1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለኦነግ ሸኔ የቀረበው የሰላም ጥሪና ተግባራዊነቱ

ሰኞ፣ የካቲት 13 2015

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በኦሮሚያ ክልል ታጥቆ ለሚንቀሳቀሰው መንግሥት ሸኔ ለሚለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ ለሚጠራው ታጣቂ ቡድን የሰላም ጥሪ አስተላልፏል። ተግባራዊነቱ ግን እያነጋገረ ነው።

https://p.dw.com/p/4Nl7h
Äthiopien | Chaffee Oromia Konferenz
ምስል Seyoum Hailu/DW

ለኦነግ ሸኔ የቀረበው የሰላም ጥሪና ተግባራዊነቱ

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በኦሮሚያ ክልል ታጥቆ ለሚንቀሳቀሰው መንግሥት ሸኔ ለሚለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ ለሚጠራው ታጣቂ ቡድን የሰላም ጥሪ አስተላልፏል። ታጣቂ ቡድኑም መንግሥት ያቀረበውን ጥሪ በአዎንታዊነት መቀበሉን አሳውቆ ሂደቶቹን ግን በጥርጣሬ እንደሚየው አስታውቋል። አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ አንድ ፖለቲከኛ እና የሕግ ባለሞያ እንደሚሉት ጅማሮው አበጀ ቢያስብልም፤ ተግዳሮቶቹ ግን ቀላል አይሆኑም። 

«በማንኛውም ሚዛን ጥሪ ማድረጋቸው መልካም ነው፡፡ መንግሥት ግን በተደጋጋሚ በመጀመሪያም ታጣቂዎቹ ጠመንጃዎችን ያስቀምጡ የሚል ሃሳቡን ያንፀባርቃልና ያ ከሃቀኛ ድርድር የመሸሽ አዝማሚ እንዳይሆን እጠረጥራለሁ። ቁርጠኝነቱ ካለ ግን የተናጠል የተውክስ አቁምና ሌሎችም ምልክቶች ያስፈልጋሉ። ፍረድ ቤት በተደጋጋሚ የፈታቸው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮችም ስማቸው ከታጣቂዎቹ ጋር በመያያዙ አሁንም እስር ቤት ውስጥ ናቸውና መተማመኑ ላይ መስራት የሚያስፈልግ ይመስለኛል።» ያሉት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፕሮፈሰር መረራ ጉዲና ናቸው። ፕሮፈሰር መረራ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየትም ከዚህ በፊትም መንግሥት ከታጣቂዎች ጋር ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን በሰላም እንዲፈታ ማሳሰባቸውን አስታውሰው ጥርጣሬያቸውን ግን አስቀምጠዋል።

«ከዚህ በፊትም ትልቁ ክፍተት መንግሥት በእኛ አገር ልምድ ወደ ሰላማዊ እርምጃ የሚመጣው በኃይል አልሳካ ሲል ወይም ብዙ ጥፋት ከደረሰ በኋላ ነው። አሁንም ቢሆን የመንግሥት ጥሪ በመልካም የሚታይ ቢሆንም ስለቁርጠኝነቱ ለመመስከር ጊዜ ያስፈልጋል ባይ ነን።»

Pro Merera Gudina vorsitzender OFECO
ምስል DW/S. Wegayehu

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ዓርብ እለት በክልሉ ምክር ቤት ጨፌ ኦሮሚያ ፊት ተቀምጠው ባስተላለፉት ጥሪ «ኦነግ ሸነ» ለሚለው ታጣቂ ቡድን በሰላም እንዲገባ ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎ፤ በታጣቂ ቡድኑ በኩልም በተሰጠው ምለሽ ጥሪው አዎንታዊ መሆኑ ተገልጾ፤ ፖለቲካዊ ውይይቶች ከፌዴራል መንግሥት ጋር መሆን እንደሚገባውና በአሸማጋይነትም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተሳትፎ እንዲያደርግ የሚል ምላሽ ነው የተሰጠው። የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያዉ አቶ ባይሳ ዋቅዎያ በዚሁ ላይ በሰጡን አስተያየት የውይይት ተግዳሮቶቹ የሚፈቱ ሆነው አሁን ላይ የሃሳቡ በሁሉም ወገን መመንጨት በራሱ የሚበረታታ ነው ይላሉ። «ጥሪው አስቀድሞም ሲጠበቅ የነበረና አሁንም ጊዜውን ጠብቆ የመጣ ነው፡፡ ግጭት አለ፡፡ ይህ ደግሞ መፈታት የሚችለው በሰላም ስለሆነ ጥሪው መቅረቡም ዘገየ ካልን ነው እንጂ አያስገርምም፡፡ ሁለቱም ወገኖች ለሰላም በጎ አስተያየት መስጠታቸው በራሱ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚስብል ነው።»

የኦፌኮው ሊቀመንበር ፖለቲከኛ መረራ ጉዲና በፊናቸው የድርድር የመፍትሄ ሃሳቡ ወደ ኋላ እንዳይጓተት የአደራዳሪነት ሚናውን የሚጫወተው አካል ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ባይ ናቸው። «አደራዳሪዎቹ መንግሥት ሲልካቸው መጥተው ጥፉ ሲላቸው ደግሞ የሚጠፉ መሆን የለበትም። አሁን ባለው ሁኔታ አይደለም ጨካ ያሉትን እኛ ከተማ ያለነውም አነጋግረው የማሳመን የገለልተኝነት አቋም ያላቸውን አካላት ከአገር ውስጥ ማግኘት አዳጋች ይመስላል። የህዝብ ጥያቄን በሃቅ ለመመለስ ሃቀኛ እርምጃ ያስልጋል።»

ከዚህ በፊት በኦሮሚያ ታጥቆ የሚንቀሳቀሰው መንግሥት ሸነ የሚለው ታጣቂ ቡድን ለመንግሥት ባቀረበው ጥሪ ለሰላም ውይይት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል። የተለያዩ በኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱና ለክልሉ ህዝብ እንቆረቆራለን ያሉ ተቋማት ተመሳሳይ ጥሪ ቢያስተላልፉም መንግሥት ግን ማዕከላዊ አመራር የሌለው በማለት ከታጣቂዎቹ ጋር የመደራደርን ሃሳብ ሲያጣጥል መቆየቱም አይዘነጋም። የሆነ ሆኖ ግን በኦሮሚያ ታጣቂዎቹ በሚንቀሳቀሱባቸው አከባቢዎች ከፍተኛ ማኅበራዊ ቀውሶች በተፈጠረው የተኩስ ልውውጥ መከተሉ እሙን ነው።

 ሥዩም ጌቱ 

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ