1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

50 ዓመታት፦ የኢትዮጵያ አብዮት ውርስ ምንድነው?

እሑድ፣ የካቲት 10 2016

የአጼ ኃይለሥላሴን ዘውዳዊ መንግሥት ከፍጻሜ ያደረሰው የኢትዮጵያ አብዮት 50 ዓመታት ሞላው። የካቲት 1966 “ፈነዳ” የሚባለው አብዮት “መሬት ላራሹ” የተፈከረበት፣ የብሔሮች እና የሐይማኖት ዕኩልነት የተጠየቀበት ነው። ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ ዶ/ር መላኩ ተገኝ እና ዶ/ር ኢዮብ ባልቻ የተሳተፉበት ውይይት የአብዮቱ ውርስ ምንድነው? ሲል ያጠይቃል።

https://p.dw.com/p/4cXJ7
አጼ ኃይለሥላሴ
የአጼ ኃይለሥላሴ ዘውዳዊ መንግሥትን በማስወገድ የፊውዳላዊ ሥርዓትን ከፍጻሜ ያደረሰው የኢትዮጵያ አብዮት የተቀሰቀሰው ከ50 ዓመታት በፊት በየካቲት ነበር። ምስል Paul Almasy/akg-images/picture-alliance

50 ዓመታት፦ የኢትዮጵያ አብዮት ውርስ ምንድነው?

ፊውዳላዊውን የመንግሥት ሥርዓት ለፍጻሜ ያበቃው አብዮት 50ኛ ዓመቱን ሲደፍን ኢትዮጵያ በታሪኳ ጉልህ ሚና የተጫወተውን ኩነት የምትዘክርበት አንዳች መርሐ-ግብር አላዘጋጀችም። አብዮቱ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ በተሳተፉበት የዘመኑ ለውጥ ፈላጊዎች ትዝታ ውስጥ ኹነኛ ቦታ ቢኖረውም በኢትዮጵያ መንግሥት ቸል ከተባለ ዓመታት ተቆጥረዋል። 

ከየካቲት 11 ቀን 1966 ጀምሮ ኢትዮጵያ ተከታታይ ተቃውሞዎች እና የሥራ ማቆም አድማዎች አስተናግዳለች። ጥያቄዎቹም ሆነ የለውጥ ፍላጎቱ ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ይዘት ያላቸው ከመሆናቸው ባሻገር ግፊቱ በየካቲት በረታ እንጂ ቀድሞም የታየ ነበር።

ወቅቱ በባለርስት እና ጭሰኛ መካከል አስከፊ ግንኙነት የዘረጋውን የመሬት ሥሪት በመቃወም “መሬት ላራሹ” የሚለው ጥያቄ ከፍ ብሎ የተፈከረበት ነው። የኃይማኖቶች እና የብሔሮች እኩልነት እንዲከበር፣ የሴቶች መብት እንዲጠበቅ ለውጥ ፈላጊዎች ግፊት አድርገዋል። የታክሲ አሽከርካሪዎች፣ ሠራተኞች፣ መምህራን እና ወታደሮች የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንገብ በየፊናቸው በዘውዳዊው መንግሥት ላይ ጫና ያደርጉ ነበር። 

የአጼ ኃይለሥላሴ ዘውዳዊ መንግሥት ከአብዮት ፊት ለፊት ከመጋፈጡ በፊት የትግራይ፣ የባሌ እና የጎጃምን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ ገበሬዎች ጭሰኝነትን ተቃውመዋል። የኢትዮጵያ ተማሪዎች በ1953 ተሞክሮ ከከሸፈው መፈንቅለ-መንግሥት በኋላ ዘውዳዊውን መንግሥት ወደ ለውጥ የሚገፉ እንቅስቃሴዎች ያደርጉ ነበር። በተለይ በትግራይ እና በወሎ የተከሰተው ረሐብ እና ንጉሣዊው መንግሥት ለመሸሸግ ያደረገው ጥረት ብዙዎችን ያስቆጣ ነው። 

ከአየቅጣጫው ለበረታው ጫና መልስ ለመስጠት ዘገምተኛ የነበሩት አጼ ኃይለሥላሴ “የጦር ኃይሎች፣ የፖሊስ እና የሕዝባዊ ጦር አስተባባሪ ኮሚቴ” በሚል ሥያሜ በተቋቋመው ደርግ ከሥልጣን የወረዱት መስከረም 2 ቀን 1967 ነው። ሥያሜውን ወደ “ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት” የቀየረው ደርግ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እና የመላ ኢትዮጵያ ሶሾሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) ህልውና ያገኙት ከአብዮቱ በተያያዘ ምክንያት ነው። ከዚያ በኋላ መንግሥቱ ኃይለማርያም አምባገነን የሆኑበት ደርግ፣ መኢሶን እና ኢሕአፓን ጨምሮ ንጉሡ ከሥልጣን  ከወረዱ በኋላ ትንቅንቅ የገጠሙ የፖለቲካ ኃይሎች ኢትዮጵያን ከአዲስ የፖለቲካ ባህል አስተዋውቀዋታል።

ለመሆኑ የኢትዮጵያ አብዮት ውርስ ምንድነው? በዚህ ውይይት የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) አባል የነበሩት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እና የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) አባል የነበሩት ዶክተር መላኩ ተገኝ፣ በዩናይትድ ኪንግደም ብሪስቶል ዩኒቨርሲቲ ሥር በሚገኘው ፔሪቮሊ አፍሪካ ጥናት ማዕከል ተመራማሪው ዶክተር ኢዮብ ባልቻ ተሳትፈዋል።

ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ 

እሸቴ በቀለ