1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለአውሮጳ ኅብረት ፈተና የሆነው የሀንጋሪ የወቅቱ የአውሮጳ ኅብረት ፕሬዝዳንትነት

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 16 2016

ኦርባን በጉብኝቶቻቸው በግልጽ የአውሮጳ ኅብረትን እወክላለሁ ባይሉም አንዳንዶች እንደሚሉት ግን የዚያ አይነት ስሜት ለማሳደር ሞክረዋል። የሩስያ ዩክሬን ጦርነት እንዲያበቃ አንድ ነገር መደረግ አለበት በሚለው አቋማቸው አሁን ወደፊት ገፍተዋል። በተአምር ጦርነቱ ያበቃል ብለን መጠበቅ የለብንም ብለዋል። ኅብረቱ ግን እርምጃቸውን ውድቅ አድርጓል ።

https://p.dw.com/p/4iduy
Orban trifft Putin in Moskau
ምስል Valeriy Sharifulin/SNA/IMAGO

ለአውሮጳ ኅብረት ፈተና የሆነው የሀንጋሪ የወቅቱ የአውሮጳ ኅብረት ፕሬዝዳንትነት

 
የሀንጋሪው ፕሬዝዳንት ቪክቶር ኦርባን ሀገራቸው በዙር የሚደርሰውን የአውሮጳ ኅብረት ፕሬዝዳንትነት ከተረከበችበት ጊዜ አንስቶ የወሰዷቸው እርምጃዎች ኅብረቱን አስቆጥቷል። ከሁሉም በተለይ ሃላፊነቱን እንደተረከቡ ያደረጓቸው ጉብኝቶችና ንግግሮች የኅብረቱን የውጭ ፖሊሲ የሚጻረሩ ናቸው ሲል እንደማይቀበለውም አስታውቋል። የአውሮጳ ኅብረት እቅድ እና የሀንጋሪ ተቃውሞ
ሀንጋሪ በዙር የሚደርሰውን የ6 ወራት የወቅቱ የአውሮጳ ኅብረት ፕሬዝዳንት ከተረከበች ወዲህ መሪዋ ቪክቶር ኦርባን ክየቭን ሞስኮን እና ቤጂንግን መጎብኘታቸው እንዲሁም የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕንም ማነጋገራቸውን የአውሮጳ ኅብረት አልተቀበለውም። በነዚህ ጉብኝቶች ኦርባን በክየቭና በሞስኮ መካከል ሰላም ለማውረድ እጥራለሁ ማለታቸው ፣ ለሀንጋሪም ለመላው አውሮጳም ጠቃሚ ባሉት በዚህ ጥረት እንደሚገፉም ማስታወቃቸው ፣ቻይናን በሩስያና በዩክሬን መካከል ሰላም ለማውረድ የቆመች ብቸኛዋ ኃያል ሀገር ሲሉ ማወደሳቸው ኅብረቱን አስቆጥቷል። ምንም እንኳን ኦርባን በጉብኝቶቻቸው በግልጽ የአውሮጳ ኅብረትን እወክላለሁ ባይሉም አንዳንዶች ግን የዚያ አይነት ስሜት ለማሳደር ሞክረዋል ብለው ያምናሉ። በጎርጎሮሳዊው ሐምሌ መጀመሪያ ላይ የአውሮጳ ኅብረትን ወክለው ድርድር እንደማያካሂዱ ኦርባን ተናግረዋል። ሆኖም የሩስያ ዩክሬን ጦርነት እንዲያበቃ አንድ ነገር መደረግ አለበት የሚለውን አቋማቸውን በዚህ የወቅቱ ፕሬዝዳትነት ሃላፊነታቸው ወደፊት ገፍተዋል። ሃላፊነቱን ሲረከቡ እንደተናገሩት የዩክሬንና የሩስያን ጦርነት «እንዲያው ምንም ሳንንቀሳቀስ በተአምር  ያበቃል ብለን መጠበቅ የለብንም ሲሉም መደረግ አለበት ያሉትን ተናግረው ነበር።

Schweizer Friedenskonferenz Josep Borell
ምስል Urs Flueeler/dpa/picture alliance

«ብራሰልስ ቁጭ ብሎ ወደ ሰላም መቅረብ አይቻልም። ምክንያቱም ሰላም በራሱ አይመጣም። ሁሉ ነገር እንዳለ ቀጥሎ አንድ ቀን ድንገት ሰላም ይመጣል ብለን የምናስብ ከሆነ የጦርነትን ባህርይ በተሳሳተ መንገድ ነው የተረዳነው ።ሰላም ለማስፈን ከተሰራ ሰላም ይመጣል። ሆኖም እርምጃ መወሰድ አለበት።ሀንጋሪ ለዚህ ሃላፊነት ልትወስድ አትችልም። ለዚህ አስፈላጊ የሆኑት ስልጣኑም፣ተገቢውም ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ክብደትም ሆነ በቂ ብሔራዊ ዓመታዊ ገቢ ወይም ጦርና ሌሎችም የሉንም።  በእግዚአብሔር ድጋፍ መሣሪያ ልንሆን እንችላለን። »የዩክሬን ቀውስ ሩስያና የምዕራቡ ዓለም ዛቻ 

እናም እነዚህ የኦርባን እርምጃዎችና ንግግሮች በአዲሱ የአውሮጳ ኅብረት የውጭ ጉዳዮች ሃላፊ በካያ ካላስ አስተያየት ኦርባን የሀንጋሪን የኅብረቱ የመሪዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንትነት በመጠቀም በኅብረቱ የዩክሬን ፖሊሲ ላይ ግራ መጋባትን መዝራት ነው ። የኦርባን ጉብኝቶችም ሆነ ንግግሮች ተቀባይነት የላቸውም የሚሉት ተሰናባቹ የአውሮጳ ኅብረት የውጭ ጉዳዮች ሃላፊ ጆሴፕ ቦሬልም  የአውሮጳ ኅብረት ዩክሬንን እንደሚደግፍ ገልጸው ጦርነቱንም በተመድ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት መጨረስ እንፈልጋለን ብለዋል። ኦርባን ከኅብረቱ ፖሊሲዎች ያፈነገጡ ጉብኝቶችን እና ንግግሮችን በወቅቱ የፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው ማካሄዳቸውን ኅብረቱ ዝም ብሎ እንደማያልፈውም ቦሬል ትናንት በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል።

USA Florida 2024 | Viktor Orban trifft Donald Trump in Mar-a-Lago
ምስል Viktor Orban via X via REUTERS

በዚሁ መሠረትም ሀንጋሪ በየዩክሬኑ ጦርነት ላይ በቅርቡ በያዘችው አቋሟ ምክንያት መጪው የኅብረቱ የውጭ ጉዳዮችና የመከላከያ ሚኒስትሮች ስብሰባ ሀንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት ሳይሆን ብራሰልስ እንደሚካሄድ ነው የገለጹት። ለዚህም ምክንያት ያሉትን አስረድተዋል። « ይህ የአውሮጳ ኅብረት ዋነኛ ፖሊሲን የሚጻረር እና የኅብረቱን ፖሊሲ እንደ ጦርነት ፓርቲ ውድቅ የሚያደርግ በመሆኑ አንዳንድ መዘዞችን ሊያስከትል ይገባል። ምልክት መላክ እንዳለብን እረዳለሁ። ተምሳሌታዊ ምልክትም ቢሆን እንደሚመስለኝ ይህን ስሜት ማሳየት  እና የሚቀጥለውን የውጭ ጉዳዮችና የመከላከያ ምክር ቤት ስብሰባዎችን ከእረፍት ስንመለስ ብራሰልስ ውስጥ መጥራት አስፈላጊ ነው።»የዩክሬን ጦርነት በአውሮጳ ያስከተለው የስደተኞች ቀውስ

የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ እንደገለጸው ይህን ዓይነቱን የስብሰባ አጠራር ከመደበኛው አሰራር የተለየ ነው።ይህም  ኅብረቱ ተቃውሞውን የገለጸበትና እንደ ማዕቀብ ሊቆጠር የሚችል እርምጃ ነው ይላል ገበያው። ኦርባን በጎርጎሮሳው ሐምሌ መጀመሪያ ላይ የሰላም ተልዕኮ ብለው በክየቭ ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር ቀጥሎም ወደ ሞስኮ አቅንተው ከሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋርም መነጋገራቸው ፣ከዚያም ወደ ቻይና ብቅ በማለት ከቻይናው ፕሬዝዳንት ከሺ ጂን ፒንግ  ጋርም መወያየታቸው ኅብረቱን በእጅጉ ያስቆጣበት መሰረታዊ ምክንያቶች  እንዳሉት የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ ያስረዳል። 

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ