1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ገና በአማራ ክልል የግጭት ድባብ እና የዋጋ ንረት ተጭኖታል

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 27 2016

ገና በአማራ ክልል የግጭት ድባብ እና የዋጋ ንረት ተጭኖታል። የቢቸና ነዋሪ “እበርካታው ሰው ቤት ሐዘን ስለገባ ከዚህ ቀደም እንደነበረው አይነት ድባብ ያየሁት የለም” ሲሉ ተናግረዋል። የጸጥታ ሁኔታው “ትንሽ አስቸጋሪ ነው” የሚሉት የደሴ ነዋሪ በበኩላቸው “ሕብረተሰቡ በጭንቀት ውስጥ ሆኖ የሚያሳልፈው በዓል” መሆኑን ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/4avYp
የገና ገበያ በባሕር ዳር ከተማ
የገና ገበያ በባሕር ዳር ከተማ ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ገና በአማራ ክልል የግጭት ሥጋት እና የዋጋ ንረት ተጭኖታል

የዘንድሮው የገና በዓል በአማራ ክልል በጦርነት ድባብ ለማክበር ህብረተሰቡ የተዘጋጀ ቢሆንም የአለው ወቅታዊ የክልሉ ፀጥታ ሁኔታ እንደበፊቶቹ ዳማቅ አያደርገውም ሲሉ የአነጋገርናቸው የአንዳንድ ከተሞች ነዋሪዎች አመልክተዋል፡፡ በሰሜን ወሎ ላሊበላ ከተማ ደግሞ በዓሉን በተሻለ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል፣ ምዕመናን ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ከተማዋ እየገቡ እንደሆነም ተገልጧል፡፡

ዛሬ በባሕር ዳር ሰባት አሚት የእንስሳት ግብይት በሚደረግበት ቦታ እንደተመለከትነው ሻጭና ገዥ እንደወትሮው በቦታው ተገኝተዋል፡ ምንም እንኳ በዚህ ዓመት በክልሉ ያለው የሰላም ሁኔታ የበዓሉን  ድባብ የቀዘቀዘ ቢያደርገውም ህብረተሰቡ እንደ አቅሙ የእርድ እንስሳትን ሲገዛና ሲሸጥ ተመልክተናል፡፡

የአማራ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት የሰላም ጥሪ

በስፍራው ያገኘናቸው አንድ ሻጭ የእንስሳት ዋጋ ወርዷል ቢሉም የባህር ዳር ከተማ ሸማች ግን እንስሳት ወደ ገበያ ብዙ አልገቡም፣ የገቡትም ቢሆን ዋጋቸው እጅግ ውድ እንደሆ ገልጠዋል ፣ በ62 ሺህ ብር አንድ የእርድ በሬ መግዛታቸውን ጠቅሰው፣ ከዚህ በፊት ግን ከ50 ሺህ ብር የበለጠ ወጪ  እንዳላወጡ አስረድተዋል፡፡ ዛሬ በሰባት አሚት በነበረው ገበያ ግን አንድ የእርድ በሬ እስከ 110 ሺህ የሚጠራ ሰንጋ መኖሩንም ነግረውናል፡፡

ባምላኩ አይተነው
ገበያው ከወትሮው እጅግ መወደዱን የተናገሩት ባምላኩ አይተነው በባሕር ዳር ከ100 ሺሕ ብር በላይ የተተመነ በሬ እንዳለ አስረድተዋል። ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በምስራቅ ጎጃም ዞን የቢቸና ከተማ አስተያየት ሰጪ ደግሞ በክልሉ ያለው ጦርነት በፈጠረው አውድ ሆኖ ሰው በዓሉን ለማክበር የሚያሳየው ነገር የለም ነው ያሉት፣ የመንገዶች መዘጋጋት የስጋ እንስሳቱን ጨምሮ ሌሎች ሸቀጦች መግብታ ባለመቻላቸው ኑሮ በእጅጉ ከባድ አድርጎታል ሲሉ ነው የገለጡት፡፡

በምዕራብ ጎጃም ዞን የቡሬ ከተማ ነዋሪም ቢሆኑ ህብረተሰቡ በዓሉን ለማክበር ጥረት እያደረገ ቢሆንም ስጋት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ “ሁለቱም ኃይሎች በቅርብ እርቀት ስለሚገኙ ከአሁን አሁን ምን ይፈጠር ይሆን የሚል ከፍተኛ ስጋት ባለበት ሁኔታ ነው ህብረተሰቡ በዓሉን ለማክበር እያሰበ ያለው፡፡” ብለዋል፡፡

ተፈናቃዮችን የማቋቋም ውጥንና የተፈናቃዮች ሥጋት

በደቡብ ወሎ ዞን የደሴ ከተማ ነዋሪ የእንስሳቱ ዋጋ የቀነሰ ቢሆንም የሌሎች ሸቀጦች ዋጋ ካለው የሰላም እጦት ጋር የበዓሉን አከባበር ጥላ ጥሎበታል ሲሉ ነው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬሌ የተናገሩት፣ ከሰሞኑ ከደብረ ብርሀን እስከ ደሴ ያለው መስመር የፀጥታ ችግር ያለበት በመሆኑ በበዓሉ አከባበር ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል ነው ያሉ፡፡

የገና ገበያ በባሕር ዳር ከተማ
የገና ገበያ በባሕር ዳር ከተማ ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በሰሜን ወሎ ዞን የቆቦ ከተማ ነዋሪ የገናን በዓል በታሻለ ሁኔታ ለማክበር በዓሉ ሀይማኖታዊ ይዘቱን ይዞ እንዲከበር የማክበሪያ ሰፊ ቦታ እንደተሰጠው አመልክተዋል፣ ነዋሪውም ምንም እንኳ ኑሮ ከባድ ቢሆንም ሰንጋዎችን ለመግዛት መዘጋጀቱን ገልጠዋል።

የአማራ ክልል ግጭትና የወባ በሽታ ስርጭት

የሰሜን ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ፀሐይነው ሲሳይ በስልክ እንደነገሩን የገና በየዓመቱ በድምቀት በሚከበርበት የላሊበላ ከተማ በድምቅት ለማክበር ዝግጅቶች ተጠናቅቀው ምዕመናን ወደ ከተማዋ በመግባት ላይ ናቸው፡፡ ከ40 በላይ ሆቴሎች በዓሉን ምክንያት በማድረግ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ያመለከቱት አቶ ፀሐይነው የየብስና የአየር ትራንስፖርትም ዝግጁ ሆነዋል ብለዋል፡፡

በአብዛኛዎቹ የአማራ ክልል አካባቢዎች በዓሉን ለማክበር ዝግጅቶች እየተደረጉ ቢሆንም የጦርነቱ ድባብና የኑሮ ውድነቱ የህብረተሰቡን ደስታ እንዳደበዘዘው ነዋሪዎቹ አመልክተዋል። 

ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ