1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፈንድቃ በዓለም ሃገራት መድረክ

ሐሙስ፣ ኅዳር 13 2016

ቦታዉ ለባለሃብት ለልማት ተብሎ በስህተት ተሰጥቶ ነበር። ፈንድቃ እየሰራ ያለዉን ነገር አልተረዱም ነበር። ህዝብ ምልከታዉን በሰጠበት ሰዓት፤ የአዲስ አበባ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ፤ ጉዳዩን ሰምተዉ አስጠሩኝ ፤ ችግሩን አስረድቼ፤ አላወቅንም ነበር፤ ይሄማ እንዴት ይሆናል፤ ብለዉ እንዲመለስ ስላደረጉልኝ፤ በኢትዮጵያ ህዝብ ስም አደርሳለሁኝ።

https://p.dw.com/p/4ZMxi
ፈንድቃ የባህል ቡድን
ፈንድቃ የባህል ቡድንምስል Ethio-Colour tradition Band(Fendika)

በዓለም የባህል መድረክ ኢትዮጵያን እያስጠራ ያለዉ ፈንድቃ የባህል ማዕከል

«አንዳንዴ ሃገሪቱ ጦርነት ላይ ነች ተብሎ ሲነገር፤ ሁሉ ነገር ጭልምልም ያለ ይመስላል። ህይወት የቆመ ይመስላል። ያ እንዳልሆነ ሰዉ በዝያም ችግር ዉስጥ፤ ተስፋን ሰንቆ እየሰራ እንዳለ ፈንድቃ አንድ ማሳያ ነዉ ። ፈንድቃን ከገነባሁ በኋላ ዛሬ እንደ በርሊን፤ ሮም፤ ፓሪስ፤ ቶክዮ ፤ ኒዮርክ ፤ ዲሲ ባሉ ከተሞች የፈንድቃን ቅርንጫፍ መክፈት እፈልጋለሁ። አንድ ቀን ይሳካ ይሆናል ብዬም አስባለሁ። ሳይደክመኝ ይጠቀሙብኛል ብዬም አስባለሁ። ፈንድቃ እንደተባለዉ በጥበብ አንድ አድርጎ ህዝብን ሰብስቦ፤ ተስፋ እየሰጠ፤ እና አንድነታችንን እያጠነከረ፤ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ያለ መድረክ ነዉ»

የፈንድቃ የባህል ማዕከል ዋና አስተዳዳሪ እና የባህል አምባሳደሩ የዓለም ሎሬት  መላኩ በላይ ከሰጠን ቃለ ምልልስ የተወሰደን ነዉ። የባህል አምባሳደሩ የዓለም ሎሬት  መላኩ በላይ እና የፈንድቃ አርቲስቶች ብሎም የስዊዘርላንድ ሙዚቀኞች በጋራ የሰሩት የሙዚቃ አልበም ዛሬ ስዊዘርላንድ ዉስጥ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ላይ በይፋ ይመረቃል። ይህ «ጎጆ» የተሰኘዉ የፈንድቃ አዲስ ሲዲ እና ሸክላ በስዊዘርላንድ በዙሪክ ከተማ በሚገኝ ሙድስ ከተባለ የጃዝ ክለብ ጋር ተቀናብሮ የተሰራ መሆኑ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ሙዚቃን በባህላዊ ሙዚቃ መሳርያ አቀናብረዉ ከምዕራባዉያኑ ጃዝ ጋር አወዳጅተዉ ለዓለም ለማዳረስ ጥረት ላይ የሚገኙት ፈንድቃዎች እና አጋሮቻቸዉ በጥበብ ቁልፍ፤ በሙዚቃ የሰላም ድልድይን  በዓለም ዙርያ ለመገንባት የታቀደበት ሥራ መሆኑን ከስዊዘርላን ይፋ የሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ። 

ፈንድቃ የባህል ቡድን በአሜሪካ
ፈንድቃ የባህል ቡድን በአሜሪካ ምስል Ethio-Colour tradition Band(Fendika)

በስዊዘርላንድ ዙሪክ ከተማ ያገኘነዉ የፈንድቃ የባህል ማዕከል ዋና አስተዳዳሪ የዓለም ሎሬት መላኩ በላይ፤ በልምምድ ጊዜ ዉጥረት ዉስጥ ሆኖ ይህን ነግሮናል።

«ፈንድቃ» ባህላዊ ቡድን በጀርመን

«ፈንድቃ ትሪዮ ካዛንችስ ከተባለ የስዊዘርላንድ ባንድ ጋር የቀረጽነዉን የሙዚቃ ሲዴ እና ሸክላ ለማስመረቅ ዝግጅት ላይ ነን የምንገኘዉ። ስዊዘርላንድ ዙሪክ ሙድ የሚባል ቦታ ነዉ ያለነዉ።  ከተለያዩ ባንዶች ጋር ይህን አይነት የጋራ ስንሰራ ብዙ ዓመታትን አስቆጥረናል። ይህ የመጀመርያችን አይደለም። የምናስመርቀዉ ሲዴ« ጎጆ» ይባላል። ከስዊዘርላንድ የጃዝ ባንድ ጋር ነዉ በጥምረት የሰራነዉ። የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ነዉ የሰራነዉ ። የብሔር ብሔረሰቦች ሙዚቃ የትግርኛ፤ የኦሮምኛ ፤ የአማርኛ፤ የኮንሶ ፤ ጉራጌኛ ሁሉ አለዉ። ይህን ሙዚቃ ነዉ ከፈረንጆቹ ጋር በመጣመር የሰራነዉ።»

 ፈንድቃ ኮሮና በሸበበዉ በጀርመኑ የጃዝ መድረክ

ባለፈዉ ሳምንት ጣልያንን ዉስጥ ነበራችሁ። በርካታ የመገናኛ ብዙኃን እንዲሁ በጣልያን በታዋቂዉ እና ጥንታዊ የኦፔራ አዳራሽ ዝግጅቶቻችሁን ማቅረባችሁ ዘግበዋል። ቆይታችሁ እንዴት ነበር?

« ጣልያን ነበርን ። አንድ ፋብሪዚዮ የሚባል የጣልያን ሙዚቀኛ ወዳጆቹን ሰብስቦ ፤ ወደ አስራ አራት ሙዚቀኞች ይሆናሉ፤ እኔ እና ተወዛዋዥ እመቤት ወልደጻድቅን ጋብዘዉ፤ አዲስ በተሰራ የጣልያን ሙዚቃ ላይ የኛን ዉዝዋዜ አሳይተናል። ይህን ዝግጅት ያሳየነዉ በ 15ኛዉ ክፍለ ዘመን በተሰራ በጥንታዊ የኦፔራ አዳራሽ ዉስጥ  ነዉ። ይህ ቦታ በተለይ ዳንስ የሚታይበት ታዋቂ አዳራሽ ነዉ። በእዉነቱ ትልቅ አድናቆትን አግኝተን ነዉ የተመለስነዉ።»  

ፈንድቃ የባህል ቡድን በጣልያን
ፈንድቃ የባህል ቡድን በጣልያንምስል Ethio-Colour tradition Band(Fendika)

በዩናይትድ ስቴትስ የተለያዩ የዓለም የሙዚቃ ጥበቦችን ወደ ሃገሪቱ በማምጣት የሚያስተዋዉቀዉ «ዘ ኬኔዲ ሴንተር»  ዘንድሮ በዓለም ሎሬት መላኩ በላይ የሚመራ እና ዘጠኝ አባላትን የያዘ ኢትዮ ከለር የተባለ የጥበብ ቡድን ከባለፈዉ መስከረም ወር አጋማሽ ጀምሮ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ዝግጅቱን አሳይቷል፤ ከፍተኛ ተቀባይነትንም አግኝቷል። በአሜሪካ መንግሥት በኩል የሚዘጋጀዉ እና 52 ዓመታትን ባስቆጠረዉ በዚህ መድረክ ላይ ኢትዮጵያዉያኑ የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች የሃገር ባህልን አስተዋዉቀዋል።  

ከወራቶች በፊት ካዛንችስ የሚገኘዉ ፈንድቃ የባህል ማዕከል ሊዘጋ ነዉ፤ ቦታዉ ለአንድ ባለሃብት ተሰጥቷል፤ በሚል በርካታ የጥበብ ታዳሚዎችን፤ በዉጭዉም ይሁን፤ በሃገር ዉስጥ ያሉትን አስከፍቶ ነበር፤ እኛም ዘግበን ነበር። ዛሬ ፈንድቃ ከቦታዉ አይነሳምንም ሰምተናል።  ግን ጉዳዩ በምን ተቋጨ?

ፈንድቃ የኪነ-ጥበብ ማዕከል እንዳይፈርስ ጥሪ ቀረበ

«እንዳልሽዉ ጉዳዩ በጣም አነጋጋሪ ሆኖ ነበር። በዝያም አጋጣሚ ለካ ይሄ ሁሉ ህዝብ ከጎኔ የቆመ ነዉ ፤ የፈንድቃ አድናቂ ነዉ የሚለዉን አይቼበታለሁ። ቦታዉ ለባለሃብት ለልማት ተብሎ በስህተት ተሰጥቶ ነበር። ፈንድቃ እየሰራ ያለዉን ነገር አልተረዱም ነበር። ከዝያም ፈንድቃ እንዳይነካ ሲል ህዝብ ሲነሳ እና ምልከታዉን በሰጠበት ሰዓት፤ የአዲስ አበባ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ፤ ጉዳዩን ሰምተዉ አስጠሩኝ ፤ ችግሩን አስረድቼ፤ አላወቅንም ነበር፤ በሚል የሃገር ሃብት መሆኑን ከተረዱ በኋላ ይሄማ እንዴት ይሆናል፤ ብለዉ እንዲመለስ ስላደረጉልኝ፤ ለዚህ ትልቅ ምስጋና በኢትዮጵያ ህዝብ ስም አደርሳለሁኝ። ምስጋናዬን አድርሱልኝ።  

የፈንድቃ የባህል ማዕከል ዋና አስተዳዳሪ እና የባህል አምባሳደሩ የዓለም ሎሬት  መላኩ በላይ
የፈንድቃ የባህል ማዕከል ዋና አስተዳዳሪ እና የባህል አምባሳደሩ የዓለም ሎሬት መላኩ በላይ ምስል Ethio-Colour tradition Band(Fendika)

አዲስ አበባ እንብርት ላይ የሚገኘዉ ይህ ባህል ማዕከል፤ ትልልቅ ሰዎችን፤ ምሁራንን፤ ትንሹን ፤ ብሎም ከፍተኛ የዓለም ባለሥልጣናትን ሁሉ የሚያስተናግድ ቤት ነዉ። ፈንድቃን ከሚጎበኙት እንግዶች መካከል  የአዉሮጳ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት፤ የአፍሪቃ ህብረት ባለስልጣናት፤ የተለያዩ ሃገራት አምባሳደሮች፤ እንዲሁም በቅርቡ የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሃመር ዘና ሲሉ ፎቶ ግራፍ ሲነሱ ታይተዋል።

ከጎዳና ሕይወት በመነሳት ከታዳሚዎች በሚያገኛት የሽልማት ገንዘብ የተማረው እና ሕይወቱን የቀየረው የባህል አምባሳደሩ የዓለም ሎሬት መላኩ በላይ፤ በፈንድቃ የባህል ማዕከል ለሚሰራቸው ስራዎች የኔዘርላንድስ የዘውድ ሽልማት የሆነውን የፕሪንስ ክላውስ 2020 ሎሬት ተሸላሚ መሆኑ ይታወቃል። መላኩ ከኔዘርላንድ ይህን የሎሪት እዉቅናን ያግኝ እንጂ ከጀርመን ፈረንሳይ እና አሜሪካን ጨምሮ ከበርካታ የዓለም ሃገራት መላኩ በላይ በባህል መድረክ ስራዉ፤ በርካታ ሽልማቶችን እና እዉቅናን አግኝቷል።  የባህል አምባሰደሩ የዓለም ሎሬት መላኩ በላይ ለሰጠን ቃለ ምልልስ እያመሰገንን ሙሉ ዝግጅቱን የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲad,ምጡ እንጋብዛለን።   

አዜብ ታደሰ

ዮኃንስ ገብረግዚአብሔር