1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምዕራብ ኦሮምያው ግጭት እንዲቆም የቀረበ ጥሪ

ሰኞ፣ ግንቦት 21 2015

ድርጅቱ ህዝቡ አሁንም ስለ ሰላም ማንባቱን ያስረዳል፡፡የነቀምቴን ከተማዋ ከአካባቢዋ የተፈናቀሉ አጨናንቀዋታልም ይላል፡፡ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርሰርቲያን የነቀምት አገረስብከት ሃላፊ አባ እስክንድር ከበደ በአከባቢው የተራዘመው ጝጭት እልባት ያገኛል የሚለው ተስፋ ቢያይልም፤ አሁንም መፍትሄው መራቁ ግን ሰቆቃውን እንዳያራዝም አስግቷል ብለዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4RwEH
Ethiopia , Oromia regional state Nekemt city
ምስል Negasa Desalegn/DW

ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የቀረበ የሰላም ጥሪ

በምዕራብ ኦሮሚያ ህዝቡ ግጭት ካስከተለው ሰቆቃ እንዲወጣ ሰላማዊ እልባት እንዲፈለግለት ተጠየቀ፡፡ ሰሞኑን የካቶሊክ ተራድኦ በችግር ላይ ላሉ አብያተክርስቲያናት (Catholic charity Aid to the Church in Need (ACN) የተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ በኢትዮጵያ መንግስት እና ሸማቂ ቡድኖች መካከል የተጀመረው የሰላም ድርድር  ፍሬ እንዲያፈራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል።

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርሰርቲያን የነቀምት አገረ ስብከት ዳይሬክተር አባ እስክንድር ከበደ በተለይም ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት፤ በነቀምቴ ዙሪያ በርካታ ህዝብን ያፈናቀለው ግጭቱ ፣በሁለቱ ተፋላሚ ቡድኖች  ድርድር ያበቃል የሚል ተስፋ ቢያሰንቅም አሁንም ድረስ ግን ግጭት መፈናቀሉ አልተገታም ሲሉ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።

የተራድኦ ድርጅቱ በሰሞኑ ዘገባው በግጭት የተማረረው ህዝብ አሁንም ስለ ሰላም ማንባቱን ያስረዳል፡፡ በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ትልቋ ከተማ በሆነችው ነቀምቴ በስፋት ከዙሪያው የተፈናቀሉ የማህበረሰብ አባላት ከተማዋን አጨናንቀዋታልም ይላል፡፡

አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ ያከሉት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርሰርቲያን የነቀምት አገረስብከት ዳይሬክተር አባ እስክንድር ከበደ በአከባቢው የተራዘመው ግጭት አሁን አሁን እልባት ሊያገኝ ነው መባሉን ተከትሎ የህብረተሰቡ ተስፋ ቢያይልም፤ አሁንም እልባቱ መራቁ ግን የህዝቡን ሰቆቃ እንዳያራዝም አስግቷል ብለዋል፡፡ “ህብረተሰቡ በሰላም እጦት እጅጉን ተሰቃይቷል፡፡ መፍትሄም ይሻል፡፡ ከህዝቡ ባሻገር የሰላም ድርድሩ መጀመሩን ተከትሎ እኛም እንደ ሃይማኖት ተቋም ደስተኞች ነበርን፡፡ ህዝቡ ያለበትን ችግር ስለምንረዳም ድርድሩ አንዳች ተስፋ እንዲያመጣ እንደሃይማኖት ተቋም በፀሎት ፈጣሪን እየተማጸን ነው፡፡ አሁን ተስፋ አድርገን የምንጠባበቀው አማራጭ የሌሌው ሰላም ምንም በማይሳነው ፈጣሪ እውን እንዲሆን ነው፡፡”

መንግስትም ሆነ ታጣቂዎች ለህዝቡ ሲሉ ለሰላም የሚበጀውን እንዲሰሩ የሚጠይቁት እኚህ የሃይማኖት አባት አሁንም ያባራ ግጭት አለመኖሩንም አስረድተዋል፡፡ “ሁለቱ ተደራዳሪ ሃይላት ለሰላም ውይይቱ በተቀመጡ ጊዜ ህዝቡ ተስፋ ነበረው፡፡ አሁን ላይ ግን ግጭቶች ስላሉ ህዝቡ ከተስፋ ወደ ሰቆቃው ተመልሷል፡፡” ይሁንና የሃይማኖት አባቱ የሃይማኖት አባቶችና ተቋማት ተፋላሚዎች መካከል እርቅ ወርዶ ህዝቡ ሰላሙን እንዲያገኝ በቂ ስራ ተሰርቷል የሚል እምነት የላቸውም፡፡ የሃይማኖት ተቋማት በዚህ መካከል ገብተው ሰላምን ማምጣት ከሚችሉበት አቅም በላይ ግጭቱ በመስፋፋቱ እድሉን መጠቀምም ከባድ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

Ethiopia , Oromia regional state Nekemt city
ምስል Negasa Desalegn/DW

የኢትዮጵያ መንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በመካከላቸው ያለውን ልዩነት በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት ከአንድ ወር በፊት በታንዛንያ ዛንዚባር ወደብ የተቀመጡበት ምክክራቸው የመጀመሪያ ምዕራፍ ያለ ምንም እልባት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በኦሮሚያ ያገረሸውን ግጭት ተከትሎም ሁለቱ ተፋላሚ ቡድኖች ጦርነት በማባባስ ሂደቱ አንደኛቸው ሌላኛቸውን ይከሳሉ፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከአንድ ሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ መንግስት የሰላም ሂደቱን በሚጣረስ መልኩ ሠራዊት በማሰማራት መጠነ ሰፊ ጦርነት ከፍቶብኛል ሲል፡ መንግስት በበኩሉ ሰላምና ፀጥታን የማስከበር መንግስታዊ ኀላፊነትን ከመወጣት ያለፈ ማንም ላይ የከፈትኩት ጦርነት የለም ይላል፡፡ የመንግስት ኮሚዩኒኩሽን አገልግሎት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ባለፈው ሳምንት ለዶቼ ቬለ በሰጡት ቃለምልልስ፤ እንደተናገሩት መንግስታቸው ሸነ ያሉት ታጣቂ ቡድን በንብረት እና ሰው ላይ ይፈጽማል ያሉትን ጥቃት የመከላከል ኃላፊነት ብቻ ነው የተወጣው፡፡

መረጃዎች እንዳሳዩት በአሁን ጊዜ በተጠቀሰው አከባቢ 20 ከመቶ የእምነቱ አብያተ ክርስቲያን በጸጥታ ችግር ምክንያት አገልግሎትም አይሰጡም፡፡ የካቶሊካዊት ቤተክርሰርቲያን የነቀምት አገረስብከት ዳይሬክተር አባ እስክንድር ከበደ እንደሚሉት የህዝቡ መከራና ሰቆቃ ሊያበቃ ይገባል፡፡ ይህ የሚሆነውም በተፋላሚ ኃይላቱ መካከል በሚደረስ ስምምነት ነው፡፡ “ህዝቡ ሰቆቃው እንደቀጠለ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እፎይታ አግኝቷል የሚባልበት ጊዜም የለም፡፡ አሁንም እንደ ህዝብም እንደ እምነት ተቋምም ሰላም የሚያመጣ መንገድ እውን ሆናል ብለን ነው ተስፋ የምናደርገው፡፡ ጦርነቱ እንደ እምነት ተቋማም በበርካታ ቤተክርስቲያን እና የልማት ተቋማት ላይ ጉዳት አድርሶብናል፡፡”

ባለፈው ሳምንት ጉባኤን የጨረሰው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስም በአገሪቱ ሰላም የሚወርድበትን መንገድ የሚያግዝ ኮሚቴ ማዋቀሩን ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

ስዩም ጌቱ

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ