90 ቀናትን በ90 ቃላት
ሐሙስ፣ ሐምሌ 17 2006«In 90 Words»በ90 ቃላት የተሰኘው ይህ ዘመቻ በፌስቡክና ትዊተር ላይ የኢንተርኔት ጸሐፍቱንና ሶስቱን ጋዜጠኞች 90 የእስር ቀናትበ90 ቃላት የሚያስታውስ ሲሆን የተጀመረው ባለፈው እሁድ ነዉ።
ስድስቱ የዞን ዘጠኝ የኢንተርኔት ጸሐፍቱንናሶስት ጋዜጠኞች በኢትዮጵያ ለእስር ከተዳረጉ ዛሬ ዘጠና ቀናት ሆናቸው፡፡ ከግል ሙያቸው ጎን ለጎን በኢ-መደበኛነት በማህበራዊ ድረ-ገፆች አማካኝነት ዞን ዘጠኝን ከመሰረቱት ወጣቶች መካከል በሌለችበት የተከሰሰችው ሶልያና ሽመልስ አንዷ ናት፡፡
አሁን ስድስቱ የኢንተርኔት ጸሐፍቱንና ሶስት ጋዜጠኞች በጊዜያዊነት ከነበሩበት የፖሊስ የምርመራ ክፍል ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ተዛውረዋል። የተከሳሾች የዋስትና መብት ጉዳይ በሐምሌ 28 ቀጠሮ የሚወሰን መሆኑን ጠበቃ አምሃ መኮንን ይናገራሉ።
በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የኢንተርኔት ጸሐፍቱን ሥራዎቻቸውን የሚዘክር በዘጠና ቃላት የተሰኘ የማህበራዊ ድረ-ገፅ ዘመቻ በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡ የዘመቻው አስተባባሪ ማህሌት ሰለሞን እና ሃሳቡን በመግለፅ የሚሳተፈዉ ጋዜጠኛ ፋሲል ግርማ ዘመቻው የኢንተርኔት ጸሐፍቱንና ጋዜጠኞቹን ለሠሩት ሥራ ለማመስገን እና ለሥራቸውም ዋጋ ለመስጠት ያለመ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ከዛሬ 90 ቀናት በፊት የታሰሩት የኢንተርኔት ጸሐፍቱንናጋዜጠኞች ጉዳይ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ከሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና ዓለም አቀፍ ተቋማትና የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪዎች ከፍተኛ ወቀሳ አስከትሏል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ የታሰሩት በሙያቸው ሳይሆን ከሽብርተኞች ጋር ባላቸው ግንኙነት ነው ማለቱ አይዘነጋም፡፡
እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሰ