አቶ በቀለ ለሐምሌ 20፣አቶ ጃዋር ደግሞ ለሐምሌ 22 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል።
ሐሙስ፣ ሐምሌ 9 2012የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተረኛ የቀጠሮ ችሎት ፖሊስ በአቶ ጀዋር መሐመድ ጉዳይ ላይ የጠየቀውን የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።ዛሬ ያስቻለው ፍርድ ቤቱ፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የፈቀደው ፖሊስ እስካሁን በምርመራ ሂደት የደረሰበትን ደረጃ በማሳወቅ ከወንጀሉ ውስብስብነት አንጻር ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ነው።ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ሪፖርት የአቶ ሃጫሉ ሁንዴሳን አስከሬን አቶ ጃዋር መሐመድ ወደ ኦሮምያ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ባመጡበት ወቅት ከጠባቂዎቻቸው በተተኮሰ ጥይት በአንድ የኦሮምያ ፖሊስ ህይወት ማለፍ ወንጀል እንደጠረጠራቸው ገልጿል።ከዚህ ሌላ ርሳቸው በሚመሩት OMN በተባለው ቴሌቪዥን በተለላለፈ የሁከት እና የአመፅ ጥሪ በተለያዩ የኦሮምያ አካባቢዎች የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን አካልም መጉደሉንና ንብረትም መውደሙን በሪፖርቱ አስታውቋል። የአቶ ጃዋር መሐመድ ጠበቃ አቶ ኢብሳ ገመዳ ክሱን ተቃውመው ለችሎቱ መከራከሪያ ማቅረባቸውን ለዶቼቬለ ተናግረዋል።አቶ ኢብሳ አቶ ጀዋር ከታሰሩ በኋላ በተፈጸሙ ጉዳዮች መከሰሳቸው ተገቢ እንዳልሆነ ፍርድ ቤቱን መሞገታቸውን ተናግረዋል። ፍርድ ቤቱ አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ በ3 መዝገቦች የተጠረጠሩ 17 ሰዎች ጉዳይ ላይ ፖሊስ የምርመራ ቀጠሮ እንዲሰጠው ባቀረበው ጥያቄ ላይም ከ11 እስከ 12 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።በዚሁ መሠረት ፍርድ ቤቱ የእነ አቶ በቀለ ገርባን ጉዳይ ሐምሌ 20 እንዲሁም የእነ አቶ ጀዋር መሐመድን ጉዳይ ሐምሉ 22 ለማየት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ።
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ