ጦርነት ኦና ያስቀራት የአፋርዋ አብአላ
አብአላ በትግራዩ ጦርነት ክፉኛ ከተጎዱት የአፋር ከተሞች አንዷናት። ጎረቤታሞቹ የአፋርና የትግራይ ህዝቦች አንዳቸው ሌላኛቸውን በጅምላ ጭፍጨፋ እየከሰሱ ነው።የከተማዋ ከንቲባ ንጹሀን አለአበሳቸው መገደላቸውን ለዶቼቬለ ሲገልጹ አንድ የትግራይ ተወላጅ ደግሞ የአፋር ሚሊሽያዎች በርካታ የትግራይ ተወላጆችን ገድለዋል በማለት ለዶቼቬለ ተናግረዋል።
«ህወሓት ሙሉ በሙሉ ከአብአላ አልወጣም»የአብአላ ከንቲባ
ፊትለፊት ከሚታየው ተራራ ወዲህ ያለችው የዞን ሁለት ርዕሰ ከተማ አብአላ ናት። የህወሓት ኅይሎች ሚያዚያ መጨረሻ ላይ የእርዳታ እህልና ቁሳቁሶች ወደ ትግራይ እንዲገቡ ከአብአላና ከሌሎችም የአፋር አካባቢዎች ለቀው ወጥተዋል ተብሏል።የአብአላ ከተማ ከንቲባ ግን ህወሓት ከአብአላ ሙሉ በሙሉ አልወጣም፤ አሁንም ከተራራው ጫፍ ላይ አሉ ይላሉ።
ሱቆች ተዘርፈዋል፤ወድመዋል
አፋርን ከትግራይ ክልል ወደ ምታዋስነው ወደ ትንሽትዋ አብአላ ከተማ የሚሄድ ማንኛውም ሰው የሚያየው በጦርነት የወደሙና የፈራረሱ ቤቶችን ነው ትላለች ከተማዋን በቅርቡ የጎበኘችው የዶቼቬለዋ ማርየል ሙለር። ከተማይቱ ኦና ሆናለች። በከተማዋ የሚገኙ ሱቆች ተዘርፈዋል ወድመዋል።
በጦርነቱ ከተገደሉት የ58ቱ የመቃብር ስፍራ
የአካባቢው የጤና ባለሥልጣን ሞሐመድ ሐሰን በስፍራው 58 ሰዎች ሲቀበሩ ማገዛቸውን ተናግረዋል። በዚያ ከተቀበሩት ስምንቱ ህጻናት ነበሩ ብለዋል ። የሞቱትም ከባድ መሣሪያ ከላይ ተተኩሶባቸው እንደሆነ እድሜያቸውም ቢያንስ አምስት አራት እስከ ስድስት ዓመት መሆኑን ገልጸዋል።
የተዘረፈው የአብአላ ሆስፒታል
በዞን ሁለት ዋና ከተማ በሆነችው አብአላ የሚገኘው የአብአላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በዞኑ ለሚገኙ ስምንት ቀበሌዎች አገልግሎት የሚሰጥ ሆስፒታል ነበር። ይሁንና ሆስፒታሉ በጦርነቱ ተዘርፏል ፤ከባድ ጉዳትም ደርሶበታል።
የህወሓት ተዋጊዎች በአብአላ በሮችና አጥሮች ላይ የጻፉት
የህወሓት ተዋጊዎች አብአላን ለቀው ቢወጡም በየበሩና አጥሩ ላይ የትግራይ መከላከያ ኃይል በእንግሊዘኛ ምህጻሩ ቲ.ዲ.ኤፍ የሚሉ ጽሁፎች ይታያሉ።
የአብአላ ከንቲባ አቶ ጣሂር ሀሰን
የአብአላ ከተማ ከንቲባ ጣሂር ሀሰን ለዶቼቬለ እንደተናገሩት በጦርነቱ ንጹሀን አለአበሳቸው ተገድለዋል። የህወሓት ኃይሎች ከባድ መሣሪያ እየተኮሱ አብአላ መግባታቸውን የተናገሩት ጣሂር ከተማይቱን ለቀው እስከወጡበት ጊዜ ድረስ ከ225 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ገልጸዋል። ከተገደሉት ውስጥ ቤት ውስጥና በመሸሽ ላይ የነበሩ ሽምግሌዎች ይገኙበታል።
ዦን ቦሳኮ በሰመራ የተመ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ዩ ኤን ኤች ሲ አር ተጠሪ
ዦን ቦሳኮ በሰመራ የተመ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ዩ ኤን ኤች ሲ አር ተጠሪ ናቸው። የትግራይ ተወጆች በሙሉ ከአብአላ ለደኅንነታቸው በሚል ወደ ሰመራ የተፈናቃዮች መጠለያ መወሰዳቸውም እንደሚረዱ ለዶቼቬለ ተናግረዋል። ይሁንና ቦሶኮ በጦርነት መሀል አንድ ቦታ መሰባሰባቸው ለአጸፋ ጥቃት የሚያጋልጥ ነው ብለዋል። በመጠለያው አምስት ህጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 70 ሰዎች በህክምናና በምግብ እጦት ሕይወታቸው ማለፉንም ለዶቼቬለ ተናግረዋል።