ያልለየለት የቡርኪና ፋሶ ዕጣ
ሐሙስ፣ ኅዳር 4 2007የጦር ኃይሉ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ሲቭሉ ማህበረሰብ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረትም ተስማምተዋል። የፕሬዚደንቱ ከሥልጣን መወገድ ለረጅም ዓመታት የዘለቀውን የአንድ ግለሰብ አገዛዝ በማክተሙ በሀገሪቱ እፎይታ ፈጥሯል። ያም ቢሆን ግን፣ ይኸው ርምጃ በቡርኪና ፋሶ ሰላም እና መረጋጋት ማምጣቱ አሁንም አጠራጣሪ እንደሆነ ይገኛል።
የቡርኪና ፋሶ የቀድሞ ፕሬዚደንት ብሌዝ ካምፓዎሬን የ27 ዓመታት አገዛዝ ለማራዘም በማሰብ ለምክር ቤቱ የቀረበውን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ረቂቅ ሕግ በመቃወም በመቶ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ ነበር በመዲናይቱ ዋጋዱጉ ለበርካታ ቀናት አደባባይ የወጣው። የወጣበት ዓላማውንም ከግብ በማድረስ ሥልጣኑን እንደጨበጡ ለመቆየት የሞከሩትን ፕሬዚደንቱን ማባረር ችሎዋል። ለዚህ ግን ትልቅ መሥዋዕትነት ነበር የከፈለው። የሲቭሉ ማህበረሰብ ተወካዮች እንዳመለከቱት፣ በዚሁ ተቃውሞ ቢያንስ 30 ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ180 የሚበልጡ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸው አሁንም በሐኪም ቤት ውስጥ ይገኛሉ። ከነዚሁ መካከል አንዱ የ25 ዓመቱ ባሶሌ ኮንስቶን ሲሆን፣ ተቃዋሚውን ለመበተን የተሰማራው የፀጥታ ኃይል ዛቻ ዓላማውን እውን ከማድረግ እንዳላገደው በቆራጥነት ነበር የገለጸው።
«እንደሚተኩሱብን ቢያስጠነቅቁንም፣ እኛ ለነርሱ ዛቻ እንደማንበረከክ በመገለጽ ተቃውሞአችንን በቁርጠኝነት ቀጥለንበታል። በዚህ ጊዜ ነበር እኔ እጄን፣ ከኔ ጋር የነበረው ደግሞ ራሱን በጥይት የተመታነው ። »
ባሶሌ ኮንስቶ ከሞት በመትረፉ ደስተኛ መሆኑን በማስታወቅ፣ ካምፓዎሬን ያወረደው የሕዝብ ዓመፅ ያለውጤት እንደማይቀር ተስፋውን ገልጾዋል። ይሁንና፣ በቡርኪና ፋሶ የሕዝቡን ተቃውሞ በተከተሉት ቀናት የታየው ሁኔታ ግን ይህ ተስፋው እውን መሆኑን አጠራጣሪ አድርጎታል።
ካምፓዎሬ እንደወረዱ የጦር ኃይሉ ሥልጣን በያዘበት ድርጊት ያልተደሰቱት የቡርኪና ፋሶ የተቃዋሚ ቡድኖች እና የሲቭሉ ማህበረሰብ ከብዙ ውይይት በኋላ ለአንድ ዓመት የሚቆይ በሲቭሉ የሚመራ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ተስማምተዋል። በስምምነቱ መሠረት፣ እአአ ህዳር 2015 ዓም በሀገሪቱ ምክር ቤታዊ እና ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ይደረጋል። ይሁንና፣ የሽግግሩን መንግሥት ምን እንደሚመራው እስካሁን በግልጽ አልታወቀም። እንደሚታየው፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በጣም መ የተከፋፈሉ ናቸው። የብዙዎቹ መሪዎች በብሌዝ ካምፓዎሬ የዴሞክራሲ እና መሻሻል ፓርቲ አባላት የነበሩ ናቸው፣ ከነዚህም በቀድሞው ፕሬዚደንት ችላ እንደተባሉ የተሰማቸው ጥቂት የማይባሉት የራሳቸውን ጥቅም የማስጠበቅ ዓላማ ይዘው የተነሱ መሆናቸው ይነገራል። እና ብዙ የፖለቲካ ታዛቢዎች እንዳስረዱት፣ የሽግግሩን መንግሥት አመራር በወቅቱ የያዙት የጦር ኃይሉ ሊየተና ኮሎኔል ያኩባ ኢዛክ ዚዳ በሥልጣኑ ኮርቻ እንደተቆናጠጡ ይቆያሉ የሚለው ሳይሆን ችግሩ፣ እስከ ምርጫው ድረስ ሊተካቸው የሚችል ተስማሚ ሲቭል ዕጩ መታጣቱ ነው። ተሰሚነት ያላቸው የተቃዋሚው ቡድን ተወካይ እና ራሱን የልማት እና የለውጥ ፓርቲ ብሎ የሚጠራው ፓርቲ መሪ ሳራ ሴሬም ግን የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ምክክር የያዙት የተለያዩት ወገኖች የሽግግሩን መንግሥት በሚመራው ዕጩ ላይ በቅርቡ ገላጋይ ሀሳብ ላይ መድረሳቸው እንደማይቀር ለቡርኪና ፋሶ ሕዝብ ቃል በመግባት፣ በሀገሪቱ ደህና ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
« ሰላም እንደሚሰፍን እና አዲሶቹ መሪዎችም ለሕዝቡ እና ለሀገሪቱ የሚበጀውን ልማት እና መሻሻል እንደሚያስገኙ ተስፋችን ነው። የሽግግሩ ጊዜ ትክክለኛ፣ ሰላማዊ፣ ወደዴሞክራሲያዊው ምርጫ የሚያመራ እና በሀገሪቱም ዴሞክራሲያዊውን ሥርዓት የሚተክል እንደሚሆን ነው ተስፋ የምናደርገው። »
ያን ፊሊፕ ሾልስ/አርያም ተክሌ
ነጋሽ መሀመድ