ጀርመን ዋንጫውን ወሰደች
ሰኞ፣ ሐምሌ 7 2006ማስታወቂያ
ጀርመን ከ24 ዓመት በኋላ ነበር የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ባለቤት የሆነችው። እንደሚታወሰው እአአ በ1954, 1974, 1990 ዋንጫ አግኝተዋል።
የጀርመን ፕሬዚደንት ዮአኺም ጋውክ እና መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በሪዮ የማራካና ስቴድየም በመገኘት ጨዋታውን ተከታትለውታል። በጀርመን እግር ኳስ አፍቃሪዉ የሀገሩን ባንዲራ በየመኪና፤ ብስክሌቱ እያዉለበለበ፤ ወይም እየለበሰ፤ የሚወደዉን ተጨዋች ምሥል እያነገባ በየአዉራ ጎዳናዉ ሲዘዋወር ነበር የዋለዉ። የፌስታ ማወራረጃዉን (ባብዛኛዉ ቢራ) እየቋጠረ ጨዋታውን በትላልቅ ቴሌቪዥኖች በተሰቀሉበት አደባባዮች ተመልክቶታል። ከግጥሚያው በኋላ ሕዝቡ በየአደባባዩ በመውጣት ደስታውን ሲገልጽ አድሮዋል። አርጀንቲናዎችም ለፌስታ-ድግሥ ቢዘጋጁም አልቀናቸውም። የእግር ኳስ ተንታኞች ዋንጫዉ ከቦይነስ አይሪስ ይልቅ ወደ በርሊን እንደሚሔድ በሰፊዉ ገምተው ነበር።