1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መሐደረ ዜና፣ሁለቱ ጉባኤዎች

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ግንቦት 14 2015

በመጀመሪያዉ የአዉቶሚክ ቦምብ መቶ ሺዎች የተንጨጨሩባት ሒሮሺማ የሰባቱን ስልጡን፣ሐብታም፣ኃያል ሐገራትን መሪዎችን ጉባኤ አስተናገደች።ለሰላም ፈላጊዎች ባደባባይ ሰልፍ እንዳሉት ቡድን ሰባት የተባለዉ ጉባኤ በዚያች በአዉቶሚክ ቦምብ 120 ሺሕ የሚገመት ሕዝብ ባለቀባት ከተማ መደረግ አልነበረበትም

https://p.dw.com/p/4RgCD
G7 Summit in Hiroshima
ምስል Susan Walsh/REUTERS

ሁለቱ ጉባኤዎች

 

 

በግጭት፣ጦርነት፣አመፅና ዉዝግብ የተመሰቃቀለዉ የአረብ ዓለም መሪዎች ጉባኤ ጂዳ-ሳዑዲ አረቢያ ላይ ስለ ሠላም፣መግባባት፣ዕርቅና ልማት እያነሳ ሲጥል፣ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ በኋላ ሰላም፣ዴሞክራሲ፣እኩልነት የሰረፀበት፣ ሐብት፣ዕዉቀት፣ ጉልበት የደለበበት የምዕራቡ ዓለም መሪዎች ጉባኤ የጦርነት ዘግኛኝ ዉጤት ከታየባት ሒሮሺማ ጦርነት፣ መቃቃር፣ መጎነታተልን አፅድቆ አበቃ።የሁለቱ ጉባኤዎች ልዩ እንግዳ የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮልድሚየር ዜሌንስኪ በሐገር-ሕዝባቸዉ ላይ የደረሰና የሚደርሰዉን ግፍ ለየጉባኤተኞች ዘርዝረዉ፣ሩሲያን ወንጅለዉ ሰላም ለማስፈን የሚጥሩትን ግን ለማነጋገር እንኳ «ተጠይፈዉ» ለተጨማሪ ዉጊያ ዛቱ።የሁለቱ ጉባኤዎች ሒደት መነሻ፣ ዉሳኔዎቻቸዉ ማጣቃሻ የዓለም ጉዞ እንዴትነት መድረሻችን ነዉ።ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

የግብፅ፣የኢራቅ፣ የሶሪያ፣ የትራንስ ጆርዳን (ኋላ ዮርዳኖስ) የሊባኖስና የሳዑዲ አረቢያ ሚንስትሮች በ1944 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የአሌክሳንደሪያ ዉል፣ ያሉት ሰነድ በስድስቱ ሐገራት መሪዎች ፀደቀ።የአረብ ሊግ ተመሰረተም።መጋቢት 1945።ካይሮ።

የአሌክሳደሪያዉን ስብሰባ ለመሩት፣ሰነዱን ላስረቀቁና የአምስቱን ሐገራት አቻዎቻቸዉን ላግባቡት ለግብፁ የትምሕርት ሚንስትር ለናጊብ አል-ሒላሊ ፓሻ በርግጥ ታላቅ ደስታ ነበር።ግን ዕዉቁ ምሑር አዲሱን ማሕበር ከማደረጃት ተጨማሪ ስራ እና አዉሮጳን የሚያነደዉን ጦርነት የመጨረሻ ምዕራፍ ከመከታተል ኃላፊነት አላመለጡም።

የአረብ ሊግ ጉባኤተኞች
የአረብ ሊግ ጉባኤተኞችምስል Saudi Press Agency/picture alliance/ASSOCIATED PRESS

አል-ሒላሊ ፓሻና ባልደረቦቻቸዉ ሊጉን የማደራጀት ኃላፊነታቸዉን ማጠናቀቃቸዉን  ለስድስቱ መስራች ሐገራት ተወካዮች ለማስረዳት ስብሰባ ሲጠሩ፣ ሳንፍራንሲስኮ-ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መተዳደሪያ ደንብ ወይም ቻርተር ተፈረመ።ሰኔ 26፣1945።

ደንቡ የዓለም ሰላምን ለማስከበር የቆመ ነዉ መባሉ በሚነገር፣በሚተነተንበት መሐል ግን ሒሮሺማ ላይ የሆነዉ ሆነ።ነሐሴ 6፣1945።በሶስተኛ ቀኑ ናጋሳኪ ተደገመች።

አል-ሒላሊ ፓሻና ባልንጀሮቻቸዉ የመሰረቱት ማሕበር አባል ሐገራት መሪዎች ጂዳ-ሳዑዲ አረቢያ ላይ ጉባኤ ሲቀመጡ፣ በመጀመሪያዉ የአዉቶሚክ ቦምብ መቶ ሺዎች የተንጨጨሩባት ሒሮሺማ የሰባቱን ስልጡን፣ሐብታም፣ኃያል ሐገራትን መሪዎችን ጉባኤ አስተናገደች።ለሰላም ፈላጊዎች ባደባባይ ሰልፍ እንዳሉት ቡድን ሰባት የተባለዉ ጉባኤ በዚያች በአዉቶሚክ ቦምብ 120 ሺሕ የሚገመት ሕዝብ ባለቀባት ከተማ መደረግ አልነበረበትም።የጃፓን የሰራተኛ ማሕበር ተወካይ እንዷ ናቸዉ።

«እኔ ጦርነትን በፍፁም እቃወማለሁ።የኑክሌር ጦር መሳሪያን አጥብቄ እቃወማለሁ።እዚሕ የመጣሁትም ለዚሕ ነዉ።ይሕ ጉባኤ የተደረገዉ የኑክሌር ጦርነት ለማዘጋጀት ነዉ።ስለዚሕ እኛ፣ ማሕበራችን ይሕን ለመቃዉም የምንችለዉን ሁሉ እናደርጋለን።»

የቡድን 7 ጉባኤ የኑክሌር ዉጊያ ስለመግጠም በርግጥ በግልፅ ያለዉ ነገር የለም።ይላል ተብሎም አይጠበቀም።ግጥምጥሞሹ ግን ትንሽ ማስደመሙ አይቀርም።ሐምሌ 17፣ 1945።የሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት አሸናፊ ሐገራት የዩናይትድ ስቴትስ፤የሶቭየት ሕብረትና የብሪታንያ መሪዎች ሰላም ስለሚያሰፍኑበት ስልት ለመነጋገር ፖስትዳም-ጀርመን ዉስጥ ተሰበሰቡ።

 የዩናይትድ ስቴትስን ፕሬዝደንት አጅበዉ በጉባኤዉ ላይ የተካፈሉት የጦር ሚንስትር ሔንሪ ስቲሞን ስለሰላም በሚነጋገረዉ ጉባኤ መሐል የሐገራቸዉ ጦር በአዉቶሚክ ቦምብ ሊመታቸዉ ያቀደዉን ከተሞች ዝርዝር የያዘዘ ሰነድ ጉዳዩን ካጠናዉ ኮሚቴ ተረከቡ።ኃምሌ 23 ነበር።1945።

DW-Karikatur von Sergey Elkin - Wie Russland Sanktion beim Export von Öl umgeht
ምስል DW

ጉባኤዉ ነሐሴ 2 አበቃ።ነሐሴ 6፣ Litel boy «ትንሹ ልጅ» የተባለዉ የዩናይትድ ስቴትስ ቦምብ ሒሮሺማን አነደደ።የሶቭየት ሕብረቱ መሪ ጆሴፍ ስታሊን «የአንድ ሐገር ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የሰላም ጉባኤ ካልተደረገ ሞቸ እገኛለሁ እያለ ከተከራከረ የጦር ሚንስትሩ ለዉጊያ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠርጥር» ያሉት ያኔ ይሆን?

ሆነም አልሆነ ባለፈዉ ሳምንት አርብ ሒሮሺማ ዉስጥ የተደረገዉን ጉባኤ ባደባባይ ሰልፍ ካወገዙት አንዷ በተለይ የአሜሪካዉን ፕሬዝደንት ጦረኛ ይሏቸዋል።

«ባይደን ሂሮሺማ ገብተዋል።የኑኬሌር ሚሳዬል ለመተኮስ ቁልፉን ይዘዉ ነዉ የመጡት።ይቅር ልላቸዉ አልችልም።የሂሮሺማ ሕዝብን ይቅርታ መጠየቅ አለባቸዉ።»

በዩናይትድ ስቴትስ አዉቶሚክ ቦምብ ብዙ ዘመዶቻቸዉ ያለቁባቸዉ የጃፓኑ ጠቅላይ ሚንስር ኪሺዳ ፉምዮ ግን ጉባኤዉ በዚያች ከተማ እንዲደረግ የወሰኑት ዓለም ከኑክሌር ጦርነት ስጋት እንድትላቀቅ በማሰብ ነዉ።ጠቅላይ ሚንስትሩ በጉባኤዉ ማብቂያ በሰጡት መግለጫም ጉባኤተኞች የኑክሌር ጦርነት እንዳይደረግ ቃል መግባታቸዉን አስታዉቀዋል።

«በኑኬሌር ጦርነት አሸናፊ እንደማይኖርና የኑክሌር ዉጊያ መጫር እንደሌለበት ዳግም ቃል ገብተናል።በዚች በአዉቶሚክ ቦምብ በተመታች ከተማ የተሰበሰቡት የቡድን 7 ሐገራት መሪዎች፣ ከቦምቡ ጥቃት የተረፉት ሰዎች ያሉትን ከሰሙ በኋላ የጥፋቱን መጠን፣የሕዝቡን ስሜትና ለሰላም ያለዉን ተስፋ መረዳታቸዉ ታሪካዊ ጠቀሜታ እንዳለዉ ይሰማኛል።»

ጠቅላይ ሚንስትር ኪሺዳ የኑክሌር ጦርነትን ይቃወማሉ።ይሁንና ጃፓን ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲሕ የምታራምደዉን ሰላማዊ መርሕ ያፈረሱ፣የጃፓንን ጦር አዳዲስ ጦር መሳሪያ ያስታጠቁ፣ለጦሩ የሚወጣዉን ገንዘብ ወደ 52 ቢሊዮን ዶላር ያደረሱ፣ የአሜሪካ አልበቃ ብሏቸዉ የብሪታንያን የጦር መርከብ ወደ ሐገራቸዉ የጋበዙ መሪ ናቸዉ።

የኪሺዳዋ ጃፓን በዩክሬኑ ጦርነት ሰበብ ከአዉሮጳና ከሰሜን አሜሪካ መንግስታት ዉጪ በሩሲያ ላይ ማዕቀብ የጣለች ብቸኛዋ ሐገርም ናት።ያስተናገዱት ጉባኤም ለዩክሬን «የማይናወጥ ድጋፉን ለመስጠት ቃል ከመግባት ዉጪ ኪሺዳ «የሕዝብ ተስፋ» ላሉት ሰላም ያሳየዉ ጭላንጭል የለም።የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ጆ ባይደንም ለዩክሬን መንግስት የሚሰጠዉን ድጋፍ ፅናት ለማረጋገጥ ያንዴ ገለፃ አላረካቸዉም።

የጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር ኪሺዳ
የጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር ኪሺዳ ምስል Kohei Choji/AP/picture alliance

«እዚሕ ሒሮሺማ ፕሬዝደንት ዜሌንስኪና ቡድን 7 ተገናኝተን የሩሲያን የጭካኔ ወረራ ለመቋቋም (ከሚፋለመዉ) ከጀግናዉ የዩክሬን ሕዝብ ጎን ለመቆም የገባነዉን የጋራና የማይናወጥ ቃል፣ ልድገመዉ፣ የጋራና የማይናወጥ ቃላችንን በድጋሚ እናረጋግጣለን።»

በጉባኤዉ መሐል ዩናይትድ ስቴትስ በተጨማሪ 71 የሩሲያና ከሩሲያ ጋር ተባባሪ በተባሉ ድርጅትና ኩባንዮች ላይ ማዕቀብ ጥላለች።ለዩክሬን ጦር ተጨማሪ ጦር መሳሪያ ሰጥታለች፣ የዩክሬን ፓይለቶች የዩናይትድ ስቴትስ ተዋጊ ጄቶችን ማብረር እንዲችሉ ለማሰልጠን ቃል ገብታለች።

ደግሞ በተቃራኒዉ ፕሬዝደንት ባይደን የዩክሬኑ ጦርነት የሚቆመዉ በዲፕሎማሲ ነዉ ይላሉ።«ይሕን ጦርነት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በቋሚነት ማስወገድ አስፈላጊ ነዉ።»

ጦርነቱን በዲፕሎማሲያዊ ድርድር ለማስቆም ከዚሕ ቀደም ቱርክ፣ቻይናና ብራዚል ያደረጉት ሙከራ የምዕራባዉያኑን ድጋፍ አላገኘም።የአፍሪቃ መሪዎች ለአዲስ ዲፕሎማሲ እየባተሉ ነዉ።

በሒሮሺማዉ ጉባኤ በተጋባዥነት የተሳተፉት የብራዚሉ ፕሬዝደንት ሉላ ዳ ሲልቫ የተዳፈነ ሙከራቸዉን ለመገላለጥ የዩክሬኑን አቻቸዉን ቮልድሚየር ዜሌንስኪን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘዉ ነበር።«ዜሌንስኪ መጀመሪያ እሺ አሉ፣ ቀጥሎ አይመቸኝም አሉ፣ ቀሩ» አሉ ሉላ።ቀጠሉም።

«ስለሰላም መወያየት የሚቻለዉ ዜሌንስኪና ፑቲን ስለሰላም መወያየት ሲፈልጉ ብቻ ነዉ።በጦርነት መሐል የሰላም ዕቅድ ማዘጋጀት አይቻልም።የምንፈልገዉ መጀመሪያ ጦርነቱ እንዲቆም ነዉ።ጥቃቱ መቆም አለበት።ከዚያ በኋላ በዩክሬንና በሩሲያ መሐል ድርድር እንዲደረግ ንግግር እንጀምራለን።»

ዘጠኝ ሺሕ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘዉ ጂዳሕ ሒሮሺማ ለመድረስ ዕለት ያልፈጀባቸዉ ዜሌንስኪ እዚያዉ ሒሮሺማ ካንዱ ሆቴል ወደ ሌላዉ ለመሔድ ፍላጎት እንጂ «ጊዜ አጡ» ቢባል ዉሸታም ያሰኛል።

የሳዑዲ አረቢያዉ አልጋወራሽ ልዑል መሐመድ ሰልማን የመሩት የአረብ ሊግ ጉባኤ ዘንድሮ የሰላም፤የልማትና መቻቻል መንፈስ ያረበበት መስሏል።ሊጉ ከ12 ዓመት በፊት ከአባልነት ያባረራትን የሶሪያን ዳግም አባልነት ጉባኤዉ አፅድቋል።የሶሪያዉ ፕሬዝደንት በሽር አል-አሰድ በጉባኤዉ ላይ ተካፍለዋል።ሶሪያ ሳዑዲ አረቢያና ግብፅን ከመሳሰሉ ከአረብ ኃያላን ጋር መወዳጀቷን በተለይም በሶሪያዉ ጦርነት ለሰላማዊ ሰዎች መገደል ተጠያቂ የሆኑት አሰድ በጉባኤዉ ላይ መካፈላቸዉን ምዕራባዉያን መንግስታትና የመብት ተሟጋቾች አልፈቀዱትም።

የአሰድ ደጋፊዎች የምዕራባዉያኑን ተቃዉሞና ማስጠንቀቂያ አይቀበሉትም።አንዳዶቹ ደግሞ ከሒሮሺማ እስከ ኢራቅ፣ ከፍልስጤም እስከ ከአፍቃኒስታን፤ ከራስዋ ከሶሪያ እስከ ሰርቢያ ለጠፋና ለሚጠፋዉ ሕይወት መጠየቅ ያለባቸዉ ሲጠየቁ አሰድም አብረዉ ይጠየቃሉ ይላሉ።

የአረብ ሊግ ዋና ፀሐፊ አሕመድ አቡል ጋይት እንዳሉት ደግሞ ሶሪያ ዳግም ሊጉን መቀየጧ የሶሪያዉን ጦርነት በሰላም ለማስቆም፣ችግረኞችን ለመርዳትና ሶሪያን መልሶ ለመገንባት ጠቃሚ ነዉ።የአረብ ፖለቲካ ተንታኝ አብዱል አዚዝ አል ራዚን ግን ለየት ያለ ምክንያት ይጠቅሳሉ።

«የዩናይትድ ስቴትስ መግለጫ አሜሪካ ከመካከለኛዉ ምስራቅ ሐገራት ጋር የተለያ፣ በሶሪያ ላይ  በቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የተቃኘ አቋም እንዳላት ያሳያል።ዩናይትድ ስቴትስ ከጦር መሳሪያ ሽያጭ ጠቀም ያለ ገንዘብ ለማግኘት ስትል የሶሪያዉ ጦርነት እንዲቀጥል ትፈልጋለች።ከቀዉሱ ለማትረፍ የመካከለኛዉ ምስራቅ ምስቅልቅል እንዳይረጋ ትፈልጋለች።»

ከ22ቱ የአረብ ሊግ አባል መንግስታት መሪዎች አብዛኞቹ አምባገነኖች፣ፈላጭ ቆራጮች፣የሕዝብ ድምፅ አፋኞች የሚባሉ ናቸዉ።ኢራቅን፣ሶሪያን፣ሊቢያን\ የመንን፤ አሁን ደግሞ  ሱዳንን በሚያወድመዉና ባወደመዉ ጦርነት በቀጥታ ወይም ምዕራባዉያንን ተከትለዉ ይሳተፋሉ ተብለዉ ይወቀሳሉ።

የሶሪያዉ ፕሬዝደንት በሽር አል አሰድ ከሳዑዲ ባለስልጣናት ጋር
የሶሪያዉ ፕሬዝደንት በሽር አል አሰድ ከሳዑዲ ባለስልጣናት ጋርምስል SANA/REUTERS

የዘንድሮዉ ጉባኤያቸዉ ግን ከሶሪያ ጋር ዳግም ከመቀራረብ ባለፍ፣ ፍልስጤሞችን ትግል ለመርዳት፣  የየምን ተፋላሚ ኃይላት የተፈራረሙትን የሰላም ዉል ለማጠናከርና ሱዳኖችን ለማስታረቅ ቃል ገብተዋል።በጂዳዉ ጉባኤ ላይ የአረቦችን ድጋፍ የጠየቁት የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮልድሚየር ዘለንስኪ ንግግራቸዉን የጀመሩት «በሩሲያ ይጨቆናሉ» ያሏቸዉን የክሬሚያ ታታር ወይም ሙስሊሞችን መሪ ሙስጠፋ ድዤሜሌቭን በማስተዋወቅ ነበር።

የጉባኤዉ የጋራ መግለጫ የመጀመሪያ አንቀፅ ግን «የፍልስጤሞች ጥያቄ አሁንም የአረቦች ማዕከላዊ ጉዳይ» መሆኑን ይጠቅሳል። 

ለሒሮሺማ ጉባኤተኞች ትልቁ ትኩረት ዩክሬንን መደገፍ፣ሩሲያን መቅጣት፣እና ቻይናን ማዉገዝ ነዉ።እንዲያዉም የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ሪሺ ሱናክ እንዳሉት የዩክሬን ጦርነት ከቡድን ሰባትም አልፎ ዓለምን ያሳስባል።

«ከዩክሬን በላይ  ቡድን 7ንና ዓለምን  የሚያሳስብ ነገር የለም።---»ዓለም የትኛዋ ትሆን? አዉሮጳና አሜሪካ፣ ዩክሬን፣ ሱዳን፣አፍሪቃ፣ አረብ ፣ቻይና ወይስ።እርስ በርስ የሚጠላለፉ አባላትን በመያዙ ጥርስና ጥፍር የለዉም የሚባለዉ የአረቦች ማሕበር ዘንድሮ ወደ ሰላም ሲያጋድል፣ የዓለም ኃያል ዲሞክራሲዎች ግን የጡንጫ መፍትሔን እንደ ዋነኛ አማራጭ እያስኬዱት ነዉ።

ነጋሽ መሐመ 

አዜብ ታደሰ