1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕንድ፤ ቻይና እና አፍሪቃ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 18 2008

ካለፈዉ ሰኞ ጀምሮ በሚንስትሮች፤በባለሙያዎችና ባለሐብቶች ደረጃ ኒዉደልሒ-ሕንድ ዉስጥ የሚመክረዉ የአፍሪቃና የሕንድ ስብሰባ ዛሬ በሁለቱ ወገኖች የመሪዎች ጉባኤ ቀጥሏል። የአፍሪቃና የሕንድን ምጣኔ ሐብታዊ ትስስር ለማጠናከር ያለመዉ ስብሰባና ጉባኤ ሲደረግ የዘንድሮዉ ሰወስተኛዉ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1Gwjv
Indien-Afrika-Gipfel in Neu Delhi Gruppenfoto
ምስል Reuters/A. Abidi

[No title]

የሕንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ናሪንድራ ሞዲ አርባ አንድ የአፍሪቃ መሪዎች የተካፈሉበትን ጉባኤ ሲከፍቱ እንዳስታወቁት ሕንድ ለአፍሪቃ የ6መቶ ሚሊዮን ዶላር የልማት ርዳታ ትሰጣለች። የአፍሪቃና የቻይና የምጣኔ ሐብት ጉባኤም ከአንድ ወር በኋላ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።ምጣኔ ሐብታቸዉ በማደግ ላይ የሚገኙት እንደ ሕንድ፤ ቻይና፤ ብራዚል እና ቱርክ የመሳሰሉት ሐገራት የአፍሪቃን ገበያ ለማግኘት ፉክክር የያዙ መስለዋል። በተለይ የሕንድና የቻይና ፉክክር ጠንከር ያለ ነዉ።

Indien-Afrika-Gipfel in Neu Delhi Rede AU Präsidentin Dlamini-Zuma
ምስል Reuters/A. Abidi


ሕንድና አፍሪቃ ዛሪ በመንግሥታት ደረጃ በጀመሩት ጉባኤ ላይ ከ 54ቱ የአፍሪቃ ሃገራት 41 የአፍሪቃ መንግሥታት መገኘታቸዉ ነዉ የተነገረዉ። የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሪንድራ ሞዲ አገራቸዉ የአፍሪቃ የልማት ትብብር አጋር በመሆንዋ ለሕንድ ክብር መሆኑን ተናግረዋል። የሕንድ-አፍሪቃ ግንኙነት ለአፍሪቃ ጠቃሚነቱ ምኑ ላይ ይሆን? ፕሪቶርያ ደቡብ አፍሪቃ የሚገኘዉ የዓለም አቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም ዋና ሥራ አስኪያጅ ጃኪ ሲሊየ እንደሚሉት ሕንድ የቻይናን ያህል የአፍሪቃ የልማት አጋር መሆን አትችልም።
«ሕንድ ከዩኤስ አሜሪካና ከቻይና ቀጥላ በዓለም በኤኮኖሚ የበለፀገች አገር ትመስለኛለች። በሚቀጥሉት ከ20-30 ዓመታት ዉስጥ ሕንድ ቻይና የደረሰችበት የኤኮኖሚ እድገት ደረጃ ትደርሳለች ተብሎ ይጠበቃል። በአፍሪቃና በሕንድ መካከል የንግድ ግንኙነቱ እያደገ ሄድዋል። ቢሆንም ግን ሕንድ ከቻይና በበለጠ የአፍሪቃ የልማት አጋር አትሆንም»
ብሪክስ በሚል አፅጽሮት የሚጠሩት በተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚገኙ አምስት ሃገራት ጉዳይ ተንታኝ አቶ ጌዲዮን ጋሞራ እንደሚሉት፤ ሕንድ፤ ቻይና ከአፍሪቃ ጋር ያላትን ምጣኔ ሐብታዊ ትስስር በማየት ነዉ የጀመረችዉ።

Indien-Afrika-Gipfel in Neu Delhi Rede Modi
ምስል Reuters/A. Abidi


«ይህ አሁን ሲገመገ ሕንድ የቻይና አፍሪቃ ጉባዔን ነዉ በቀጥታ ገልብጠዉ የተጠቀሙት ። በቻይና በጎርጎረሳዊዉ 2000 ዓ,ም ላይ ቤጂንግ ላይ ተካሄደ ከዝያ አዲስ አበባ ቀጠለ፤ ከዛም መልሶ ቤጂንግ ተካሄደ፤ ከዛ ግብጽ ሻርማርሼክ ተካሄደ፤ ከዛ መለሰና ቤጂንግ ተካሄደ ከወር በኋላ ደቡብ አፍሪቃ ላይ ይካሄዳል። ሕንዶቹም እንዲህ አንዴ አፍሪቃ ዉስጥ አንዴ ሕንድ ዉስጥ እያደረጉ እየቀያየሩ ነዉ ጉባዔዉን እያካሄዱ ያሉት። ግን ምንድነዉ እዚህ ላይ ቻይና ያላትን የኤኮኖሚ ጉልበት ሕንድ የላትም። ሕንድ በአፍሪቃ ዉስጥ ልታገኝ የምትችለዉንም ጥቅም ታቃለች። ከአፍሪቃ ብዙ ነገር ማግኘት እንደሚቻል አዉቃለች።»
የዓለም አቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም ዋና ሥራ አስኪያጅ ጃኪ ሲሊየ በበኩላቸዉ ሕንድ ከአፍሪቃ ጋር ያላት ግንኙነት ወደ ንግዱ ያደላ መሆኑን አንስተዋል። ቻይና በበኩልዋ በአፍሪቃ በመንግሥት ደረጃ ከፍተኛ መዋዓለ ንዋይ እንደምታፈስና ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገች መሆንዋን ገልፀዋል።


ብሪክስ በሚል አሕጽሮት የሚጠሩት በተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚገኙ አምስት ሃገራት ጉዳይ ተንታኝ አቶ ጌዲዮን ጋሞራ፤ የሕንድና የቻይና ከአፍሪቃ ሃገራት ጋር አጋርነታቸዉን ማጠናቀራቸዉ የተለያዩ ጠቀሜታን አስገኝቶላቸዋል።
«የቻይኖችና የሕንዶች ወደ አፍሪቃ መምጣት የአፍሪቃን ተፈላጊነት በጣም እንዲጨምር አድርጎታል። ስለዚህ ሌሎቹም እየተወዳደሩ ነዉ ማለት ነዉ»

Indien-Afrika-Gipfel in Neu Delhi Teilnehmer aus Afrika
ምስል Reuters/A. Abidi


እንድያም ሆኖ ይላሉ አቶ ጌዲዮን አፍሪቃ ለዉጭ ሃገራት መዋለ ንዋይ አፍሳሾች መስጠት ያለባትን መለየት ይኖርባታል።
«መጠንቀቅ የሚገባቸዉም ነገር አለ። ሙሉ በሙሉ ራሳቸዉን ከፍተዉ መስጠት የለባቸዉዉም። የራሳቸዉ አገር በቀል ኢንዱስትሪዎች እንዲያድጉ በራሳቸዉ ማስኬድ ይገባቸዋል። በተጨማሪ የዉች መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች አገር ዉስጥ ያሉ ባለሃብቶች ከዉጭ ከሚመጡት ባለሃብቶች ጋር የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር በጋር እንዲሰሩ ማድረግ ይኖርባቸዋል።»
የዓለም አቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም ዋና ሥራ አስኪያጅ ጃኪ ሲሊየ በበኩላቸዉ አፍሪቃ ለእድገትዋ በራስዋ መጣጣር እንዳለባት ነዉ የገለፁት።

አዜብ ታደሰ


ነጋሽ መሃመድ