1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ስነቃ ራሴን ዓይነ ስውር ሆኜ አገኘሁት»

ዓርብ፣ ነሐሴ 3 2016

ሰዎች በህይወታቸው ብዙ ፈተና ሊገጥማቸው ይችላል። የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት እንግዳችን ግን ከብዙ በላይ ተፈትኗል ማለት ይቻላል። ህይወቱን ሙሉ በሙሉ ስለለወጠው አደጋ እና እንዴት እጣ ፈንታውን ተቀብሎ እየኖረ እንደሆነ ገልፆልናል።

https://p.dw.com/p/4jG0p
መልስ ታዬ በ ማህበራዊ ሳይንስ ሲመረቅ
መልስ ታዬ በ ማህበራዊ ሳይንስ ሲመረቅምስል Privat

«ዓይነ ስውር ሆኜ ራሴን አገኘሁት» መልስ ታዬ

መልስ ታዬ አሳዛኝ ልብ ወለድ የሚመስል ታሪኩን ያካፈለን «ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ» ሲል ጀምሮ ነው።  ጊዜው የካቲት ወር  2010 ዓም ነበር።  በዚህ ወቅት በደብረ ማርቆስ ዩንቨርሥቲ የ3ተኛ ዓመት የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ምህንድስና ተማሪ የነበረው ወጣት አንደኛው ወሰነ ትምህርት ተጠናቆ ተማሪዎች ለዕረፍት የሚወጡበት ጊዜ በመጠቀም ለአንድ ሳምንት ቤተሰቦቹን ለመጠየቅ ወደ ቡሬ ዳሞት ጎጃም የተጓዘው። እቤቱ ሲደርስ ከመሸ ነበር።  እዛም ሁለት ነገሮች ገጠሙት፤ በአንድ በኩል  ታላቅ እህቱ የሴት ልጅ እናት ሆና ጠበቀችው ። በሌላ በኩል ደግሞ ሌላኛዋ እህቱ በጠና ታማ ለሞት እየተጠበቀች ነበር ። እህቱም የዛኑ ሌሊት አረፈች።  «ለዕረፍት የሄድኩት ልጅ ሀዘን ተደግሶ ጠበቀኝ» ይላል መልስ ታዬ። ሀዘኑ ግን በዚህ አላበቃም።  « የካቲት 16 ቀን ነበር። ዓርብ ዕለት ፤ ቤታችን ከአዲስ አበባ ባህርዳር  አልፎ የሚሄደው ዋና መንገድ ፊት ለፊት ነው። እና ብዙ ጊዜ የመኪና አደጋ ይደርሳል። እና ያን ቀንም የሆነው ያ ነው።»

በመኪና አደጋ አይኑን እና ቤተሰቡን ያጣው መልስ

ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ የጎረቤቶቹን ጨምሮ በዚህ ጎዳና ላይ በተደጋጋሚ የመኪና አደጋ ሲደርስ መልስ ተመልክቷል። የአሁኑን ለየት የሚያደርገው የደረሰው አደጋ በእሱ እና በቤተሰቡ ላይ መሆኑ ነው።« መኪናው መንገድ ስቶ መጣ እና መኖሪያ ቤታችን ላይ ነው ጥሶ የገባው። እኔ ተኝታቸለሁ።  እናቴ አለች። የወንድማችን ልጅ፤ አራስ የሆነች እህቴ ከእነ ልጃ ነበረች። በእንደዚህ ሁኔታ እያለን ነው አደጋው የደረሰው። በአደጋው የስድስት ሰው ህይወት የጠፋበት አደጋ ነው ።  ሹፌሩ፣ እናቱ እና እህቱ ሞተዋል። እኛ ጋር የተረፍነው እኔ እና አራሷ እህቴ ብቻ ነን። እኔም የአይነ ስውርነትን ህይወት ጀመርኩ። የህይወቴ ምዕራፍ የተቀየረው እንዲህ ነው። »

መልስ ታዬ ከአደጋው በፊት ቀይ ኮፍያ አድርጎ
መልስ ታዬ ከአደጋው በፊት ምስል Privat
መልስ ታዬ ከአደጋው በፊት
መልስ ታዬ ከአደጋው በፊት ምስል Privat

መልስ ይህንን ሁሉ ያወቀው ለቀናት ኮማ ውስጥ ቆይቶ ከነቃ በኋላ ነው። አይኑን በተመለከተ ማንንም መጠየቅ አላስፈለገውም። « በቃ ማየት ተስኖታል» ይህንን መቀበል ያቃተው እና በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ምንም አይነት ለውጥ እንደማያገኝ የተነገረው ወጣት ጉዳት ከደረሰባት እህቱ በቀር እናቱን ጨምሮ በወቅቱ እቤት ውስጥ የነበሩት ቤተሰቦቹ ስለመሞታቸው የተነገረው ከሆስፒታል ወደ ቡሬ ዳሞት ከተመለሰ በኋላ ነው።  ያኔም ሁሉ ነገር ይመልጥ ጨለመበት። « በቃ ጥፋ ጥፋ አለኝ ግን ወዴት? ልሒድስ ብል እንዴት ብዬ ? አንድ ርምጃ እንኳ ያለሰው መሪነት መንቀሳቀስ የማልችል ሆኜ አርፌዋለው»  ሲል ነው መልስ ከጥቂት አመታት በፊት የተሰማውን ስሜት የገለጸልን « ያን ጊዜ ክብደት ጨምሬያለሁ። ከዛ በመቀጠል ደግሞ በተወሰነ መልኩ ወደ ድባቄ ውስጥ ገብቼ ነበር። ከባድ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት። በቃላት የሚገለፅ አይደለም። ስነቃ አይነ ስውር ሆኜ ነው ያገኘሁት»

ዓይነስውርነት ያልገታው ጥረትና ስኬት

ለ15 ወራት ገደማ ቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ ያሳለፈው እና የህይወት ትርጉሙ የጠፋበት ወጣት ግን  በመጨረሻ ተስፋ አገኘ።  ፈጣሪ  ከወደቁሁበት ትቢያየን አራግፎ አነሳኝ »  የሚለው መልስ የትምህርት መስኩን ከተፈጥሮ ሳይንስ ወደ ማህበራዊ ሳይንስ በመቀየር ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ ሊሆን ችሏል። «በ 2015 ዓ ም ነው በማህበራዊ ሳይንስ የተመረኩት። አሁን መደበኛ የሚባል ስራ እየሰራሁ አይደለም። ግን አሁን በቦሌ ክፍለ ከተማ በሴቶች ህፃናት እና ማህበራት ፅህፈት ቤት ውስጥ ኢንተርንሺፕ እያደረኩኝ ነው። እና ደግሞ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ውስጥ ኃላፊነት አለኝ። እዛ ነው ጊዜዬን እያሳለፍኩ ያለሁት።»

በአሁኑ ሰዓት ከበጎ አድራጎት ስራ ላይ በተጨማሪ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ማዳበር ላይ ያተኮረው መልስ የሚቀጥለው ዓመት መደበኛ ስራ እንደሚጀር ተስፋ ያደርጋል። መልስ በህይወቱ ተመልሶ ተስፋ እንዳይቆር የረዳውንም ነገር አጫውቶናል። በአንድ በኩል የዘመድ አዝማድ ምክር ነበር።  ሌላው ደግሞ የሆነ ጊዜ ላይ  አይነ ስውርነቱን አሜን ብሎ መቀበል መቻሉ ነው። « ከልጅነቴ አንስቶ አዲስ ነገሮች ሲገጥሙኝ ራሴን ከሁኔታው ጋር አላምዳለው። እና ያለፍኩበት ነገር በጣም ከባድ እንደሆነ የገባኝ ሰዎች የሚሰጡኝን አስተያየት ስሰማ ሳይ ነው።»

ስክሪን ሪደር ቴክኖሎጂ

Äthiopien | Das Leben von Melis Taye nach Erblindung
ምስል Privat

መልስ የአይነ ስውራን ፅህፈት ዘዴ የሆነውን ብሬል እስካሁን አልተማረም። ይህም ከእሱ ጋር ከመኪና አደጋው የተረፈችው እህቱ  ወንድሟን ለመርዳት ባደረገችው ጥረት ከአንድ ቴክኖሎጂ ጋር ስለተዋወቀች ነው። « አይነ ስውራን የምንጠቀመው ስክሪን ሪደር የሚባለው ቴክኖሎጂ ስልክ እና ኮምፒውተር ላይ መጫን ይቻላል። ያኔ ማንኛውንም እንቅስቃሴ በድምፅ ይነግረናል። ስንፅፍም እንደዛው ነው። በጋራ የምንማማርበት ከ1300 አባላት በላይ አባላት ያሉት የአይነ ስውራን የቴሌግራም ገጽም አለን። እዛ ላይ ነው የነበረኝን እውቀት ይበልጥ ያዳበርኩት።»

ምንም እንኳን መልስ በቴክኖሎጂ በመታገዝ መፃፍ እና ማንበብ ቢችልም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ራስን ችሎ መንቀሳቀስ ግን አሁንም ትልቅ ፈተናው ነው።« ከልጅነቴ አንስቶ እየለመድኩት የመጣሁት ነገር ስላልሆነ ለእኔ አዲስ እና ከባድ ነበር። መንገዶች ምቹ አይደለም። ለአካል ጉዳተኞች ሁኔታዎች ምቹ አይደሉም እኛ ሀገር። ትግል ነው። በእንደዚህ አይነት ሂደቶች የሚያልፉ ሰዎችን የምመክረው ነገሮችን አምነን መቀበል አለብን። »

የማህበራዊ ሳይንስ ምርቁ መልስ ለጋዜጠኝነት ሙያ ልዩ ፍቅር እንዳለውም ገልፆልናል።  ፍቅር ብቻ ሳይሆንም ለግማሽ ዓመት የዘለቀ የጋዜጠኝነት እና ስነ ፁሁፍ ስልጠና ወስዷል። በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፎ ህይወትን በእራሱ መንገድ እንደ አዲስ የጀመራት የመልስ ታዬ ታሪክ በተለይ ተስፋ ለሚቆርጡ ወጣቶች ተስፋ ሰጪ እንደሚሆን እንገምታለን።

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ