1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ ኮሪያ እና አፍሪካ አንዳቸው ከሌላው የሚፈልጉት ምንድነው?

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ግንቦት 28 2016

በመጀመሪያው የኮሪያ አፍሪካ ጉባኤ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ እና የኬንያን ጨምሮ 25 የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል። ከደቡብ ኮሪያ የወጪ እና ገቢ ንግድ አፍሪካ ያላት ድርሻ ከ2% ያነሰ ነው። የአፍሪካ መሪዎች ደቡብ ኮሪያ ከደረሰችበት የቴክኖሎጂ ዕድገት እንድታቋድሳቸው ይፈልጋሉ። ደቡብ ኮሪያ በአንጻሩ በአፍሪካ ማዕድናት ላይ አይኗን ጥላለች።

https://p.dw.com/p/4gg9R
የኮሪያ አፍሪካ ጉባኤ
በኮሪያ አፍሪካ ጉባኤ 25 መሪዎችን ጨምሮ የ48 የአፍሪካ ሀገሮች ተወካዮች ተገኝተዋል። ምስል Yonhap/picture alliance

ደቡብ ኮሪያ እና አፍሪካ አንዳቸው ከሌላው የሚፈልጉት ምንድነው?

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የኬንያው አቻቸው ዊሊያም ሩቶ በጣልያን አፍሪካ ጉባኤ በተሳተፉ በስድስተኛ ወሩ ሴዑል ነበሩ። ሦስቱ የአፍሪካ ቀንድ ሃገራት መሪዎች በደቡብ ኮሪያ ብቻቸውን አልነበሩም።

በደቡብ ኮሪያ ፕሬዝደንት አስተናጋጅነት በተካሔደው የመጀመሪያው የኮሪያ አፍሪካ ጉባኤ ከአፍሪካ 25 መሪዎችን ጨምሮ የ48 ሃገራት ተወካዮች በጉባኤው ተገኝተዋል።

በጉባኤው በማዕድን፣ በኃይል እና ማምረቻው ዘርፍ ላይ ያተኮሩ 50 ገደማ ሥምምነቶች እንደተፈረሙ የደቡብ ኮሪያ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል። ሞዛምቢክ፣ ማዳጋስካር እና ታንዛኒያ ከደቡብ ኮሪያ መንግሥት እና ኩባንያዎች ጋር የተለያዩ ሥምምነቶች ከተፈራረሙ መካከል ናቸው።

ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ በቀጣይ አራት ዓመታት ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች የ1 ቢሊዮን ዶላር የፋይናንስ ሥምምነት መፈራረማቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። በጉባኤው ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደቡብ ኮሪያ ግንኙነት ትኩረት ሊያደርግባቸው ይገባል ያሏቸውን ሦስት ምክረ ሐሳቦች አቅርበዋል።

የመጀመሪያው የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን እና የትብብር ምርምርን ለማሳደግ የኮሪያ አፍሪካ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ማቋቋም ነው። ዐቢይ በከተማ ልማት፣ በማጓጓዣ እና በአርቴፊሺያል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ይፈልጋሉ።

የኢትዮጵያ እና የደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናት
ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ በቀጣይ አራት ዓመታት ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች የ1 ቢሊዮን ዶላር የፋይናንስ ሥምምነት መፈራረማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጽህፈት ቤት አስታውቋል። ምስል Office of the Prime Minister-Ethiopia

ደቡብ ኮሪያ ከፍተኛ እምርታ ካሳየችበት የቴክኖሎጂ ዕድገት እንድታቃምሳቸው ፍላጎታቸውን ያሳዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ብቻ አይደሉም። በጉባኤው ንግግር ባደረጉ የአፍሪካ መሪዎች ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል ተብለው የተነሱ ጉዳዮች ቢኖሩም ይኸው የቴክኖሎጂ ጉዳይ ግን ግንባር ቀደም ሆኖ ታይቷል።

የርዋንዳው ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ “ከአርቴፊሺያል ኢንተለጀንስ እና ሮቦቲክስ እስከ አነስተኛ የኑክሌር ኃይል ማመንጫዎች፣ በወሳኝ ጥሬ ማዕድናት የኃይል ሽግግርን ለማፋጠን አፍሪካ እና ኮሪያ ጎን ለጎን ሊሠሩ ሊሰሩ ይገባል” ሲሉ ተደምጠዋል።  

ከዚህ ቀደም የአፍሪካ መሪዎች በአንድ መሪ፣ በአንድ ሀገር በሚቀርብላቸው ግብዣ ተቀብለው እንደ የሩሲያ አፍሪካየቻይና አፍሪካየጣልያን አፍሪካ እና የአሜሪካ አፍሪካ በመሳሰሉ ስብሰባዎች መገኘታቸውን የነቀፉት የኬንያው ዊሊያም ሩቶ እንደ ሌሎች አቻዎቻቸው ሁሉ በደቡብ ኮሪያ ነበሩ።

ሩቶ በዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት ላይ ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል የሚሉትን ማሻሻያ ጉዳይ በኮሪያ አፍሪካ ጉባኤ ላይም አንስተዋል። ፕሬዝደንቱ ወደ ደቡብ ኮሪያ ባቀኑበት ኬንያ መቀመጫውን በሴዑል ያደረገው የዓለም አቀፉ የክትባት ኢንስቲትዩት አባል ሀገር ሆናለች። የኬንያ መንግሥት ከደቡብ ኮሪያ የወጪ ንግድ ባንክ ጋር የ238 ሚሊዮን ዶላር የፋይናንስ ሥምምነት ተፈራርሟል።

ሩቶ ለአፍሪካ የኤኮኖሚ ለውጥ ያስፈልጋል የሚሉትን የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማግኘት ግን እንደ ዐቢይ እና ፖል ካጋሜ ሁሉ አይናቸውን ደቡብ ኮሪያ ላይ ጥለዋል። “የኮሪያ እና አፍሪካ የተቀየረ አጋርነት ስኬታማ እና ዘላቂ እንዲሆን የአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት አቅምን በመጠቀም ላይ የታቀደ መሆን አለበት” ሲሉ የኬንያው ፕሬዝደንት ተናግረዋል። 

ዊሊያም ሩቶ
የኬንያው ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ከዚህ ቀደም በቡድን የአፍሪካ መሪዎች በአንድ ሀገር ተጋብዘው የሚሰበሰቡበትን ልማድ እንደሚያቆሙ ተናግረው የነበረ ቢሆንም ከሌሎች በርካታ አቻዎቻቸው ጋር በኮሪያ አፍሪካ ጉባኤ ታድመዋልምስል Dominika Zarzycka/NurPhoto/picture alliance

ዊሊያም ሩቶ “ኮሪያ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በተለይም በሮቦት፣ ባዮ ቴክኖሎጂ፣ አርቴፊሺያል ኢንተለጀንስ እና ኳንተም ኮምፒውቲንግ ዘርፎች የደረሰችበት አስደናቂ ግስጋሴ አፍሪካ ስኬታማ የኤኮኖሚ ሽግግር ለማድረግ ያላትን አቅም ያጎለብታል” የሚል ተስፋ አላቸው።

የአፍሪካ መሪዎች ዓይናቸውን የጣሉበት ቴክኖሎጂ በደቡብ ኮሪያ ኤኮኖሚ ዋንኛ ከሆኑ ዘርፎች ቀዳሚው ነው። በእስያ አራተኛ ግዙፍ ኤኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ደቡብ ኮሪያ ባለፈው ሚያዝያ ወር ብቻ 56 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሸቀጥ በዓለም ገበያ ሸጣለች። ቻይና እና አሜሪካ ቀዳሚ የደቡብ ኮሪያ ደንበኞች ናቸው። ማይክሮ ቺፕስ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቁሳቁሶች፣ ተሽከርካሪዎች እና የነዳጅ ውጤቶች ሀገሪቱ ከወጪ ንግድ ጠቀም ያለ ገቢ ከምታገኝባቸው ሸቀጦች መካከል ይመደባሉ።

እንደ ብዙ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ ሀገሮች ሁሉ ደቡብ ኮሪያም ከአፍሪካ ጋር በሚኖራት ግንኙነት በተለይ በማዕድናት ላይ ዓይኗን ጥላለች። ዛሬ ረቡዕ በተካሔደ የቢዝነስ ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝደንት ዩን ሱክ ዮል “በወሳኝ ማዕድናት ረገድ ከአፍሪካ አገሮች ጋር አጋርነት ለማበጀት እና ተመሳሳይ እሴት ካላቸው ሃገራት ጋር ለሁሉም ጠቃሚ የሆነ የቁልፍ ማዕድናት ደሕንነት ትብብር ለማስፋት ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ እቅጩን ተናግረዋል።

ትናንት ማክሰኞ ከተካሔደው ጉባኤ በኋላ የአፍሪካ እና የደቡብ ኮሪያ መሪዎች በማዕድናት ዘርፍ ያለውን ትብብር ለማጠናከር ያለመ የከፍተኛ ባለሥልጣናት ውይይት ለመጀመር መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

የዕቃ መጫኛ እና ማውረጃ እና ኮንቴይነት በደቡብ ኮሪያ
የደቡብ ኮሪያ ኤኮኖሚ ከእስያ በአራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ሀገሪቱ ከአፍሪካ ያላት የንግድ ግንኙነት እጅግ አናሳ ነው። ምስል picture-alliance/NurPhoto/Seung-il Ryu

አፍሪካ የደቡብ ኮሪያ የማይክሮቺፕስ እና የኤክትሪክ ተሽከርካሪ አምራቾች በጥብቅ የሚፈልጓቸው ኒኬል፣ ኮባልት፣ ግራፋይት እና ሊቲየም ማዕድናት መገኛ ነች። የደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናት በማዕድናት እና ሌሎች የተፈጥሮ ሐብቶች ረገድ ግንኙነቷን ማስፋቷ ለኢንዱስትሪው አስተማማኝ የአቅርቦት ሰንሰለት ይፈጥራል የሚል ተስፋ አድሮባቸዋል።

ፕሬዝደንት ዩን ሱክ ዮል ደቡብ ኮሪያ ለአፍሪካ የምትሰጠው የልማት እርዳታ በሚቀጥሉት አምስት ገደማ ዓመታት በእጥፍ ጨምሮ 10 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያድግ ተናግረዋል። ፕሬዝደንቱ “የኮሪያ ኩባንያዎች ወደ አፍሪካ በቀላሉ የሚገቡበትን መንገድ ለማመቻቸት ወደ 14 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ በወጪ ንግድ ለተሰማሩ ኩባንያዎች ይቀርባል” ብለዋል።

ደቡብ ኮሪያ የአፍሪካ መሪዎችን ያስተናገደችው ሰሜን ኮሪያ በተንሳፋፊ ፊኛዎች ቆሻሻ እና እዳሪ ወደ ግዛቷ አሻግራ ባራገፈች በጥቂት ቀናት ልዩነት ነው። ዩጋንዳ፣ ዚምባብዌ እና ሞዛምቢክን ከመሳሰሉ የአፍሪካ ሀገራት ለረዥም ዓመታት የዘለቀ ግንኙነት ያላት ሰሜን ኮሪያ ፕሬዝደንት ዩን ሱክ ዮል ሥልጣን ከያዙ በኋላ ከደቡብ ኮሪያ ጋር የገባችበት ውዝግብ እንደገና የማገርሸት አዝማሚያ አሳይቷል።

ፕሬዝደንት ዩን ሱክ ዮል ከኪም ጆንግ ዑን የአሜን ኮሪያ መንግሥት ከደቡብ ኮሪያ ጋር በገባበት ፍጥጫ እንደ አሜሪካ ካሉ ልዕለ ኃያላን በተጨማሪ አፍሪካን ከጎናቸው ማሰለፍ ይፈልጋሉ።

ደቡብ ኮሪያ እና ወደ ሴዑል ያቀኑ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በጥምረት ባወጡት የአቋም መግለጫ የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት በሰሜን ኮሪያ ላይ ያስተላለፈው የውሳኔ ሐሳብ ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ