዉ ቫግነር ቡድን፣ የሊቢያዉ የኸሊፋ ሐፍጣር ጦር፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬት መንግስት የሐምዲቲን ፈጥኖ ደራሽ ጦር ይደግፋሉ። 
የአል ቡርሐን መንግስት ኬንያም የሐምዲቱን ፈጥኖ ደራሽ ጦር ይደግፋል በማለት ይወነጅላታል።አንድ ሰሞን የሱዳን ጋዜጦች ኢትዮጵያም በሱዳን መከላከያ ጦር ላይ ዉጊያ ከፍታለች በማለት ዘግበዉ ነበር።ኋላ ግን ከጋዜጠኞቹ ቢያንስ አንዱ ይቅርታ መጠየቁ ተሰምቷል።
አል ቡርሐን «ጦርነቱ አካባቢዉን«» ያዳርሳል ባሉ ሳልስት ባለፈዉ ቅዳሜ ደብሊን-አየር ላንድ አዉሮፕላን ማረፊያ ዉስጥ የዩክሬኑን ፕሬዝደንት ቮልዶሜየር ዘሌንስኪን አነጋግረዋል።
ዜሌኒስኪ አል ቡርሐንን ካነጋገሩ በኋላ በቴሌግራም ባሰራጩት መልዕክት እንዳሉት ዉይይታቸዉ ያተኮረዉ በሁለት ጉዳዮች ላይ ነበር።ዜሌንስኪ «ሩሲያ በገንዘብ የምትደግፋቸዉ» ና «ሕገ-ወጥ» ያሏቸዉ ኃይላት ስለሚያደርጉት እንቅስቃሴና የዩክሬን ስንዴ ሱዳን ስለሚደርስበት ሁኔታ።
በኢትዮጵያና ኬንያ ላይ ያነጣጠረዉ ዉንጀላ ወይም ዘገባ እዉነትም ሆነ ሐሰት የሱዳኑ ጦርነት ከአካባቢዉ አልፎ ዓለም አቀፋዊ መልክና ባሕሪ መያዙን ለማወቅ አል ቡርሐን ራሳቸዉ ካደረጉት ሌላ ሌላ ማስረጃ መፈለግ በርግጥ ጊዜ ማባከን ነዉ።ቅርጽና አድማሱን ያሰፋው የሱዳን ጦርነት
አል ቡርሐን ከዚሕ ቀደም ከእስራኤል መሪዎች ጋር ዩጋንዳ ዉስጥ ተገናኝተዉ ተነጋግረዋል።አሁን ደግሞ የኪቭ መሪዎችን ጠጋ-ጠጋ ማለታቸዉ የመጨረሻ ግባቸዉን የትነት ጠቋሚ ነዉ።ጄኔራሉ ኒዮርክ ላይ በአሸባሪነት እንዲፈረጁ ሲወተዉቱ ከነበሩት ከፈጥኖ ደራሽ ጦር አዛዦች ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸዉን ሰሞኑን ለቢቢሲና ለሮይተርስ ዜና አገልግሎት በሰጡት መግለጫ አስታዉቀዋል።
እያወገዙ ድርድር።
እዚያዉ ኒዮርክ ዉስጥ የዓለም ፍርድ ቤት ተወካዮች፣ የሰበአዊ መብቶች ተሟጋቾችና የኃያላን ሐገራት ዲፕሎማቶች ስለሱዳን እያነሱ ይጥሉ ነበር።
የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ልዩ አማካሪ አማል ክሎንይ እንደሚሉት የዛሬ 20 ዓመት የተደረገዉ የዳርፉር ጦርነት ወንጀለኞች ለፍርድ ባለመቅረባቸዉ የዘንድሮዉ ግፍ ተደገመ ይላሉ።
«በጎሳ ላይ ያነጣጠረ ግፍ፣ መንደሮችን ማቃጠል፣ በጅምላ መግደልና ሰላማዊ ሰዎችን ማባረር-ይሕ የዛሬ 20 ዓመቱ ዳርፉር ነበር።ይሕ ቅዠት አሁንም እየተደገመ ነዉ።ለምን? ሁላችንም እንደምናዉቀዉ ላለፈዉ ወንጀል ተጠያቂ የሆኑት ወገኖች ለፈፀሙት ምግባር መልስ እንዲሰጡ ባለመደረጉ ነዉ።»
ዳርፉር ዉስጥ የዛሬ 20 ዓመትም ሆነ ዘንድሮ ተፀፈ ለሚባለዉ ግፍ በግንባር ቀደምትነት ይጠየቃሉ የሚባሉት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር አዛዦች ናቸዉ።በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የብሪታንያ አምባሳደር ባርባራ ዉድዎርድ ግን መጠየቅ ያለበት ሁሉም ነዉ ባይ ናቸዉ።
«የዳርፉሩ ግፍ በፈጥኖ ደራሽ ኃይልና በተባባሪዎቹ ሚሊሻዎች መፈፀሙ በግልፅ ቢታወቅም፣ የሱዳን ጦር ይሎችን ጨምሮ ሁለቱም ኃይላት፣ሱዳንን ዳግም ከጦርነት በመዶላቸዉ ተጠያቂ ሥለመሆናቸዉ ግልፅ  ልንሆን ይገባል።»
የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ከሪም AA ኻንም የብሪታንያዋን አምባሳደር ሐሳብ የሚጋሩ ይመስላሉ።
«በዚሕ ግጭት በግልፅ የሚታወቁ ሁለት ወገኖች አሉ።ፈጥኖ ደራሽ ጦርና ጦር ኃይሎች።ታሪኩ በደንብ  ይታወቃል።የሚደግፏቸዉ አንዳድ መንግስታት አሉ።እነማን እንደሆኑ መናገር አያስፈልገኝም።እንደሚመስለኝ ከተዋጊዎች ይልቅ ሰብአዊነትን እንዲደግፉ እንፈልጋለን።»
ሱዳን በ1956 ነፃነቷን ካወጀችበት ጊዜ ጀምሮ ጦርነት ተለይቷት አያዉቅም።ዋናዉ ጦርነት ደቡብ ሱዳን ዉስጥ ሁለቴ በተደረገዉ ረጅም ጦርነት ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ አልቋል።ለኢትዮጵያ ኤርትራ እንደነበረች ሁሉ ለሱዳንም የደቡብ ሱዳን መገንጠል ሰላም ያመጣል ተብሎ ነበር።ተገነጠለች።ለሁለቱም ሱዳኖች ያመጣዉ ሠላም የለም።

Krieg im Sudan | Flüchtlinge im Tschad
ምስል MOHANED BELAL/AFP
ሐምዲቱ በቅርቡ ባስተላለፉት መልዕክት ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸዉን አስታዉቀዋል
ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ (ሀምዲቲ) ለፈጥኖ ደራሽ ጦራቸዉ ንግግር ሲያደርጉምስል Rapid Support Forces/AFP
«የፈጥኖ ደራሽ ኃይልና ተባባሪዎቹ በአሸባሪነት መፈረጅ አለባቸዉ» አል ቡርሐን
ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ንግግር ሲያደርጉምስል Craig Ruttle/AP/picture alliance
ኻርቱም የተጀመረዉ ጦርነት ወደ ዳርፉር ተስፋፍቷል
ርዕሰ ከተማ ኻርቱም በጦርነቱ በከፊል ስትጋይምስል Wang Hao/XinHua/picture alliance

ከ2003 ጀምሮ ምዕራብ ሱዳን ዳርፉር ዉስጥ በተደረገዉ ጦርነት 200 ሺሕ ሕዝብ አልቋል።2 ሚሊዮን ተፈናቅሏል።ሱዳን።15 መፈንቅለ መንግስታትና ሙከራዎች አስተናግዳለች።የመጨረሻዉ ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አልቡርሐን እንደ ሊቀመንበር፣ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ እንደ ምክትል የመሩና ያስተባበሩት ነዉ።ጥቅምት።2021።
ሁለቱ ጄኔራሎች የሚመሯቸዉ ኃይላት ካለፈዉ ሚዚያ ጀምሮ በገጠሙት ዉጊያ በጣም ሲያንስ 5 ሺሕ፣ ሲበዛ 10 ሺሕ ህዝብ አልቋል።በጦርነቱ መሐል  በመቶ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ፣የኤርትራ፣ የሶማሊያና የሶሪያ ስደተኞች መገደላቸዉም ተዘግቧል።ከ5 ሚሊዮን የሚበልጥ ሱዳናዊ አንድም ተሰዷል አለያም ተፈናቅሏል።
የጦር አበጋዞቹ ዛሬም ከሰላም ጥሪ ይልቅ የተጨማሪ ዉጊያ፣ ዛቻ ፉከራ፣ ድጋፍ የማሰባሰብ ዘመቻ ላይ ናቸዉ። ቸር ያሰማን። 
 

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር