1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕደረ ዜና፣ ብሔራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ ዉስብስብ ችግሮች መፍትሔ ያመጣ ይሆን?

ሰኞ፣ ግንቦት 26 2016

ወጣቶች ሥራ የላቸዉም።ሥራ ያለዉም ከቤቱ በሰላም ወጥቶ መግባቱ አጠራጣሪ ነዉ።የኑሮ ዉድነት፣ ድርቅ፣ ረሐብ ሚሊዮኖችን ተመፅዋች አድርጓቸዉ።ብሔራዊ ምክክር፣ ውይይት፣ ድርድር፣ አብዮት ይባል ሕዝባዊ አመፅ የኢትዮጵያ ሕዝብን ከሞት፣ከሥደት፣ ከረሐብ፣ ሥቃይና ሰቆቃ የሚያላቅቅ መፍትሔ ካላመጣ በርግጥ ሁሉም ከንቱ ነዉ።

https://p.dw.com/p/4gbEh
የምክክሩ ሒደት የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግሮች በዉይይት ለመፍታት እንደሚረዳ አዘጋጆቹ እየተናገሩ ነዉ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር አዲስ አበባ ዉስጥ ባለፈዉ ቅዳሜ በይፋ በተጀመረበት ወቅትምስል Solomon Muchie/DW

ማሕደረ ዜና፣ ብሔራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ ዉስብስብ ችግሮች መፍትሔ ያመጣ ይሆን?

 

ለረጅም ጊዜ ሲፈለግ፣ ሲጠየቅ፣ሲጠበቅ፣ ሲነገር የነበረዉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ባለፈዉ ቅዳሜ በይፋ ተጀምሯል።የምክክሩ ሒደት ብዙዎች እንደሚያምኑበት ረጅም፣የሚመከርባቸዉ ጉዳዮች በጣም ብዙ፣ ዉስብስብና ጥልፍልፍ ናቸዉ።በተፈለገና በታሰበዉ መንገድ ይቀጥል፣ የሚፈለገዉን ዉጤት ያመጣ ይሆን? ያፍታ ዝግጅታችን ጥያቄ ነዉ፣ አብራችሁን ቆዩ።

ከዚያ የኢትዮጵያ ትላልቆች ከታደሙበት ትልቅ፣ አዲስ አዳራሽ፣ አዳዲስ ሙዚቃ፣ ማርሽ፣ ነባሩ ብሔራዊ መዝሙርም ተንቆረቆረ።ቅዳሜ።አላማዉ አዘጋጆቹ እንዳሉት የኢትዮጵያን የዘመናት ጥርቅም፣ ዉስብስብና  አወዛጋቢ ችግሮች በዉይይት ለመፍታት ነዉ።ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ስብሰባና ዓላማዉን «የማይዘነጋ»አሉት።ጭብጨባዉም ቀለጠ።

«ከወትሮዉ በተለየ መንገድ በዚሕ መንገድ መገናኘታችን  በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ አንዱ የማይዘነጋ ምዕራፍ ሥለሆነ ይሕንን ዕድል ያገኘን፣ በዚሕ ታሪካዊ አዳራሽ የምገኝ፣ ለኢትዮጵያ የሚበጀዉን ለመምከር የወሰንን፣ ሁላችሁም፣ ሁላችንም እንኳን ደስ ያላችሁ፣ ደስ ያለን እላለሁ።»

የጠቅላይ ሚንስትሩ የሠላም ጥሪና መልዕክት ከአዲሱ አራሽ ሲንቆረቆር ባንድ ወቅት ለጠቅላይ ሚንስትሩ አዲስ መንግስት  ጠንካራ ድጋፍ ሲሰጡ ከነበሩ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች አቶ የሺዋስ አሰፋና ብጤዎቻቸዉ እዚያዉ አዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸዉን ሰማን።

ኢትዮጵያ የምክክርና ዉይይት ጥያቄ ያልተመለሰባት ሐገር

 

ኢትዮጵያ ነባሮቹን ይሁን በቅርብ ዘመን ታሪኳ የገጠሟትን ችግሮች ለማስወገድ ዉይይት፣ ድርድር፣ ምክክር እንዲደረግ የየዘመኑ ገዢዎች አማካሪዎች፣ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ምሑራን፣የኃይማኖት መሪዎች፣ የሐገር ሽማግሌዎች፣ ጋዜጠኞች ሳይቀሩ የየዘመኑን መሪዎች ያልጠየቁ፣ያላሳሰቡ፣ ያልመከሩ፣ ያልተቹበት ጊዜ የለም።አንዳቸዉም አልተቀበሉትም።

ንጉሰ ነገስት አፄ ኃይለሥልሳሴ በ1953 መፈንቅለ መንግስት ከተሞከረባቸዉ በኋላ የሩቁ አይደለም የቅርብ ዘመድ፣ ታማኝ ጄኔራሎቻቸዉን፣ የሲቢል ሹማምቶታቸዉን፣ ዲፕሎማቶቻቸዉን፣ የፖለቲካ አማካሪዎቻቸዉን የእንመካከር ጥያቄ አልሰሙም።አብዮት ሥርዓታቸዉን መንግሎ ጣለዉ።ለዉይይት፣ ድርድር፣ ምክክር፣ ጥያቄና ምክር የደርግ ሥርዓት አፀፋ ከአፄዉ የከፋ እንጂ የተለየ አልነበረም።በጠመንጃ ኃይል ተወገደ።1983።

ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የሚመሩት ኮሚሽን ምክክሩን ለማስጀመር ለሁለት ዓመታት ያክል ሲጥር ነበር
የኢትዮጵያ ብሑራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ ምስል Sjewangizaw Wegayehu/DW

በዚያ ዘመን ዓለም አዲስ ከጀመረችዉ የፖለቲካ ጉዞ ጋር የአራት ኪሎ ቤተ-መንግስትን የተቆጣጠረዉ ኢሕአዴግ የኢትዮጵያን ችግሮች ለመፍታት ለዉይይት-ምክክር እንዲገዛ ከቀዳሚዎቹ ሥርዓታት ሁሉ ጠንከራ ግፊት፣ተደጋጋሚ ጥያቄና ትችት ገጥሞት ነበር። አልተቀበለዉም።በሕዝባዊ አመፅ ተወገደ።2010።

አሁንም ፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፕሬዝደንት መረራ ጉዲና በቅርቡ እንዳሉት  የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታምሟል።50 ዓመቱ።

«ባለፉት 50 ዓመታት ከፖለቲካ አዙሪት መዉጣት አልተሻለም።ሥለዚሕ ፖለቲካችን ታሟል።እሱን ማዳን ካልተቻለ ሐገሪቷም አትድንም። ሁሉም ሕዝቦች ጥያቄቸዉ አላቸዉ---ያ የተበላሸ ፖለቲካ ኢትዮጵያ በሚባል ደረጃ ሁሉንም እስር ቤት ከትቷቸዋል።»

በመሠረቱ ኢትዮጵያ ዉስጥ ብሔራዊ ምክክር ያስፈለገዉ ፕሮፌሰር መረራ «ታሟል» ያሉትን የኢትዮጵያ የ50 ዓመት ፖለቲካ ለማከም ወይም «የታሪክ ሸክሞች» ያሉትን ነባር ችግሮች ለማቃለል ነዉ።አቶ ባይሳ ዋቅ ወያ የቀድሞዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለሙያ የሕግ አዋቂም ናቸዉ።የኢትዮጵያ መንግስት የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ከመሠየሙ በፊት በነበረዉ ዉይይትና ዝግጅት ላይ ተካፍለውለዋልም።

«ኢትዮጵያ የብዙ ዘመናት ታሪክ የኖራት፣ የሊግ ኦፍ ኑሽን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መሥራችና አባል የሆነች ሐገር እንዴት አንድ አገረ ብሔር መመሥረት አልቻለችም።በሌላ አማርኛ ለምድነዉ አንድ የጋራ ማንነት ልንፈጥር ያልቻልነዉ።መሠረታዊ ችግሩን ይሕንን፣ ለምንድነዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ የጋራ ማንነት ወይም ተቀራራቢ ማንነት የሌለዉ----ሰዎች ለምንድነዉ በባንዲራ፣ በብሔር፣ በኃይማኖት---»

የምክክሩ ሒደት የሚፈለገዉን ዉጤት ያመጣ ይሆን?

 

የእስከ ቅዳሜዉ ሒደት ዓመታት ጠይቋል።ብቻ ምክክሩ በይፋ ተጀመረ። ግን መሠረታዊ የኢትዮጵያ ችግሮችን ለመፍታት መጥቀም አለመጥቀሙ አሁንም እንዳከራከረ ነዉ።መንግስትን በነፍጥ የሚወጉ ኃይላት በምክክሩ አይሳተፉም።«ኮከስ» የሚባለዉ ስብስብ የሚያስተናብራቸዉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም አልተካፈሉም።ኢሕአፓም በምክክሩ እንደማይሳተፍ አስታዉቋል።

ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ በምክክሩ ላለመካፈል ከሰጧቸዉ ምክንያቶች ዋናዉ ምክክሩን ያደራጀዉ ኮሚሽን በመንግስት የተሰየመ መሆኑን ነዉ።፣ከክላዊ መስተዳድሮችም ቅዳሜ በይፋ በታወጀዉ ምክክር የተወከሉት 10 ናቸዉ።በመንግስት ባለሥልጣናት ቋንቋ «የፀጥታ መታወክ» ካለባቸዉ ወይም ግጭት ከሚደረግባቸዉ አካባቢዎች ተሳታፊ መምረጥ ወይም መለየት አልተቻለም።

በምክክሩ ሒደት ሁሉም  ወገኖች አለመካፈላቸዉ የምክክሩን አላማ ገና ከጅምሩ  እንዳይቀጨዉ ማሳሰቡ አልቀረም።አቶ ባይሳ ዋቅወያን በጣም የሚያሳስበዉ ግን ምክክሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወይም ደፈጣ ተዋጊዎች አለማሳተፉ ብቻ አይደለም።ምክክሩ በየአካባቢዉ ከተራዉ ሕዝብ አለመጀመሩ የብሔራዊ ምክክርን አላማና ትርጓሜ፣ የሚታሰበዉን ዉጤም እንዳጨናጉለዉ ያሰጋል-እንደ አቶ ባይሳ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ለብሔራዊ ምክክሩ ተሳታፊዎችን ሻሸመኔ ከተማ ዉስጥ  ሲያስመርጥ
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር የሚሳተፉ የየአካባቢ ተወካዮችን ለመለየት ከተደረጉ ስብሰባዎች አንዱ-ሻሸመኔምስል Sjewangizaw Wegayehu/DW

«13ቱም ክልልሎች በሙሉ ቢሳተፉ፣ ጠቅላላ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በሙሉ ቢሳተፉ፣ የፖለቲካዉን ጥያቄ ፓርት ይፈታሉ እንጂ ---ታች ሔደሕ ትናንት እንደ ሰዉ ያልተቆጠረዉን ሰዉ ስሜት ሳትጠይቅ፣ ይኸ ይኸን ከሥረ መሠረቱ አጥፍተን የምንግባባቸዉ ነገሮች ላይ ተግባብተን፣ በማንግባባቸዉ ላይ ደግሞ ላለመግባባት ተስማምተን ካልቀጠልን----»

 

የኢትዮጵያ ድርብርብ ችግሮች 

 

ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ የምክክር ሂደቱን በይፋ ሲያስጀምሩ እንዳሉት የኢትዮጵያ ታሪክ የዉጊያ ታሪክ ነዉ።ዛሬም ትግራይ የሁለት ዓመት ጦርነት ባስከተለባት መፈናቀል፣ ረሐብና ፖለቲካዊ ቀዉስ ግራ ቀኝ እየተላጋች ነዉ።የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ዉጊያ ላይ ናቸዉ።ጋምቤላ ባለፍ አገደም ግጭት የነዋሪዎችዋን ህይወት፣ ደምና ሐብት እየገበረች ነዉ።በአብዛኛዉ የኢትዮጵያ አካባቢ ዘረፋ፣ እገታ፣ ሥርዓት አልበኝ ነግሷል።

ወጣቶች ሥራ የላቸዉም።ሥራ ያለዉም ከቤቱ በሰላም ወጥቶ መግባቱ አጠራጣሪ ነዉ።የኑሮ ዉድነት፣ ድርቅ፣ ረሐብ ሚሊዮኖችን ተመፅዋች አድርጓቸዉ።ብሔራዊ ምክክር፣ ውይይት፣ ድርድር፣ አብዮት ይባል ሕዝባዊ አመፅ የኢትዮጵያ ሕዝብን ከሞት፣ከሥደት፣ ከረሐብ፣ ሥቃይና ሰቆቃ የሚያላቅቅ መፍትሔ ካላመጣ በርግጥ ሁሉም ከንቱ ነዉ።

አቶ ባይሳ ከአፍቃኒስታን እስከ አፍሪቃ፣ ከቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ እስከ ቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ሪፐብሎኮች የነበሩ ቀዉሶችን በቅርብ አይተዋል፤ አንዳዴም በየመፍትሔዉ ሂደት ወይም ሙከራ ተሳትፈዋል።የኢትዮጵያን ድርብርብ ቀዉስ ለማቃለል አጭሩ መፍትሔ ይላሉ የቀድሞዉ ዲፕሎማት «አላዉቅም»

«ባጭሩ ወንድሜ ነጋሽ መልሱን አላዉቅም።ዛሬ በዛሬ ዘመን ዛሬ ጁን 2፣ ዓለም ላይ ካሉ ችግሮች በጣም የተወሳሰበዉን መፍትሔ ለማስቀመጥም አስቸጋሪ የትኛዉን ብትለኝ የኢትዮጵያ ጉዳይ ነዉ።»

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ዓላማዉን ከሚያስተዋዉቅባቸዉ መልዕክቶች አንዱ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ዓላማዉን ከሚያስተዋዉቅባቸዉ መልዕክቶች አንዱምስል Seyoum Getu/DW

ከችግሩ ዉስብስብነት በላይ በገዢና ተቃዋሚ ፓርቲነት፣ በመንግስትና አማፂነት፣ በሐገር ዉስጥና በስደተኛ ፖለቲከኝነት ወይም ደጋፊነት የተከፋፈሉት ልሒቃንና ተከታዮቻቸዉ አስተሳሰብ፣ በኃይማኖት፣ በጎሳ፣ በጎጥና መንደር የተከፋፈሉት ወገኖች የማይታረቅ የሚመስል አቋም ለሩቁ አይደለም ለቅርቡ ታዛቢ-ለሸምጋይም ግራ ነዉ።

አቶ ባይሳም እንደ ቅርብ ታዛቢ ለኢትዮጵያ ችግሮች መፍትሔዉን «አላዉቅም» ብለዋል።ወደ መፍትሔዉ እንደ መንደርደሪያ ሊሆን የሚችለዉን አንድ ነገር ግን ይጠቁማሉ።

«አንድ ለችግሮች መፍቻ ሳይሆን፣ ለችግሮች መፍቻ መንደርደሪያ መጀመሪያ የሚሆን ነገር ምንድነዉ ጠመንጃን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ አዉጥተን ሰዎች ቁጭ ብለን መነጋገር መቻል አለባቸዉ።ሌላ ምንም የለም።ያ ሲሆን ለመፍትሔዎች የሚሆን መሠረት መገንባት እንጀምራለን።»

ይሆን ይሆን? እንዴት? ደግሞስ መቼ?

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ