1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትኢትዮጵያ

የ12ኛ ክፍል ፈተና ክርክር

ዓርብ፣ ኅዳር 28 2016

በታዳጊነት እድሜ የሚገኙ አራት ተማሪዎችን በዚሁ ጉዳይ ላይ ልናከራክራቸው ወደናል፡፡ ተማሪዎቹ ጠንከር ያለውን የ12ኛ ክፍል የፈተና አሰጣጥና በርካቶችን ከዩኒቨርሲቲ መግቢያ ያራቀውን ውጤት በሁለት መልኩ አይተው ትችትና ሙገሳቸውን ችረውታል፡፡

https://p.dw.com/p/4YmCR
አምስት ወጣቶች ቁጭ ብለው
ሊዲያ መለስ እና ተወያዮቿምስል S. Getu/DW

የ12ኛ ክፍል ፈተና ክርክር

የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር በዚህ ዓመት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤትን ይፋ ሲያደርግ በ2015 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከተፈተኑት 845,000 ተማሪዎች ውስጥ ከ96 በመቶ የላቁቱ ፈተናውን አላለፉም ወይም የፈተናውን 50 በመቶ ጥያቄ በትክክል አልመለሱም፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፈሰር ብርሃኑ ነጋ በወቅቱ በሰጡት መግለጫ እንዳብራሩትም በ2015 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ብሔራዊ ፈተናውን ተፈትነው ውጤታቸው ይፋ ሲሆን፤ ከ 3,106 ትምህርት ቤቶች 1,328ቱ አንድም ተማሪ ማሳለፍ አለመቻላቸው  ተነስቷልም፡፡

በዚህ የዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች የሬዲዮ መሰናዶ በታዳጊነት እድሜ የሚገኙ አራት ተማሪዎችን በዚሁ ጉዳይ ላይ ልናከራክራቸው ወደናል፡፡ ከአራቱ ተማሪዎች ሁለቱ ብሔራዊ ፈተናውን የተፈተኑ ሲሆን ሁለቱ ደግሞ የ11 እና 12ኛ ክፍል ተማሪ ናቸው፡፡ ተማሪዎቹ ጠንከር ያለውን የ12ኛ ክፍል የፈተና አሰጣጥና በርካቶችን ከዩኒቨርሲቲ መግቢያ ያራቀውን ውጤት በሁለት መልኩ አይተው ትችትና ሙገሳቸውን ችረውታል፡፡

የፈተና አሰጣጥ ሂደቱ ደጋፊዎች

የፈተና አሰጣጥ ሂደቱን አስፈላጊነት አሞግሰው አስተያየት የሰጡቱ ተማሪዎች በአገሪቱ  በርካታ ሰዎች ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርት ተከታትለው አጠናቀው ሲወጡ በብዛት ስራ አጥ መሆናቸው ከወዲሁ ጥራት ያለውን የሰው ሃይል የማዘጋጀት አስፈላጊነት ያነሳሉ፡፡ እንደ እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች ፈተናው ኩረጃን በጥብቅ ክትትል የሚያስቀር ሂደት ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ በራስ መተማመን እና በራስ ጥረት የሚያምኑ ተማሪዎች ብቻ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን እንዲቀላቀሉ ይረዳል፡፡

የፈተና አሰጣጥ ሂደቱን የሚቃወሙ

በሌላ በኩል ደግሞ ድንገት ተነስቶ በ12ኛ ክፍል ብቻ ጠንከር ባለ ሁኔታ ፈተናን በመስጠት ተፈላጊውን የትምህርት ጥራት ማረጋገጥ አይቻልም የሚሉት ተሟጋቾች፤ ጥራት ያለው ትምህርትን አስቀድሞ ከታች በመጀመር መስጠት ሲገባው በ12ኛ ክፍል ብቻ በዚህ መጠን ተማሪዎችን የጣለ ፈተና መስጠት ለወላጅና ተማሪዎቹ ሞራልም ኪሳራ አድራሽ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ ሃሳብ የሞገቱት ተማሪዎቹ ሰፊ የጸጥታ ችግር ባለበት ሁኔታ የተማሪዎቹ በበቂ ሁኔታ መዘጋጀት ጥያቄ ውስጥ በሚገባበት ወቅት፣ ከታች ጀምሮ የመምህራን እና ትምህርት ቤቶችም ጥራት በአስተማማኝነት ሳይገመገም ተማሪዎች ላይ ብቻ የወደቀው ፈተና የትምህርት ጥራቱን ለማምጣት ትክክለኛው መንገድ መሆኑን በአጠራጣሪነት ያነሳሉ፡፡ በመሆኑም ከፈተናው ባሻገር በትምህርት አሰጣጥ ሂደቱ አስፈላጊነት ላይ ሊቶከር ይገባል በማለት ሃሳባቸውን አንስተዋል፡፡

ከዚህ በተቃራኒው በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መርካታቸውን የገለጹት የክርክሩ ተሳታፊዎች ከታች ጀምሮ ለትምህርት ጥራት አስፈላጊ የሆኑ ተግባራትን መከወን ከምንም በላይ ወሳኝ ቢሆንም ከታች አልተሰራም ተብሎ የ12ኛ ክፍልን ተማሪዎች በዘፈቀደ እና በገፍ የሚያልፉበት ፈተና መሰጠት የለበትም ብለዋል፡፡

ክርክራቸውን በድምፅ ማድመጥ ይቻላል።

 

አወያይ: ሊዲያ መለስ

አዘጋጅ: ሥዩም ጌቱ