1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡባዊ ጀርመን ጎርፍ እና የመንግስት ምላሽ

ዓርብ፣ ሰኔ 7 2016

በደቡባዊ የጀርመን ግዛቶችን ጎርፍ ያደረሰውን ጉዳት ተከትሎ የድንገተኛ አደጋ መድን ሽፋን በሀገር አቀፍ ደረጃ አስገዳጅ ሆኖ እንዲተገበር ተጠይቋል።በሰሞኑ የጎርፍ አደጋ የአምስት ሰዎችን ሕይወት ጠፍቷል፤ ከሁለት ቢሊዮን ዩሮ በላይ የኢኮኖሚ ጉዳትም ደርሷል።

https://p.dw.com/p/4h39U
Überschwemmungen in Süddeutschland | Pfaffenhofen an der Ilm
ምስል Wolfgang M. Weber/IMAGO

ደቡባዊ ጀርመን ጎርፍ እና የመንግስት ምላሽ


አደጋውን ተከትሎ የጀርመን የአካባቢ ሚኒስቴር መሰል አደጋዎችን ለመካላከል የሚያስችል ሕግ በማርቀቅ ላይ መሆኑን አስታውቋል።

ካለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ አንስቶ ለቀናት የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ የደቡባዊ ጀርመን ግዛቶችን በእጅጉ ማጥቃቱ ይታወሳል። ወንዞች ሞልተው፣ ግድቦች ገደባቸውን ጥሰው የስራ እና መኖሪያ አካባቢዎችን ማጥለቅለቃቸውን ተከትሎ የአምስት ሰዎችን ሕይወት አልፏል። እስካሁን በተደረግ ጥናት ጎርፉ ከሁለት ቢሊዮን ዩሮ በላይ የኢኮኖሚ ጉዳትም አድርሷል።

በአደጋው በዋንኛነት የተጠቁት የባቫሪያን እና የባደን ቩተምበርግ ግዛቶች ሲሆኑ፥ የእርሻ ማሳዎች፣ ፋብሪካዎች እና አነስተኛ ቢዝነሶች ከፍ ያለ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በ130 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ማሳቸው በጎርፍ የተጥለቀለቀባቸው ጆርጅ ሽላክትቦየር ለዶቸ ቬለ እንደተናገሩት፣ የደረሰ የድንች እና የስንዴ ምርታቸውን ከመሰብሰባቸው በፊት የተከሰተው ጎርፍ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ከጥቅም ውጪ አድርጎታል። “ልፋታችን በሙሉ መና ቀርቷል፤ በማረሻ መኪና እንኳን ወደ ማሳው መዝለቅ አልቻልንም። እናም መንግስት የሚሰጠንን ድጋፍ እየጠበቅን ነው” ብለዋል።የጀርመን ገበሬዎች መንግሥትን በመቃወም አድማ መቱ

በአደጋው በዋንኛነት የተጠቁት የባቫሪያን እና የባደን ቩተምበርግ ግዛቶች ሲሆኑ፥ የእርሻ ማሳዎች፣ ፋብሪካዎች እና አነስተኛ ቢዝነሶች ከፍ ያለ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በአደጋው በዋንኛነት የተጠቁት የባቫሪያን እና የባደን ቩተምበርግ ግዛቶች ሲሆኑ፥ የእርሻ ማሳዎች፣ ፋብሪካዎች እና አነስተኛ ቢዝነሶች ከፍ ያለ ጉዳት ደርሶባቸዋል።ምስል ANNA SZILAGYI/EPA

ቬከር ኖይሰን የተባለ የኮንስትራክሽን ማሽነሪ ማምረቻ ደግሞ በጎርፉ ጉዳት ከደረሰባቸው ፋብሪካዎቸ መካክል አንዱ ነው። ምርቶቹን ወደ ዓለም አገራት ይልክ የነበረው ይህ ፋብሪካ በዋና ማምረቻው እና በምርት ማከማቻ ማዕከሉ ላይ ጉዳት በመድረሱ ሙሉ በሙሉ ስራ አቁሟል። የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ ሔልሙት ቦየር እንዳሉት፣ የደረሰው ጉዳት መጠን ገና አልታወቀም፤ ዳግም ስራ ለመጀመርም ከሳምንታት በላይ ሊወስድ ይችላል።በተለያዩ ሃገራት የተባባሰው ዝናብና ጎርፍ

የመኪና መሸጫ መደብር ባለቤቱ አልሚር አሊኒ በበኩሉ፣ የስራ ቦታው ሙሉ በሙሉ በጎርፉ በመጥለቅለቁ ራሱን እና ቤተሰቡን ይዞ መሸሹን ተናግሮ፥ ዳግም ስራ ከመጀመሩ አስቀድሞ የደረሰውን የጉዳት መጠን እያጣራሁ ነው ብሏል። ይሁንና አነስተኛ መደብሩ ለመሰል አደጋ የመድን ሽፋን ስለሌለው የመንግስትን እገዛ እየጠበቀ እንደሆነ ተናግሯል።

የፌዴራሉ መንግስት እና የአደጋው ዋንኛ ሰለባ የሆኑት የባቫሪያን እና የባደን ቭትንበርግ ግዛቶች ለተጎጆዎች የአስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያደርሱ አስታውቀዋል። ይሁንና ጉዳዩን የሚከታተሉ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች መንግስት በአደጋ መከላከል ስራ ላይ የሚጠበቅበትን አልሰራም ሲሉ ይተቻሉ። ለማሳያም በ2023 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ለአደጋ መከላከል ከተያዘው የ100 ሚሊየን ዩሮ በጀት አርባ በመቶው ጥቅም ላይ አለመዋሉን ይጠቅሳሉ።

የፌዴራሉ መንግስት እና የአደጋው ዋንኛ ሰለባ የሆኑት የባቫሪያን እና የባደን ቭትንበርግ ግዛቶች ለተጎጆዎች የአስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያደርሱ አስታውቀዋል።
የፌዴራሉ መንግስት እና የአደጋው ዋንኛ ሰለባ የሆኑት የባቫሪያን እና የባደን ቭትንበርግ ግዛቶች ለተጎጆዎች የአስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያደርሱ አስታውቀዋል። ምስል Daniel Reinelt/Eibner/IMAGO

የጀርመን የአካባቢ ሚኒስትር ስቴፊ ለምከ፥ በበኩላቸው ለዴር ሽፒገል መጽሔት በሰጡት ቃል፥ “ነገሮች እንደቀደመው ጊዜ አይቀጥሉም፤ ከዚህ በኋላ ለመሰል ተደጋጋሚ የተፈጥሮ አደጋዎች ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን” ብለዋል። የአረንጓዴ ፓርቲ አባል የሆኑት ሚኒትሯ አክለውም፣ የጎርፍ አደጋ መከላከል ህግ አርቅቀው በዚሁ ዓመት ለማስተግበር እየሰሩ እንደሆነ አስታውቀዋል። በህግ የተደገፈ የአደጋ መከላከል እስካልተተገበረ ድረስ መሰል አደጋዎች የሚያደርሱት ጉዳት እና ከጉዳቱም ለመውጣት የሚጠይቀው ሃብት በእጅጉ እንደሚጨምርም ሚኒስትሯ አሳስበዋል።

መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ከቀናት በኋላ ከአስራ ስድስቱ  የጀርመን ግዛቶች መሪዎች ጋር በሚያደርጉት ምክክር፣ መሰል አደጋዎችን የመከላከል እና ጉዳት የደረሰባቸውን የመደገፍ ተግባራት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ ተብሏል። በውይይታቸው ከሚያነሷቸው አጀንዳዎች መካከል የድንገተኛ አደጋ መድን ሽፋን በአቀፍ አቀፍ ደረጃ አስገዳጅ ሆኖ እንዲተገበር የሚለው አንዱ ይሆናልም ተብሎ ይጠበቃል። ሾልስ በአደጋው ማግስት ለእንደራሴዎች ምክር ቤት አባላት ባደረጉት ንግግር ይህንኑ ጉዳይ አንስተው እንደነበር ይታወሳል።

በሸማቾች ጥበቃ ላይ መንግስትን የሚያማክረው የባለሙያዎች ቦርድ በበኩሉ፣ በሕግ ደረጃ አስገዳጅ የመድን ሽፋንን መተግበር እንደሚቻል ጠቅሶ፥ ነገር ግን የመድን ሽፋን ሰጪ ኩባንያዎችን የመምረጥ መብቱ ለሸማቹ ሊተው ይገባል ሲል ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

መሳይ ወንድሜነህ
ፀሀይ ጫኔ
ሂሩት መለሰ