1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለቀድሞ ተዋጊዎች አቀባበል ተደረገ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 20 2015

ዛሬ በመቐለ ሁሉም ክፍለ ከተሞች በሺዎች ለሚቆጠሩ ከትግራይ ሐይሎች ለተሰናበቱ የቀድሞ ተዋጊዎች ይፋዊ የእንኳን ደህና መጣችሁ ስነስርዓቶች ሲከወኑ ውለዋል። የትግራይ ሐይሎች ዋና አዛዥ ጀነራል ታደሰ ወረደ፣ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት በመጀመርያ ዙር ከ50 እስከ 55 ሺህ የሚሆኑ የቀድሞ ተዋጊዎች መሰናበታቸው ትናንት አስታውቀዋል።

https://p.dw.com/p/4UU2h
Demobilized Tigrayan army members
ምስል Million Hailesialssie/DW

የተበተኑት ተዋጊዎች ድጋፍ አልተደረገላቸዉም

በመቐለ ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ትናንትናና ዛሬ በርካታ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ቀድሞ መኖርያቸው፣ ቤተሰባቸው እየተመለሱ ነው። የቀድሞ ተዋጊዎቹ ማቋቋሚያ የሚሆን እስካሁን የተደረገላቸው ነገር እንደሌለ ይናገራሉ። እነዚህ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ በቀጣይ የማቋቋም ስራ እንደሚከወን ጀነራል ታደሰ ወረደ ተናግረዋል።

በአውቶሞቲቪ ኢንጅነሪንግ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቆ፣ መስፍን ኢንዳስትሪያል ኢንጅነሪንግ በተባለ ተቋም ውስጥ ለዓመታት ሥራ ላይ የነበረው ወጣቱ ኢንጅነር ምሕረትአብ ሙዑዝ፥ ከጦርነቱ መቀስቀስ በኋላ እንደበርካቶች የዕድሜ እኩዮቹ፣ ሕይወቱ አስቦት በማያውቅ መንገድ መቀየሩ ይገልፃል። አንድም ቀን ጠበንጃ የማንገብ ሐሳብ እንዳልነበረው የሚናገሩ ምሕረትአብ፥ ጦርነቱ ከተጀመረ በኃላ «እየሆነ የነበረው ሁሉ አማሮኝ፣ ለትግል በረሃ ወጣሁኝ» በማለት ወደ ትግራይ ሐይሎች መቀላቀሉን የሚያስረዳ ሲሆን፣ በጦሩ መካናይዝ ክፍል ተመድቦም ከሁለት ዓመት በላይ ውግያ ላይ መቆየቱ ይገልፃል። ምሕረትአብ ሙዑዝ ሰሞኑን በይፋ ከትግራይ ሐይሎች ተሰናብተው ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲገቡ እየተደረጉ ካሉ ከ50 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች መካከል አንዱ ነው። ለወጣቱ ኢንጅነር እና የቀድሞ የትግራይ ሐይሎች አባል፥ ጦርነት ቆሞ ሰላማዊ መንገድ መጀመሩ ትልቅ ብስራት ነው።

Demobilized Tigrayan army members
ምስል Million Hailesialssie/DW

 

«የጦርነቱ ግዜ ከባድ ነበር። ግን ደሞ የህልውና ጉዳይ ስለሆነ ግዴታ ነበር። ከነበረው፥ አሁን የተሻለ ሁኔታ አለ። በውግያ የሚመጣ መፍትሔ የለም። ያልተፈለ የሰው እልቂት ነው ያስከተለው። መሰናበቴ ጥሩ ስሜት ነው የፈጠረብኝ» ይላል የቀድሞ ተዋጊው ምሕረትአብ። ሌላው ራሱን «ተጋዳላይ ካሕሳይ ተክለ» ብሎ ያስተዋወቀን የ29 ዓመት ወጣት በበኩሉ፥ ከሁለት ዓመት በፊት የነበረው የግል ስራ ጥሎ የትግራይ ሐይሎችን መቀላቀሉ፥ በጦሩ አርሚ 33 መቆየቱ ነግሮናል።

 

«ሁሉም ታጋይ ወደ በርሃ ሲወጣ እመለሳለሁ የሚል ሀሳብ ይዞ አይደለም የሚሄድ። ግን የዕድል ጉዳይ ከብስል ጥሬ ተመልሰናል። ወደ ወላጆቻችን፣ ቤተሰባችን፣ መንደራችን መመለሳችን አስደስቶናል። እንደምታየው አንፃራዊ ሰላም አለ። ይሁንና ብዙ ነገር ገና ነው። ነፃ ያልወጣ ግዛት አለን። አሁንም ትግል አቆምን ማለት አይደለም። የትግራይ ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎቶች አልተመለሱም» የሚለው ወጣቱ የቀድሞ ተዋጊ ካሕሳይ ተክለ፥ አሁን ላይ ከጦሩ ተሸኝቶ ወደ ቀድሞ ሰላማዊ ሕይወቱ መግባቱ እንዳስደሰተው አክሎ ይገልፃል።

Demobilized Tigrayan army members
ምስል Million Hailesialssie/DW

 

ላነጋገርናቸው ጨምሮ፥ ዛሬ በመቐለ ሁሉም ክፍለከተሞች በሺዎች ለሚቆጠሩ ከትግራይ ሐይሎች ለተሰናበቱ የቀድሞ ተዋጊዎች ይፋዊ የእንኳን ደህና መጣችሁ ስነስርዓቶች ሲከወኑ ውለዋል። የትግራይ ሐይሎች ዋና አዛዥ ጀነራል ታደሰ ወረዳ፣ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት በመጀመርያ ዙር ከ50 እስከ 55 ሺህ የሚሆኑ የቀድሞ ተዋጊዎች መሰናበታቸው ትናንት አስታውቀዋል። የቀድሞ ተዋጊዎች ጉዳይ እንዲከታተል እና እንዲያቋቋም ታስቦ ወደሥራ የገባው የፌደራል መንግሥቱ የተሃድሶ ኮሚሽን ሥራውን በፍጥነት እየከወነ አይደለም ብለው የወቀሱት ጀነራሉ፥ በነርሱ ፍጥነት መሄድ ስለማንችል እና ሰራዊቱ የመበተን ተግባር መጀመር ስላለብን በራሳችን መንገድ መቀነስ ጀምረናል ሲሉ አክለዋል።

ያነጋገርናቸው አሁን ላይ ከጦሩ የተሰናበቱ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ የሚረዳቸው የማቋቋም ስራ እስካሁን አለመከወኑ የሚገልፁ ሲሆን፥ ከጦርነት መልስ በሚጀምሩበት ሰላማዊ ሕይወት የሚረዳቸው ድጋፍ እንዲያገኙም ይጠብቃሉ።

Demobilized Tigrayan army members
ምስል Million Hailesialssie/DW

 

«ሦስት ዓመት ያክል በበርሃ ነበር ስንንከራተት የነበርነው። በእጃችን የያዝነው ነገር የለም። አስተዳደሩ ይሁን ሌላ የሚመለከተው፣ የሥራ ዕድል ሊያመቻችልን አልያም ሁኔታ ሊያመቻችልን እንጠብቃለን። በትግራይ ዳግም ግንባታ ላይ ተሳታፊ መሆን ነው ፍላጎታችን« ካሕሳይ ተክለ ይላል። የቀድሞ ተዋጊዎች መልሶ በማቋቋም ዙርያ የተናገሩት፣ የትግራይ ሐይሎች ዋና አዛዥ ጀነራል ታደሰ ወረዳ፥ ጉዳዮ የትግራይ ህዝብ እና መንግሥት ቀጣይ ትልቅ አጀንዳ ይሆናል ብለዋል።

 

ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን የተባለው ተቋም በቅርቡ እንዳስታወቀው፥ እስከ መጪው ኅዳር ወር ድረስ ባለው 75 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎች የስነልቦናና የሙያ ስልጠና ተሰጧቸው፣ ወደ ሰላማዊ ኑሮአቸው ለመመለስ እየሠራ መሆኑ ይገልፃል። ከነዚህ መካከል 50 ሺህ የሚሆኑ ከትግራይ መሆናቸው ተመላክቷል።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ