1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግብጽ ባንዳ ሲሉ የጠሯቸውን የውስጥ ኃይሎች በመጠቀም ግጭት እንዲፈጠር እየሰራች ነው

ቅዳሜ፣ ጳጉሜን 2 2016

"ሁለት መቶ እና ሁለት መቶ ሃምሳ አመት እድሜ ያለው ፣ ትናንትና የተፈጠሩ ዛሬ እኛን እንደፈለጉ ያደርጉናል ። ቁጭ በል ፣ ብድግ በል ፣ ወደ ቀኝ እና ግራ ዙር እያሉን ነው" ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

https://p.dw.com/p/4kOSw
Äthiopien I Äthiopische Verteidigungskräfte bei der Feier des 47. Jahrestages
ምስል Mesay Teklu/DW

"ግብጽ ወረራ ልትፈፅምብን አትችልም"

የኢፌድሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ  "የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ናት" ያሏትን ግብጽ  ባንዳ ሲሉ የጠሯቸውን የውስጥ ኃይሎች በመጠቀም ግጭት እንዲፈጠር እየሰራች ነው ሲሉ ተናገሩ።

በቅርቡ "ግብፅሞቃዲሾ ስለመጣ ወደ ኢትዮጵያ ወረራ ይፈፅማል ብሎ የሚያስብ ካለ ሞኝ ነው ፤ አያደርጉትም እነሱ በእጅ አዙር ሊዋጉ ይፈልጋሉ" ያሉት ኤታማዦር ሹሙ "በእጅ አዙርም ይምጣ በቀጥታም ይምጣ የኢትዮጵያ አቅም አሁን ከባድ ነው"  ብለዋል።

ኤታማዦር ሹሙ ይህን ያሉት መቀመጫውን ሀረር ከተማ ያደረገው የምስራቅ ዕዝ አርባ ሰባተኛ አመት ምስረታን አስመልክቶ ትናንት  በሀረር ከተማ በየካሄደ የዕዙን ታሪክ የሚዘክር የመፅሀፍ ምረቃ በተከናወነበት መድረክ ነው።

በሀረር ከተማ የምስራቅ ዕዝን የጦር ሜዳ እና ተያያዥ ታሪክ በሚያትተው መፅሀፍ ምረቃ ላይ ትናንት ዘለግ ያለ ንግግር ያደረጉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ብርሀኑ ጁላ የረዥም ዘመን ታሪክ ያላት ሀገር እርስ በእርስ በመታኮስ ማሳለፏ የረባ ነገር እንዳይኖራት በማድረግ  ሀገሪቱ በግጭት ውስጥ እንድትቆይ አድርገዋል ካሏቸው  ታሪካዊ ጠላቶች ካሏቸው መክከል ግብፅን በመጥቀስ "የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ናት" ብለዋል።

"ግብፅ ሞቃዲሾ ስለመጣ ወደ ኢትዮጵያ ወረራ ይፈፅማል ብሎ የሚያስብ ካለ ሞኝ ነው ፤ አያደርጉትም" ሲሉም ተደምጠዋል ኤታማዦር ሹሙ።

ሀገሪቱ ወደ ኖርማላይዜሽን እንድትመጣ አሁንም ትግል ስላለ ሰራዊቱ መዘናጋት አያስፈልግም ያሉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዡ የሀገሪቱ ህዝቡም "የኢትዮጵያን ሁኔታ በደምብ መረዳት አለበት በደምብ አልተረዳም" ብለዋል።

 በሀረር በተከናወኑ መርሀ ግብሮች የተገኙት የኤፌድሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ብርሀኑ ጁላ ሰሞንኛ ውጥረት በሆነው የሶማሊያ - ግብፅ - ኢትዮጵያ ጉዳይ ጠንከር ያሉ መልዕክቶችን ሲያነሱ ተደምጠዋል
በሀረር በተከናወኑ መርሀ ግብሮች የተገኙት የኤፌድሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ብርሀኑ ጁላ ሰሞንኛ ውጥረት በሆነው የሶማሊያ - ግብፅ - ኢትዮጵያ ጉዳይ ጠንከር ያሉ መልዕክቶችን ሲያነሱ ተደምጠዋልምስል Mesay Teklu/DW

የዚያድባሬ ጦር በኢትዮጵያ ላይ የፈፀመውን ወረራ ለመቀልበስ በወቅቱ  በተወሰዱ እርምጃዎች የተመሰረተው የምስራቅ ዕዝ በጅግጅጋ እና ሀረር ከተሞች አርባ ሰባተኛ አመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ መርሀ ግብሮች እያከበረ ይገኛል።

በዛሬው እለትም በሀረር ከተማ ስታድየም የዕዙ ምስረታ በዓል ማጠቃለያ ዝግጅት የሀገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ሹሞች እንዲሁም የሀረሪ ክልል እና የድሬደዋ መስተዳድር  ባለስልጣናት እና  የአካባቢው ህብረተሰብ በተገኙበት ተከብሯል።

ትናንት በሀረር በተካሄደው መድረክ ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ምን አሉ?

በዓለም የረዥም ዘመን ታሪክ አላት የምንላት ሀገር አሁን ያለችበትን ሁኔታ ያነሱት የኢፌድሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ብርሀኑ ጁላ በነዚህ ዘመናት ምንድን ነው የሰራነው? ብለን ልንጠይቅ ይገባል ብለዋል።

"ሁለት መቶ እና ሁለት መቶ ሃምሳ አመት እድሜ ያለው ፣ ትናንትና የተፈጠሩ ዛሬ እኛን እንደፈለጉ ያደርጉናል ። ቁጭ በል ፣ ብድግ በል ፣ ወደ ቀኝ እና ግራ ዙር እያሉን ነው" ሲሉ በቁጭት ገልፀዋል።

"እንደዛ የሆነው ስላልሰራን ነው ።ያልሰራነው ደግሞ ስንዋጋ ስለኖርን ነው። አጀንዳችን  መታኮስ መዋጋት ነው" ያሉት ፊልድ ማርሻል  ከዚህ ግጭት በስተጀርባ ደግም "ታሪካዊ ጠላቶች አሉን፤ በተለይ ግብፅ ለምን እንደምንፈራ አላውቅም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ናት" ነው ያሉት።

"እኛን በማዳከም በታሪካችን በሙሉ ሁሉንም ስራ የሰሩት እነሱ (ግብፆች) ናቸው ። ከባህር እንድንርቅ ያደረጉ ፣ የተለያዩ ኃይሎችን በሀገር ውስጥ የተለያዩ ኃይሎችን የፈጠሩ ፣ ከለውጥ በኃላ በሰሜን ኢትዮጵያ ለነበረው ግጭት መሳሪያ ሲያቀብሉ እነሱ ናቸው " ሲሉ ወቅሰዋል።

"ኢትዮጵያ ወደ ኖርማላይዜሽን የምትገባው ገና ነው ። አሁንም ትግል አለ ስለዚህ መዘናጋት አያስፈልግም" በማለት ሰራዊቱ "መሰልጠን ፣ መግባባት ፣ ሰራዊት መገንባት ፣ስራዊት ማብዛት ፣ መታጠቅ እና ቆቅ መሆንም ያስፈልጋል " ሲሉ በአፅንኦት ተናግረዋል ።

 የምስራቅ ዕዝ አርባ ሰባተኛ አመት ምስረታ
የምስራቅ ዕዝ አርባ ሰባተኛ አመት ምስረታምስል Mesay Teklu/DW

በሌላ በኩል " ህዝባችን የኢትዮጵያን ሁኔታ በደንብ መረዳት አለበት ። በደንብ አልተረዳም ማንም ነው የሚነዳው ፣ የውጭ ኃይል መሳሪያ ይሆናል ። ተገዝቶ የሚዲያ ሰራተኛ ሆኖ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ይሰራል። ታጥቆ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ይሰራል" ሲሉ ወቅሰዋል።

ከአሁን በኃላ "ኢትዮጵያ እስካሁን እየተንከባለልን በመጣነው መንገድ መቀጠልጥል የምትችል አይመስለኝም"  ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ማሰብ አለበት። ሰራዊታችን ደግሞ ሀገሪቱን ለማስቀጠል ከዛሬ ቀደም ከከፈልነው መስዋዕትነት በላይ ለመክፈል መዘጋጀት አለበት ብለዋል።

"ሶስቴ አራቴ ሞክረው ልክ ገብተው አይቻልም ብለው ሄደዋል " በእጅ አዙር ሊዋጉን ይፈልጋሉ ። ነገር ግን በእጅ አዙርም ይምጣ በቀጥታም ይምጣ "የኢትዮጵያ አቅም አሁን ከባድ ነው" እኛን ያስቸገረን የኛ ባንዳ ነው ብለዋል።

ከአርባ ሰባት አመት በፊት የተመሰረተው የምስራቅ እዝ ላለፉት ተከታታይ ቀናት በልዩ ልዩ መርሀ ግብሮች የምስረታ በዓሉን እያከበረ ይገኛል። 

ከትናንት በስቲያ በጅግጅጋ እንዲሁም ትናንት እና ዛሬ በሀረር በተከናወኑ መርሀ ግብሮች የተገኙት የኤፌድሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ብርሀኑ ጁላ ሰሞንኛ ውጥረት በሆነው የሶማሊያ - ግብፅ - ኢትዮጵያ ጉዳይ ጠንከር ያሉ መልዕክቶችን ሲያነሱ ተደምጠዋል ። የኃገሪቱ መከላከያ ኃይል ኢትዮጵያን በሚመጥን መልኩ መደራጀቱንም አስገንዝበዋል።

መሳይ ተክሉ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር