1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የተጎጂ ቤተሰቦችን አጽናንተዋል ፡፡

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 20 2016

በአሁኑወቅት የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች በአደጋው ሥፍራ በመገኘት ተጎጂ ቤተሰቦችን እያፅናኑ ፤ የተለያዩ ድጋፎችንም እያደረጉ ይገኛሉ ፡፡ ዛሬ አደጋው በደረሰበት የኬንቾ ሻቻ ቀበሌ የተገኙት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በጎፋኛ ብርታቱን ይስጣችሁ / ታሳ ደንደኣሞ / በማለት ተጎጂዎችን አጽናንተዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4ipDy
Prime Minister Abiy Ahmed visits a village hit by deadly landslide in Gofa zone
ምስል DW

በጎፋ የተጎጂዎች ድጋፍና የጠፉትን ፍለጋ

በጎፋ ዞን ባለፈው ሠኞ በደረሰው የመሬት መደርመስ አደጋ ከናዳ ሥር ተቀብረው የሚገኙ ሰዎችን የማፈላለጉ ጥረት ዛሬም ለስድስተኛ ቀን ሲካሄድ ነው የዋለው፡፡ በዞኑ የገዜ ጎፋ ወረዳ መንግሥት ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው በፍለጋው ከአካባቢው ነዋሪዎች በተጨማሪ በጎ ፍቃደኛ ታራሚዎች ጭምር እየተሳተፉ ይገኛሉ ፡፡
በዛሬው ዕለት ሦስት አስክሬኖች  ተገኝተው ለየቤተሰቦቻቸው መሰጠታቸውን ለዶቼ ቬለ የተናገሩት የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ የዓለም መሪነህ አስፋው “ ፍለጋው በጣም አድካሚና ተስፋ አስቆራጭ ነው ፡፡ ያምሆነ የቤተሰብ አባሎቻቸውን ያላገኙ ነዋሪዎች በቁፋሮው ሥፍራ አዲስ ነገር እየጠበቁ ይገኛሉ ፡፡ አሁንም የቀሪ ሰዎች ፍለጋው እየተካሄደ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡

ዛሬ ሐምሌ 20 ቀን በተካሄደ ቁፋሮ ተጨማሪ የ3 ሰዎች ስከሬን ተገኝቷል።
ዛሬ ሐምሌ 20 ቀን በተካሄደ ቁፋሮ ተጨማሪ የ3 ሰዎች ስከሬን ተገኝቷል።ምስል DW


ያልተገኙ ሰዎች ምን ያህል ይሆናሉ?   
በአደጋው ሥለሞቱትም ሆነ ከናዳው ሥር ተቀብረው በሚገኙ ሰዎችን በተመለከተ እስከአሁን የተለያዩ አኀዛዊ መረጃዎች ሲወጡ ቆይተዋል ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የሟቾቹ ቁጥር እስከ 500 ሊደርስ እንደሚችል ቀደምሲል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል ፡፡
እስከ አሁን በአደጋው ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 231 መድረሱን ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የጠቀሱት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ  “ አደጋው ከደረሰበት ወቅት በትክክል በቦታው የነበሩ ሰዎችን የመለየት ሥራ ተከናውኗል ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 231 አስክሬን ተገኝቷል ፡፡ ተጨማሪ ማጣራት የሚጠይቅ ቢሆንም አሁን አስከሬናቸው ያልተገኙ ሰዎች ቁጥር 18 መሆናቸውን ያሳያል ፡፡ ቀሪ ሰዎችን የማፈላለጉ ሥራ በነገው ዕለትም የሚቀጥል ይሆናል “ ብለዋል ፡፡

 በጎፋ ዞን ኬንቾ ሻቻ ቀበሌ አደጋው የደረሰበት ቦታ
በጎፋ ዞን ኬንቾ ሻቻ ቀበሌ አደጋው የደረሰበት ቦታምስል DW


የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማጽናኛ መልዕክት
በአሁኑወቅት የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች በአደጋው ሥፍራ በመገኘት  ተጎጂ ቤተሰቦችን እያፅናኑ ፤ የተለያዩ ድጋፎችንም እያደረጉ ይገኛሉ ፡፡ ዛሬ አደጋው በደረሰበት የኬንቾ ሻቻ ቀበሌ የተገኙት ጠቅላይ ሚንስትር  ዐብይ አህመድ በጎፋኛ ብርታቱን ይስጣችሁ / ታሳ ደንደኣሞ / በማለት ተጎጂዎችን አጽናንተዋል፡፡
በጎፋው መሬት መንሸራተት አደጋየሟች ቤተሰቦችን ለመደገፍየክልሉ መንግሥት ጥሪ ማድረጉን ተከትሎ  አሁን ላይ የክልል መንግሥታት  ፣ ግለሰቦች ፣ ተቋማት ፣ የጎረቤትና ወዳጅ አገራት የተለያዩ ድጋፎችን እያበረከቱ ይገኛሉ ፡፡
ዛሬ ማለዳ ደግሞ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ለአደጋው ተጠቂዎች ድጋፉ  75 ቶን ምግብ ነክና ሌሎች  የሰብዓዊ  ቁሳቁሶች ድጋፍ የላከ ሲሆን የከልል መንግሥታትም የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፎችን እያደረጉ ይገኛሉ ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር