1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጋምቤላ ውስጥ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ጥቃት

ሰኞ፣ ግንቦት 14 2015

የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በጋምቤላ ክልል ባደረሱት ጥቃት የ10 ሰዎች ሕይወት አለፈ። ከትናንት በስተያያ ቅዳሜ ማታ 5 ሰአት ገደማ ከደቡብ ሱዳን የመጡት ታጣቂዎች በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን ሁለት ወረዳዎች ውስጥ ጥቃቱን ማድረሳቸውን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/4RfnB
Äthiopien | Stadt Gambella
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ጥቃት

 ከደቡብ ሱዳን  ተነስተው ድምር ጥሰው ወደ ጋምቤላ ክልል በመሻገር በተለያየ ጊዜ ጥቃት ይፈጽማሉ። የተባሉ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በክልሉ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ስድስት ጊዜ ጥቃት አድርሰዋል። የክልሉ መንግሥት የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ እንዳመለከተው ታጣቂዎቹ ቅዳሜ ማታ በኑዌር ዞን ዋንቱዋ እና ማኩዌይ በተባሉ ወረዳዎች ውስጥ ባደረሱት ጥቃት የሰው ሕይወት ማለፉን ገልጸዋል። የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡቶው ኡኮት በሁሉቱም ወረዳዎች ጥቃቱ ቅዳሜ ማታ  የተፈጸመ መሆኑን አብራርተዋል። በዋንቱዋ ወረዳ በዕለቱ 20 በሚደርሱ ሰዎች ላይ ጉዳት የደረሰው ሲሆን ከዚህም መካከል  ዘጠኙ ሕይወታቸው ሲያልፍ በማኩዌይ ወረዳም የአንድ ሰው መሞቱን ጠቁመዋል። በሁለቱም ስፍራ በደረሰው ጥቃት በርካታ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱንም ተናግረዋል። በተደጋጋሚ ጥቃት የሚያደርሱት የሙርሌ ታጣቂዎች ከዚህ ቀደምም ሕጻናትን አግተው እንደነበር እና ከብቶች መዝረፍቸውን አቶ ኡቶው አክለዋል።

ከደቡብ ሱዳን ተነስተው በጋምቤላ ጉዳት የሚያደርሱ ታጣቂዎችን ለመከላከል በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም ጋምቤላን ከሚያዋስኑ የደቡብ ሱዳን ዞኖች ጋር በጁባ ከተማ ተወያይተው እንደነበርም ገልጸዋል። ከየካቲት ወር አጋማሽ ወዲህ የሙርሌ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ ተገድቦ ቢቆይም በድንገት ጥቃት ማድረስና ከብት መዝረፍ መቀጠላቸውን አስረድተዋል። በክልሉ ደረጃ የጸጥታ ሀይልን በተለይም በታጣቂዎች መግቢያ አካባቢ ስፍራውን በሚያውቁ የሚሊሻ አባላት እንዲጠበቅ እየተደረገ ነው ብለዋል። ጥቃት አድርሰዋል ከተባሉ ታጣቂዎች መካከል እስካሁን የተያዘ አለመኖሩንም ጠቁመዋል።

የኑዌር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቦዝ ቲር የሙርሌ ታጣቂዎች ከቅዳሜው ጥቃት በፊት በሌላ ወረዳ አንድ ወረዳው ውስጥ ባለፈው ሳምንት በሰው ላይ ጥቃት ፈጽመው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በቅዳሜው ጥቃት በአንድ ቤተ እምነት ውስጥ በነበሩ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ገልጸው ታጣቂዎቹ ከዞኑ በቅርብ ርቀት እንደሚንቀሳቀሱ እና እገዛ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል፡፡ በአኙዋ እና ኑር ዞን አዋሳኝ በኩል በድንገት ጥቃት እንደሚያደርሱም ገልጸዋል፡፡ በተደጋጋሚ ከደቡብ ሱዳን ተነስተው ወደ ጋምቤላ በመሻገር ጥቃት የሚያደርሱት ታጣቂዎቹ የካቲት 1 ቀን 2015 እንደዚሁ በክልሉ አኙአ ብሔረሰብ ዞን ውስጥ ባደረሱት ጥቃት የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉንና አንድ ሰው መቁሰሉን ዘግበን ነበር። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከፌደራል መንግሥት ጋር በመሆን እየተሠራ እንደሚገኝ የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ገልጸዋል።

ነጋሳ ደሳለኝ 

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ