1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በፌዴራል ስርዓቱና ህገመንግስቱ ላይ የተደረገ ዳሰሳዊ ጥናት

ዓርብ፣ ኅዳር 7 2016

በኢትዮጵያ ፌዴራል ስርዓት እና ህገመንግስት ላይ ያተኮረው ጥናት ይፋ ሆነ፡፡ አፍሮባሮሜትር የተሰኘው የጥናት ተቋም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ስርዓት እና ህገመንግስት ጉዳይ ላይ ያስጠናውን የትናት ውጤት ነው ዛሬ ይፋ ያደረገው፡፡

https://p.dw.com/p/4Z1qA
ጥናቱን ያደረግ ተቋም ባልደረቦች ማብራሪያ ሲሰጡ
አፍሮባሮ የተባለዉ አጥኚ ተቋም ባልደረቦችምስል Seyoum Getu/DW

«ጥናቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጣን ጊዜ ይገደብ፤ ህገመንግሥቱ ይሻሻል፤ አዲስ አበባ የራስዋ አስተዳደር ታግኝ»

በፌዴራል ስርዓቱና ህገመንግስቱ ላይ የተደረገ ዳሰሳዊ ጥናት
በኢትዮጵያ ፌዴራል ስርዓት እና ህገመንግስት ላይ ያተኮረው ጥናት ይፋ ሆነ፡፡ ዋና መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ አድርጎ በአፍሪካ አቀፍ ደረጃ የህዝብ አስተያየትን መሰረት አድርጎ ጥናቶችን የሚሰራው አፍሮባሮሜትር የተሰኘው የጥናት ተቋም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ስርዓት እና ህገመንግስት ጉዳይ ላይ ያስጠናውን የትናት  ውጤት ነው ዛሬ ይፋ ያደረገው፡፡ ይፋ የሆነውን የጥናቱን ውጤት ለመገናኛ ብዙሃን ያብራሩት የአፍሮባሮሜትር የአፍሪካ ኮሚዩኒኬሽን አስተባባሪ የሆኑት ጋናዊት ማሜ ኢኩያ እና የጥናት ተቋሙ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ አገራዊ አስተባባሪ ሙሉ ተካ ናቸው፡፡ አቶ ሙሉ በዚሁ ለመገናኛ ብዙሃን በተሰጠው መግለጫ እንዳብራሩት ከፌዴራል ስርዓት እና የተማከለ ስርኣት የትኛው የአስተዳደር ስርዓት ተመራጭ ነው የሚለው ጥያቄ ለጥናቱ ታዳሚያን ቀርቦ የፌዴራል ስርኣት የሚለው የተሻለ ብልጫ ያገኘበት ምላሽ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡ “ህገ መንግስቱን እና ፌደራላዊ ስርዓቱን ለማዳን” በትግራይ የተጠራ ጉባኤ

የፌዴራል ስርአት አወቃቀር ድጋፍና ተቃውሞ 


አፍሮ ባሮሜትር በኢትዮጵያ የህዝብ አስተያየትን በማሰባሰብ ለዘጠነኛ ዙር የሰራውን የዳሰሳ ጥናት (Survey) ዛሬ ይፋ ሲያደርግ የጥናቱ ውጤት 54 በመቶ ኢትዮጵያውያን ከተማከለው (አሃዳዊ) የመንግስት መዋቅር ይልቅ የፌዴራል ስርኣት አስተዳደርን ምርጫቸው ማድረጋቸውን ያትታል፡፡ 42 በመቶ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ኢትዮጵያ በተማከለ ስርዓት እንዲትመራ የሚለውን ፍላጎታቸውን ማሳየታቸው ነው የተነገረው፡፡ ቀሪዎቹ መላሾች የትኛውም ቢሆን ግድየላቸውም አሊያም ምርጫቸውን አያውቁም፡፡ ከዚህ ነጥብ አኳያ በዚህ ጥናት መደምደሚያም ኢትዮጵያውያን ከተማከለ የመንግስት ስርዓት ይልቅ ፌዴራላዊ መንግስትን ይመርጣሉ፡፡  

የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ
የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ምስል Eshete Bekele/DW

 

በአዲሱ የአፍሮባሮሜትር የዳሰሳ ጥናት መሰረት ምንም እንኳን ከዚህ ቀደም ከተደረገው የዳሰሳው ጥናት አኳያ በንጽጽር የዚህ አመለካከት ድጋፍ ቢቀንስም፤ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን አሁንም ነጻ የክልል መንግስታት ያለው ፌዴራሊዝም ለአገሪቱ የተሻለው የመንግስት መዋቅር አድርገው ይመለከቱታል፡፡
ከዚህ በፊት ማለትም ከ3 ዓመታት በፊት በጎርጎሳውያን የቀን ቀመር 2020 አፍሮባሮሜትር ይፋ ባደረገው ጥናት መሰረት 61 በመቶ ኢትዮጵያውያን ፌዴራላዊ ስርዓትን ምርጫቸው ሲያደርጉ 37 ከመቶ ብቻ የተማከለ የመንግስታዊ አስተዳደር ለአገራችን የሚበጅ ነው ብለው መርጠው ነበር፡፡
በጥናቱ መሰረት የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም የብሔር ማንነትን (Ethnicity) መሰረት አድርጎ እንደተዋቀረ ይቀጥል ወይስ አከባቢያዊ (Geographical) የፌዴራላዊ ስርኣት ቅርጽ ይኑረው በሚለው ሃሳብ ግን እጅግ ተቀራራቢ ውጤት ነው የተገኘው፡፡ የፌዴራል ስርዓቱ ከቀጠለ ምን መምሰል አለበት በሚለው በዚህ ሃሳብ ላይ መልስ ከሰጡ ኢትዮጵያውያኑ 49 በመቶው አሁን ያለው የብሔር ማንነትን ማዕከል እንዳደረገ ይቀጥል ሲሉ 48 በመቶዎቹ ደግሞ ክልሎቹ በመልከዓምድራዊ ገጽታ እንዲዋቀር እንደሚፈልጉ ነው የገለጹት፡፡ በዚህ ጥናት መሰረት ከዚህ በፊት በዚህ ሃሳብ ላይ በስምንተኛው ዙር በ2012 ዓ.ም. የተደረገው የአፍሮባሮሜትር የጥናት ውጤት እምብዛም ከዚህ ያልራቀ ምላሽ የተገኘበትም ነበር፡፡ 
ስለህገመንግስቱ የጥናቱ ውጤት

ዛሬ ይፋ በተደረገው የአፍሮ ባሮሜትር የጥናት ውጤት መሰረት አብዛኛው ኢትዮጵያውያን አሁን ላይ በተግባር ላይ ያለው የአገሪቱ ህገመንግስታዊ ስርኣት እንዲሻሻል ይፈልጋሉ፡፡ የአፍሮባሮሜትር ኢትዮጵያ አስተባባሪው ሙሉ ተካ “ህገመንግስቱ ይሻሻል፣ ተወግዶ በአዲስ ይተካ ወይስ ባለበት ይቀጥል የሚለው ውዝግብ በልእቃኑ መካከል ሰፊ ውዝግ የሚያስነሳ አንዱ ሃሳብ” መሆኑን አስታውሰው በዚህ የህገመንግስት ማሻሻያ ሃሳብ ላይ ተስማምተው ምላሻቸውን የሰጡ የጥናቱ ተሳታፊዎች “ሁለት ሶስተኛ ወይም 67 በመቶ ገደማ ናቸው” ብለዋል፡፡ ቀሪዎቹ 16 በመቶ መላሾች ህገመንግስቱ ሙሉ በሙሉ ተወግዶ በአዲስ ህገመንግስት እንዲተካ እንፈልጋለን ሲሉ በተመሳሳ 16 በመቶ ያህሎቹ ደግሞ ህገመንግስቱ በፍጹም መነካት የለበትም በማለት ባለበት እንዲቀጥል ሲሉ መልሰዋል፡፡ አፍሮ ባሮሜትር 2012 ዓ.ም. ካስጠናው ዳሰሳዊ ትናት አንጻር ህገመንግስቱ እንዲቀየር እንፈልጋለን ያለሁ አሁን በ5 በቶ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡ 
በህገመንግስት ማሻሻያ በተነሱ አበይት ጉዳዮች ላይ የተሰጡ ምላሾች
አብዛኛው አስተያየት ሰጪዎች የደገፉት የህገመንግስት ማሻሻያ ውስጥ መሰረታዊ በሚባሉ አወዛጋቢ ጉዳዮች ላይም ተለያዩ ፍላጎቶች ተንጸባርቀውበታል፡፡ ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ ሌሎች የስራ ቋንቋዎችን ለፌዴራል መንግስት መጨመር በሚለው ሃሳብ አስፈላጊነት 67 በመቶ የጥናቱ ተሳታፊዎች እስማማለሁ በሚል ነው ምላሻቸውን የሰጡት፡፡ 30 በመቶ ያህሎቹ ደግሞ በፍጹም አሁን በሚሰራበት አማርኛ ቋንቋ ብቻ መቀጠል ያስፈልጋል በሚል ነው ፍላጎታቸውን የገለጹት፡፡ 
ህገመንግስቱ የሚሻሻል ከሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር የስልጣን ዘመን መገደብ አለበት በመሚል ሃሳብ የተስመማሙት ደግሞ 66 በመቶ ናቸው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትርነት የስልጣን ዘመን ሳይገደብ አሁን ባለበት ህገመንግስታዊ አግባብ ይቀጥል ያሉ ደግሞ 27 በመቶ ያህል ዘጎች ናቸው፡፡
የአገሪቱ ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል በማድረግ እንደ ሌሎች ክልሎች ሁሉ እራሱን የቻለ ክልላዊ አስተዳደር የማድረግ ሀሳብን ደግፈው ምላሻቸውን የሰጡት ደግሞ 54 በመቶ የጥናቱ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡ 34 በመቶ ያህሉ አሁን ባለው ሁኔታ መቀጠል ተገቢ ነው ብለው ነው አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡ በ212 ዓ.ም. ይፋ በተደረገው በዚህ ጥናት የአዲስ አበባን ሉዓላዊ ግዛት (ክልላዊ መስተዳድር መዋቅርነትን ሃሳብ) የደገፉ 35 በመቶ ብቻ ነበሩ፡፡

ጥናቱን ያደረገዉ የአፍሮባሮ አርማ
አፍሮባሮ የተሰኘዉ አጥኚ ተቋም አርማምስል Seyoum Getu/DW

የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸውን እድል በራሳቸው የመወሰን የመገንጠል እና የራሳቸውን የክልል መንግስት የመመስረት መብት የሚያረጋግጠውን አንቀጽ 39 መወገድን ሃሳብ ደግፈው ምላሻቸውን የሰጡ የጥናቱ ተሳታፊዎች 46 በመቶ ናቸው፡፡ 47 በመቶዎቹ ደግሞ አንገጹ መነካት የለበትም በማለት ነው የመለሱት፡፡ 
ከሰንደቃላማ ጋር ተያይዘው ለሚነሳውም ውዝግብ ከተሰበሰበው የጥናቱ ተሳታፊዎች ግብረመልስ 29 በመቶ ያህሎቹ ብቻ በባንዲራው መሃል የሚገኘው የኮከብ ምልክት ይወገድ ሲሉ 62 በመቶዎቹ መነካት የለበትም በሚል በአሁኑ ይቀጥል የሚለውን ፍላጎታቸውን አንጸባርቀዋል፡፡  
ስለጥናቱ የገለልተንነት እና አካታችነት ሁኔታ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የተነሳላቸው የጥናቱ ውጤት አቅራቢዎቹ በጥናቱ ከብሔራዊ ስታትክስ የተገኘን ዴሞግራፊ (ስሌቶች) ተወስዶ ሁሉንም የህብረተሰብ አካላት እዲያካተት ጥረት ተደርጓል የሚል ምላሽ ነው የተሰጠው፡፡ 
አፍሮባሮሜትር አፍሪካ ላይ ትኩረት ያደረጉ ገለልተኛ ጥናትና ምርምር የሚሰራ ተቋም ስለመሆኑ የሚገለጽ ሲሆን በዋናነት በዴሞክራሲ፣ አስተዳደርና የኑሮ ጥራት ላይ ታማንና ገለልተኛ አቋምን የሚያንጸባርቅ መረጃዎችን በማሰባሰብ ከ1999 የጎርጎሳውያን ዓመት ጀምሮ በ42 የአፍሪካ አገራት በተለያዩ ዙሮች ጥናት መስራቱ ይነገራል፡፡ 


ሥዩም ጌቱ 
አዜብ ታደሰ 
ታምራት ዲንሳ