1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለታላቁ የህዳሴ ግድብ የደን ምንጣሮ 4 ወራት የተሻገረው የክፍያ ጥበቃ

ማክሰኞ፣ መስከረም 24 2015

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ውሀ ሲሞላ የሚተኛበትን ስፍራ ለ3ኛ ዙር የምንጣሮ ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ወጣቶች ስራውን ካጠናቀቁ ከአራት ወራት በላይ ቢሆናቸውም እስካሁን በውላቸው መሠረት ክፍያ እንዳልተፈጸመላቸወ ተናገሩ፡፡ የክልሉ የቴክኒክ እና የስራ ዕድል ፈጠራ ተገቢውን ማጣራት ማጠናቀቁን ገልጿል።

https://p.dw.com/p/4Hj5A
Äthiopien | Stausee Projekt Grand Ethiopian Renaissance Dam
ምስል Eriko Tolosssa

የግድቡ ውሃ የሚርፍበት ቦታ ጽዳት እና የወጣቶች ቅሬታ

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ውሀ ሲሞላ የሚተኛበትን ስፍራ ለ3ኛ ዙር የምንጣሮ ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ወጣቶች ስራውን ካጠናቀቁ ከአራት ወራት በላይ ቢሆናቸውም  እስካሁን በውላቸው መሠረት ክፍያ እንዳልተፈጸመላቸወ ተናገሩ፡፡ ከወረዳ እስከ ክልል የቴክኒክ ሙያና የስራ ዕድል ፈጠራ ኤጀንሲ ድረስ የሰሩበትን እንዲከፈላቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ምላሽ እንዳላገኙ በምንጣሮ ስራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ለዶይቼቨለ ተናግረዋል፡፡ በስራ ቦታ ላይ በህመምና መድሀኒት እጦት የሰው ህይወት ማለፉንም በስራው ላይ የተሳተፉ ወጣቶች ገልጸዋል፡፡ በምንጣሮ ስራ የተሳተፉ ወጣቶች በተደጋጋሚ ጥያቄዎችን እያቀረቡ እንደሚገኙም ጠቁሟል፡፡  የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የቴክኒክ ሙያና የስራ ዕድል ፈጠራ ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ታሪኩ ኩመራ ለተደራጁ ማህበራት ክፍያውን ለመፈጸም አስፈላጊውን ማጣራት ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡

በ3ኛ ዙር የታላቁ ህዳሴ ግድብ  የደን ምንጣሮ ስራ ላይ ከ14 ሺ በላይ ወጣቶች መሳተፋቸውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የቴክኒክ ሙያና የስራ ዕድል ፈጠራ ኤጀንሲ መረጃ ያመለክታል፡፡ በምንጣሮ ስራው ላይ ከመተከል ዞን ወምበራ ወረዳ በኩል ከተሳተፉት መካከል ወጣት ኢርኮ ቶለሳ አንዱ ሲሆኑ ስራውን ካጠናቀቁ ከአራት ወር በላይ ቢሆንም ተገቢውን ክፍያ እንዳተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

Äthiopien | Abholzung von Wäldern für einen Stausee
ምስል Eriko Tolosssa

የምንጣሮ ስራውን በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ በመሆን መስራታቸውን የተናገሩ ሲሆን በወቅቱ በስራ ላይ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው እንዲሆን በመድሐኒት እጦትም ለከፋ ችግር የተጋለጡ መኖራቸውን ወጣቱ አብራርተዋል፡፡ የምንጣሮ ስራውን ለማከናወን በመንግስትና በማህበራት መካከል በተፈረወመው ውል መሰረትም ስራው ከተጠናቀቀ በ15 ቀናት ጊዜ ውስጥ የሰሩበት እንዲከፈላቸው መጠቀሱንም አክለዋል፡፡

በ3ኛ ዙር የህዳሴ ግድብ ደን ምንጣሮ ላይ የተሳፉት ሌላው የመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ  የማህበር ሰብሳብ በተመሳሳይ በሚያዚያ ወር መጨረሻ ስራውን አጠናቀው ቢመለሱም በስራው ለተሳተፉት ማህበራት ክፍያ አለመፈጸሙን ተናግረዋል፡፡ በ45 ቀናት ውስጥ ስራውን ሰርተው ለመመለስ በወቅቱ ወደ ምንጣሮ ስፍራው ቢያቀኑም በርካታ ቀናትን በመንገድ ላይ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ በስፍራው የነበረው ፈጣኝ የአየር ንብረት በመቋቋም በማህበራቸው ጋር ከወረዳው ወደ ስፍራውስራ የነበሩ ከአንድ ሺ በላይ ወጣቶች ክፍያ እንዳልተፈጸመው አመልክተዋል፡፡

Äthiopien | Abholzung von Wäldern für einen Stausee
ምስል Eriko Tolosssa

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የቴክኒክ ሙያና የስራ ዕድል ፈጠራ ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ታርኩ ኩመራ በምንጣሮ ስራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ክፍያ በተገባው ውል መሰረት እንደሚከፈላቸው ተናግረዋል፡፡ በሄክታር የተሰጣቸውን መሬት የመለካት ስራና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዩች ረጅም ጊዜ መውሰዱን ገልጸው ከዛሬ ጀምሮ ለማህበራት  እንደሚከፈልም አክለዋል፡፡

በ2014 ዓ.ም 3ኛው ዙር የምንጣሮ ሥራ ላይ 546 የተደራጁ ማሕበራት (ከ14ሺ በላይ ወጣቶች) 21 ሺ ሄክታር መሬት የደን ምንጣሮ ስራ ላይ መሳተፋቸውን የክልሉ የስራ ዕድል ፈጠራ ኤጀንሲ ከዚህ ቀደም ገልጾ ነበር።

ነጋሳ ደሳለኝ

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ