1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መንግሥት በኦሮሚያ ክልል ጸጥታ እንዲያስከብር መጠየቁ

ሰኞ፣ ኅዳር 26 2015

በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞኖች ውስጥ ለዓመታት የዘለቀውና በንጹሐን ሰዎች ላይ የሚፈፀመው የጭካኔ ግድያ፣ ማሰቃየት፣ እገታ፣ ማፈናቀል እና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ከሰሞኑ ተባብሶ መቀጠሉ እየተነገረ ነው።

https://p.dw.com/p/4KUvS
Logo des Ethiopian Human Rights Council
ምስል Ethiopian Human Rights Council

ለመንግሥት የቀረበው ጥሪ

መንግሥት በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀመውን ግድያ እና ማፈናቀል ማስቆም ከተሳነው ሀገር ለከፋ አደጋ ውስጥ ልትገባ እንደሚችል ተገለፀ። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው ፖለቲከኛ እና የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪዎች አንድም ተጠያቂነት እንዲሰፍን፣ በሌላ በኩል የሀገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲስተካከል መፍትሔ ያሉትን አመላክተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ካልተደረገ መንግሥትን ብቻ ሳይሆን ሀገርን ጭምር አደጋ ውስጥ የሚጥል ሁኔታ መከሰቱ አይቀርም ሲሉ አስጠንቅቀዋል። 

በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞኖች ውስጥ ለዓመታት የዘለቀውና በንጹሐን ሰዎች ላይ የሚፈፀመው የጭካኔ ግድያ፣ ማሰቃየት፣ እገታ፣ ማፈናቀል እና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ከሰሞኑ ተባብሶ መቀጠሉ እየተነገረ ነው። በክልሉ የተለያዩ የወለጋ አካባቢዎች የአማራ ተወላጆች ላይ እየተፈፀመያለው «ማንነትን መሰረት ያደረገ የዘር ጭፍጨፋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እና እየሰፋ ይገኛል» ያለው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቃ (አብን ) «የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በወለጋ እና ሌሎች አካባቢዎች በንፁሐን አማሮች ላይ እየተፈፀመ ያለውን ጭፍጨፋ፣ ማፈናቀል፣ እገታ እና የንብረት ዝርፊያ ለማስቆም ፍላጎት እና አቅም እንደሌለው በተደጋጋሚ ጊዜ ታይቷል፣ ቀላል የማይባለው የክልሉ መዋቅርም የጭፍጨፋው ተሳታፊና ሽፋን ሰጭ ሆኗል» በማለት ደምድሟል።

Logo | National Movement of Amhara

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በበኩሉ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ ጊዜ በታጠቁ ቡድኖች በዋናነት በሸኔ ታጣቂ ቡድን ጥቃቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን በመግለጽ የፌደራል እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥታት ይህንን ድርጊት እንዲያስቆሙ ፣ የሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች እንዲያከብሩ እና እንዲያስከብሩ በተደጋጋሚ ጊዜ ቢወተውትም ሁለቱ አካላት ለጉዳዩ ተገቢውን በቂ ትኩረት በመስጠት ዘላቂ መፍትሔ ባለማምጣታቸው ጥቃቶች በተደጋጋሚ ጊዜ እየተጸሙ ይገኛል» ብሏል። የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ሥራ አሥኪያጅ አቶ ያሬድ ኃይለማርያም እንደሚሉት የዚህ ሁሉ ጭካኔ የተሞላበት ችግር ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሰብዓዊ መብት ሲጥሱም ሆነ ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲከሰት መከላከል ባለመቻላቸው ተጠያቂ አለመደረጋቸው ነው።
ኦሮሚያ ክልል ታጣቂ ኃይሎች በስፋት የሚንቀሳቀሱበት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ያሬድ መንግሥት ይህንን በኃይልም ይሁን በፖለቲካ ሥራ ማስተካከል እንዳለበት ገልፀዋል።
ከምንም በላይ የመንግሥት አካላት ለእንዲህ ያለው አስከፊ ወንጀል ምንም መግለጫ የማይሰጡ እና ዝምታን የሚመርጡ መሆናቸው ለጉዳዩ ትኩረት የተነፈገው ለመሆኑ እና የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ችግር የመኖሩ ማሳያ መሆኑን ይህም ሰዎች የራሳቸውን የተሳሳተ ድምዳሜ እንዲወስዱ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
የፌደራል መንግሥት በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለውን የዘር ጭፍጨፋ በአስቸኳይ ጣልቃ ገብቶ ማስቆም እና ጥፋተኞች ላይ እርምጃ መውሰድ ይገባዋል ሲል የጠየቀው አብን በክልሉ አመራሮች ላይ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥ እና ችግር ወደተፈጠረባቸው ሥፍራዎች የመከላከያ ሠራዊት በፍጥነት እንዱሰማራም ጠይቋል። የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ዶክተር መራራ ጉዲና መንግሥት ለዚህ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ካልወሰደ ሄዶ ሄዶ ሀገር የሚበትን አደጋ ሊደቅን ይችላል ብለዋል።
ወለጋ ውስጥ ውጊያ እና የተኩስ ድምፅ ዛሬም መኖሩ ተነግራል። በአካባቢው የሚታየው ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለምን አላገኘም የሚለውን ከፌዴራልም ሆነ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥታት መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው ምላሽ አላገኘም። በወለጋ ዞኖች ሸኔ የተባለው ታጣቂ ቡድን አሰቃቂ ግድያዎችን በአካባቢው ነዋሪ የአማራ ተወላጆች ላይ እየፈፀመ መሆኑ ተደጋግሞ ሲገለጽ በተመሳሳይ ጽንፈኛ የተባለ የአማራ ታጣቂ ቡድን በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ግድያ እየፈፀመ መሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተደጋግሞ ይሰማል።

Pro Merera Gudina vorsitzender OFECO
ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ምስል DW/S. Wegayehu

ሰሎሞን ሙጬ 

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ