1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ህወሓት የትግራይ ክልላዊ መንግሥትን ወነጀለ

ሰኞ፣ ጳጉሜን 4 2016

በፖለቲካዊ አቋማቸው በአባላቶቼ ላይ ከሓላፊነት የማንሳት፣ የማገድና የማሰር እርምጃዎች በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እየተወሰደባቸው ነው ሲል ህወሓት ከሰሰ። የህወሓት ከፍተኛ አመራር የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እርምጃዎች ሕገወጥ ሲሉ ገልፀዋቸዋል። በሌላ በኩል የህወሓት አባላት እና አመራሮች በሽረ ልያካሂዱት የነበረ የተቃውሞ ሰልፍ ተከልክሏል።

https://p.dw.com/p/4kQE8
አቶ አማኑኤል አሰፋ -  የህወሓት ከፍተኛ አመራር
አቶ አማኑኤል አሰፋ - የህወሓት ከፍተኛ አመራር ምስል Million Hailesialssie/DW

ህወሓት የትግራይ ክልላዊ መንግሥትን ወነጀለ

በፖለቲካዊ አቋማቸው ምክንያት በአባላቶቼ ላይ ከሓላፊነት የማንሳት፣ የማገድ እና የማሰር እርምጃዎች በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እየተወሰደባቸው ነው ሲሉ ህወሓት ከሰሰ። የህወሓት ከፍተኛ አመራር አቶ አማኑኤል አሰፋ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እርምጃዎች ሕገወጥ ሲሉ ገልፀዋቸዋል። በሌላ በኩል የህወሓት አባላት እና አመራሮች በሽረ ልያካሂዱት የነበረ የተቃውሞ ሰልፍ ተከልክሏል።

ከተመሰረተ ሃምሳ ዓመታት ሊሞላው ጥቂት ወራት የቀሩት እና በትግራይ ላለፉትከሰላሳ በላይ ዓመታት ስልጣንን በብቸኝነት ተቆጣጥሮ ያለው ህወሓት፥ የገጠመው ክፍፍል ተከትሎ አሁን ላይ በከፍተኛ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ነው። ለወትሮው ተቃዋሚ ፖለቲካ ፖርቲዎች ያቀረቡ የነበረ አባላቶቼ ታሰሩ፣ ከስራ ተባረሩ፣ ታገዱ የሚል ቅሬታ አሁን ከህወሓት ወገን እየተሰማ ነው። በቅርቡ በተደረገ የህወሓት ጉባኤ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው የተሾሙት አቶ አማኑኤል አሰፋ በሰጡት መግለጫ፥ በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች የህወሓት አባል የሆኑ አመራሮች ከስልጣን የማውረድ፣ ከስራ እና ደሞዝ የማገድ እንዲሁም የማሰር እርምጃዎች በክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር እየተወሰዱ ነው በማለት ገልፀዋል። እንደማሳያ በማለት ደግሞ በአክሱም፣ ሳምረ እንዲሁም በትግራይ ደቡባዊ ዞን ዛታ እና ሰለዋ ወረዳዎች የተደረጉ ባለስልጣናት ከሓላፊነት የማውረድ እርምጃ አንስተዋል። እንደ አቶ አማኑኤል ገለፀ እነዚህ ዒላማ የተደረጉ የህወሓት አባላት፥ እርጃው የተወሰደባቸው በፖለቲካዊ አቋማቸው ብቻ ነው።

አቶ አማኑኤል "ሕገመንግስታዊ አሰራር በመጣስ፥ የከተሞች እና ወረዳዎች አመራር ከሓላፊነታቸው የማንሳት እና የመሾም ሁኔታ እየታየ ነው። እንደምሳሌ በአክሱም የታየ አለ። በተመሳሳይ በደቡብ ምስራቅ ዞን ሳምረ ወረዳ ተመሳሳይ አካሄድ አለ። በደቡባዊ ዞንም ቢሆን በጉባኤ የተሳተፉ የዛታ እና ሰለዋ አመራሮች በቀጥታ ደብዳቤ ባይፃፍም፥ ተነስ አትበለው እንደሚነሳ አድርገው የሚያስብል አካሄድ አለ። በተመሳሳይ በርካታ አመራሮች በፖለቲካ እምነታቸው እና አቋማቸው ምክንያት ታስረዋል፣ ከስራቸው ታግደዋል፣ ደሞዝ ተከልክለው ነው ያሉት። ይህ ሁሉ ሕገወጥ አካሄድ ነው" ብለዋል።

እነዚህ ሕገወጥ የተባሉ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እርምጃዎች ለማረም እየሰራሁ ነውሲል ህወሓት ገልጿል። "እነዚህ ሁሉ ሕገወጥ ተግባራት ለማረም የሚያስችል ስልጣንና ሐላፊነት በፓርቲያችን እና በየደረጃው ባሉ ምክርቤቶች አለ። ስለዚህ ምክርቤቶቹ ያላቸው ሕገመንግስታዊ ስልጣናቸው ተጠቅመው እንዲያያሙት እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ይሰራል። እንደ ፓርቲ ለእንደነዚህ ያሉ ሕገወጥ ተግባራት ምላሽ ለመስጠት ያልቸኮልነው፣ ወዳለው ፖለቲካዊ ትኩሳት ነዳጅ መጨመር ስላልፈለግን ነው" ሲሉ አቶ አማኑኤል ገልፀዋል።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የህወሓት አባላት እና ደጋፊዎች የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እርምጃዎች በመቃወም በሽረ ከተማ ሊያደርጉት የነበረ የተቃውሞ ሰልፍም በከተማዋ አስተዳደር ተከልክሏል። ጳጉሜ 1 ቀን 2016 ዓመተምህረት የሽረ ከተማ አስተዳደር በሽረ ለሚገኘው የህወሓት ፅሕፈት ቤት በፃፈው ደብዳቤ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የቀረበው ጥያቄ ማስተናገድ እንደማይችል የገለፀ ሲሆን፥ ዓመት በዓል መቅረብ እና እየታየ ያለው ፖለቲካዊ ትኩሳት ጥያቄው ላለማስተናገድ ምክንያት ብሎ የከተማዋ አስተዳደር ጠቅሷል። በዚህ እና ተዛማጅ የህወሓት ቅሬታዎች ዙርያ ከትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

 

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ