1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አትሌት ታምራት ቶላ በፓሪስ ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያን አሸነፈ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 4 2016

የፓሪስ ኦሎምፒክ ማራቶን አሸናፊው አትሌት ታምራት ቶላ የህይወቴ ትልቁን ጎል አሳክቻለሁ አለ። አትሌቱ እጅግ በጣም አስቸጋሪ የነበረውን የፓሪስ ወበቅ ተቋቁሞ የኦሎምፒክ ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያን ከ24 ዓመታት በኋላ ለሀገሩ አስገኝቷል።

https://p.dw.com/p/4jKWO
አትሌት ታምራት ቶላ
አትሌት ታምራት ቶላምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance

የፓሪስ ኦሎምፒክ ማራቶን አሸናፊው አትሌት ታምራት ቶላ የህይወቴ ትልቁን ጎል አሳክቻለሁ አለ። አትሌቱ እጅግ በጣም አስቸጋሪ የነበረውን የፓሪስ ወበቅ ተቋቁሞ የኦሎምፒክ ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያን ከ24 ዓመታት በኋላ ለሀገሩ አስገኝቷል። 
ታምራት ቶላ ዛሬ ጠዋት የተካሄደውን የማራቶን ውድድር 2 ሰዓት ከ06 ደቂቃ ከ26 ሰከንድ በሆነ ጊዜ መግባት ችሏል። 
በውድድሩ ታምራት በኬንያዊው አትሌት ሳሙኤል ዋንጂሩ ተይዞ የነበረውን 2:06.32 ሰዓት በማሻሻል አዲስ የኦሎምፒክ ክብረ ወሰን ማስመዝገብ ችሏል። አትሌቱ  ከድሉ በኋላ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ «ይህ ቀን ለእኔ የተለየ ነው ፤ ፓሪስን አመሰሰግናለሁ» ብሏል። 
በውድድሩ ትውልደ ሶማሊያዊው  በሽር አብዲ ለቤልጅየም የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል። የቶኪዮ ኦሎምፒክ ፣ የቦስተን እና ቺካጎ ማራቶኖች አሸናፊ እና በዚሁ ውድድር የማሸነፍ ከፍተኛ ግምት የተሰጠው ኬንያዊው ቤንሰን ኪፕሩቶ ሶስተኛ በውጣት ለኬንያ የነሐስ ሜዳሊያ አስገኝቷል። 

አትሌት ታምራት ቶላ ውድድሩን ሪከርድበማሻሻል ጭምር ውድድሩን ያጠናቅቅ
አትሌት ታምራት ቶላ ውድድሩን ሪከርድበማሻሻል ጭምር ውድድሩን ያጠናቅቅምስል JOEL CARRETT/AAP/IMAGO


በውድድሩ የተሳተፈው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ዴሬሳ ገለታ አምስተኛ ሲወጣ አንጋፋው አ,ትሌት ቀነኒሳ በቀለ 39ኛ በመውጣት ውድድሩን አጠናቋል። 
በማራቶን የፈጣን ሰዓት ባለቤት እና በዚህ ውድድር ታሪክ ሊሰራ ይችላል ብለው ኬንያዊያን ተስፋ አድርገውበት የነበረው ኪፕቼጌ ውድድሩን አቋርጦ ለመውጣት ተገዷል።
በፓሪስ ኦሎምፒክ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘው ታምራት ቶላ በተጠባባቂነት ተይዞ የነበረ ሲሆን አትሌት ሲሳይ ለማ መጎዳቱን ተከትሎ ተክቶ መግባቱ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ የኦሎምፒክ የማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ለመጨረሻ ጊዜ ያገኘችው በሲዲኒ ኦሎምፒክ ከ24 ዓመታት በፊት ነበር። 
በፓሪስ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የሩጫ ውድድሮች ዛሬ ምሽት እና ነገ ጠዋት ይደረጋሉ ። ምሽት 3 ሰዓት ላይ የወንዶች የ5 ሺ ሜትር የፍጻሜ ውድድር ፤ ምሽት 3 ሰዓት ከ25 ላይ የሴቶች የ1500 ሜትር የፍጻሜ ውድድር እንዲሁም ነገ እሁድ ጠዋት 3 ሰዓት ላይ የሴቶች የማራቶን ውድድር ይደረጋል ።
ሃይማኖት ጥሩነህ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር