1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለእገታ የሚዳረጉት አገር አቋራጭ ሾፌሮች አቤቱታ

ሐሙስ፣ መጋቢት 28 2015

በኢትዮ - ጅቡቲ አውራ ጎዳና መስመር ከመተሀራ እስከ ወለንጭቲ በሚገኝ ስፍራ ላይ ማክሰኛ መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ. ም 17 የአገር አቋራጭ ጭነት መኪና አሽከርካሪዎች ባልታወቁ ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ተሰማ። ታጋቾችን ለማስለቀቅቅም ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚጠየቅ መስማታቸውን ከአሽከርካሪዎች አንዱ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4PnAy
Äthiopien Protest LKW-Fahrer in Bahir Dar
ምስል DW/A. Mekonnen

«የታገቱትን ለማስለቀቅ በሚሊየን ብር ይጠየቃል»

በኢትዮ - ጅቡቲ አውራ ጎዳና መስመር ከመተሀራ እስከ ወለንጭቲ በሚገኝ ስፍራ ላይ ማክሰኛ መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ. ም 17 የአገር አቋራጭ ጭነት መኪና አሽከርካሪዎች ባልታወቁ ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ተሰማ። የአጋቾቹ ድርጊት ከመደጋገሙ በላይ ለማስለቀቂያ በሚል  ለረዳቶች 1 ሚሊዮን ፣ ለአሽከርካሪዎች ደግሞ 1.5 ሚሊዮን ብር እየጠየቁ መሆኑን መስማታቸውን ከአሽከርካሪዎች አንዱ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። በተደጋጋሚ «እገታዎች በሚፈፀሙባቸው አካባቢው ላይ ጥበቃዎች አሉ» የሚሉት አሽከርካሪዎች እገታውን የሚፈፀሙት በ500 ሜትር እና 1 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ጥበቃዎች ባሉበት ሁኔታ መሆኑ ግራ አጋብቶናል ይላሉ። ችግሩን በተመለከተ ጥቆማዎች እንደሚደርሱት ያስታወቀው የፌዴራል ፖሊስ መንገዱ በፌዴራል ፖሊስ እና በመከላከያ ሠራዊት አባላት እንደሚጠበቅ አመልክቶ፣ በአሁኑ ወቅት መንገዱ ሰላም መሆኑን ገልጿል። የአገር አቋራጭ አሽከርካሪዎች የስጋት ድምጽ

የኢትዮጵያ የገቢ ምርትና ሸቀጦች ማጓጓዣ ዋነኛ መሥመር በሆነውና ኢትዮጵያን ከጅቡቲ በሚያስተሳስረው አውራ መንገድ ላይ በአገር አቋራጭ መኪና አሽከርካሪዎች ላይ የሚፈፀመው ግድያ፣ ዝርፊያና እንግልት አለመቆሙ አሽከርካሪዎችን አሳስቧል። በጉዳዩ ላይ ከወራት በፊት በሠራነው ዘገባ ስምንት የአገር አቋራጭ መኪኖች አሽከርካሪዎች በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች ውስጥ በታጣቂዎች እንደተገደሉ እና ሌሎች ሰባት ባልደረቦቻቸው ደግሞ በተፈፀመባቸው ጥቃት የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጾ ነበር። ይህ ችግር መልኩን ቀይሮ ወደ እገታ እና ቤዛ ወይም ማስለቀቂያ ገንዘብ ጥየቃ መሻገሩን ከአሽከርካሪዎች አንዱ አቶ ዓለማየሁ ቤኪሳ ከትናንት በፊት የተፈፀመ ያሉትን በምሳሉ በመጥቀስ ገልፀውልናል።

Äthiopien Straßenblockade in Methara
ምስል DW/Y. Geberegzihaber

ይህንን እና በመንገድ ላይ የሚደርስባቸውን ሌሎች ጥቃቶች ፍራቻ የተወሰኑ አሽከርካሪዎች ከሥራ ገበታ በማይገኙበት ወቅት «አድማ አድርጋችኋል ፣ አመጽ ልታስነሱ ነው ፣ ተልእኮ አላችሁ» በሚሉ ማስፈራሪያዎች ለእንግልት እየተዳረጉ መሆኑንም ያስረዳሉ። ከዚህ አልፎም «ነገሩ የፖለቲካ ትርጉም እየተሰጠው» ላልጠበቁት ችግር እየተጋለጡ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

«አሽከርካሪ ምን ችግር አለበት?» ብሎ የሚያነጋግራቸውና የሚጠይቃቸው የመንግሥት አካል እንደሌለ የሚገልፁት እኒሁ አሽከርካሪ «የመንገዶች ደህንነት ይጠበቅልንና ሥራችንን እንሥራ» የሚል እንጂ ሌላ ጥያቄ የለንም ብለዋል። አክለውም በተለይ ሶማሌ ክልል ላይ ውኃ እና መብራት የመሳሰሉ አገልግሎቶች ችግር ሲገጥማቸው መንገድ የመዝጋት እርምጃ ይወሰዳልም ነው ያሉት። የከባድ መኪና ሾፌሮች ሮሮ 

ስለጉዳዩ ከትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ለማጣራት የተደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም። የፌዴራል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጀላን አብዲ ጥቆማ እንደሚደርሳቸው ገልፀው በአሁኑ ወቅት ግን መንገዱ ሰላም ነው ብለዋል። አሽከርካሪዎቹ የሚደርስባቸውን ችግር ለመገናኛ ብዙኃን በማሳወቃቸው እና ድምፃቸውን በማሰማታቸው ለችግር እየተጋለጡ መሆኑን ገልፀው ይህንን ችግራቸውን ለተለያዩ የፌዴራል መንግሥት አካላት ለማሳወቅ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ወዲህ ወዲያ ሲሉ እንደዋሉ ለማወቅ ችለናል። የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማሕበር ደረቅና ፈሳሽ ጭነቶችን የሚያጓጉዙ ከ25- 30 ሺህ የሚደርሱ ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎችን በሥሩ ማቀፉን ከዚህ በፊት ከማሕበሩ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
 

ሰለሞን ሙጬ 

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶ ስለሺ