ያመፁ ወታደሮችና የኤርትራ መንግሥት
ማክሰኞ፣ ጥር 14 2005ትናንት ባመጹ ወታደሮች ተቋርጦ ነበር የተባለው የኤርትራ መንግሥት ቴሌቪዥን ስርጭት መቀጠሉ ተዘገበ ። በፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ መሰረት የኤርትራ መንግሥትም በዋና ከተማይቱ አስመራ ሁሉም ነገር ሠላማዊ መሆኑን አስታውቋል ። ይሁንና በጉዳዩ ላይ ለዶቼቬለ አስተያየታቸውን የሰጡ የፖለቲካ ተንታኞች ፣ ያመጹት የኤርትራ ወታደሮች እርምጃ በኤርትራ መንግሥት ውስጥ ውጥረቱ የመባባሱና የአገዛዙ የመዳከም ምልክት መሆኑን ተናግረዋል ።
የኤርትራ ፕሬዝዳንት የአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ቃል አቀባይ አቶ የማነ ገብረ መስቀል እንደ ትናንት ሁሉ ዛሬም አስመራ ሰላማዊ ናት ማለታቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል ። አንድ የተቃዋሚ ድረ ገፅን የጠቀሰው AFP ወደ 100 ይጠጋሉ ያላቸው ትናንት የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴርን የተቆጣጠሩ ያመፁ ወታደሮች አዛዥ እጃቸውን ለመስጠት መስማማታቸውን ዘግቧል ።
የዘገባው እውነትነት ግን በሌላ ምንጭ አልተረጋገጠም ። አንዳንድ ምንጮችም የወታደሮቹን እርምጃ ከመፈንቅለ መንግሥት ጋር አስተካክለውታል ። በብሪታኒያው የጥናት ተቋም ቻተምሃውስ የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳዮች አጥኚ አህመድ ሶልሜን ግን ከኤርትራ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት በማይቻልበት ሁኔታ የተፈፀመውን ለማወቅ አዳጋች መሆኑን ነው ለዶቼቬለ የተናገሩት ።
« መፈንቅለ መንግሥት ወይም በወታደሩ ውስጥ አመፅ ነበር ለማለት አስቸጋሪ ነው ። በአሁኑ ጊዜ የትናንቱ እርምጃ ውጤት ምን እንደሆነ ለማወቅ መጠበቅ አለብን ። ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ሁኔታው ምን እንደሆነ አናውቅም ። ሆኖም የሆነ አይነት አመፅ እየተካሄደ ነው ። »
በአንዳንድ ዘገባዎች እንደተጠቆመው ወታደሮቹ ህገ መንግሥቱ እንዲከበርና የፖለቲካ እሥረኞች እንዲፈቱ የሚጠይቀው መግለጫቸው ትናንት በኤርትራ ቴሌቪዥን እንዲነበብ አድርገዋል ። የአፍሪቃ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች አማካሪና የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር ማሃሪ ታደለ ማሩ የወታደሮቹ እርምጃ ለመንግሥት የማስጠንቀቂያ ደውል ነው ይላሉ ።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ይህን መሰሉ የአመፅ እንቅስቃሴ መካሄዱ ሲነገር የአሁኑ የመጀመሪያው ነው ። ይህ ወዴት ሊያመራ ይችላል ? ምንስ ያመለክታል ተብለው የተጠየቁት የቻተም ሃውሱ ተንታኝ አህመድ ሶልመን ሲመልሱ
« ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማምጣት አለማምጣቱ ወደፊት የሚታይ ይሆናል ። እኔ ግን ለውጥ ማምጣቱን እጠራጠራለሁ ። ኢሳያስ ሁኔታዎችን መቆጣጠር የሚችሉ ይመስለኛል ። ሆኖም በርግጥ ይህ እርምጃ በቅርቡ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ አሊ አብዶ ከድተው መኮብለላቸው ከተዘገበ በኋላ የተወሰደ 2 ተኛ እርምጃ ነው ። ስለዚህ በራሱ በአስመራ መንግሥት ውስጥ ውጥረቱ እየተጠናከረ የመምጣቱ ምልክቶች አሉ ። »
የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር መሃሪም ተመሳሳይ አስተያየት ነው ያላቸው ።
ትናንት በኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ያመፁ ወታደሮች ወሰዱ የተባለው እርምጃ የቻተም ሃውሱ ተንታኝ አህመድ ስልሜን እንዳሉት የህዝቡ ብሶት መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ።
« የተደማመረ ነገር እንዳለ ይታያል የሰብአዊ መብት ይዞታው ወጣት ኤርትራውያን በግዳጅ ለውትድርና መመልመላቸውና በአነስተኛ ክፍያም ለረዥም ጊዜ እንዲያገለግሉ በመደረጉ በርካታ ወጣት ዜጎች ህይወታቸውን ለማትረፍ ወደ ሌሎች የአካባቢው ሃገራት እየተሰደዱ ነው ። ስለዚህ ባለፉት 24 ሰአታት የተከናወኑት ድርጊቶች ለተፈፀሙት ሁኔታዎች እንደ ምሬት መግለጫ ሆነው ነው የሚታዩ ይመስለኛል ። ይህ እንደሚሆንም የሚጠበቅ ነው ። ሆኖም በኛ ግምት ይህ የአገዛዙ መዳከም ምልክት ነው ። »
ሂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ